ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ20ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሰረት በማድረግ የሳምንቱን ምርጥ ቡድን እንዲህ አሰናድተናል።

አሰላለፍ 3-4-2-1

ግብ ጠባቂ


ፋሲል ገብረሚካኤል – ባህር ዳር ከተማ

በግብ ጠባቂዎቹ ደካማ አቋም እና ግለሰባዊ ስህተቶች በተደጋጋሚ ዋጋ ሲከፍል የሰነበተው ባህር ዳር ከተማ በዚህ ሳምንት የፋሲል አቋም አትርፏል ማለት ይቻላል። ግብ ጠባቂው አንድ ግብ ቢያስተናግድም መከላከያዎችን አሸናፊ ማድረግ የሚችሉ አራት አጋጣሚዎችን በጥሩ የጊዜ አጠባበቅ እና የግብ ጠባቂ ክህሎት የግቡን መስመር እንዳያቋርጡ አድርጓል።

ተከላካዮች


አዩብ በቀታ -አዲስ አበባ ከተማ

በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ቡድኑን በውሰት ከተቀላቀለ በኋላ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች በቋሚነት የተሰለፈው አዩብ ቡድኑ ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋራ ያሳየው ብቃት ልዩ ነበር። ከወትሮ ለየት ባለ መልኩ ከፍ ባለ ፍላጎት ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ጫና ለማሳደር የጣሩትን የአዳማ አጥቂዎች በመቆጣጠር እና ግቡን ተጋላጭ ባለማድረግ የተዋጣለት ጊዜ አሳልፏል።

በርናንድ ኦቼንግ – አርባምንጭ ከተማ

አዞዎቹ በዚህ ሳምንት ሽንፈት ያስተናግዱ እንጂ ከቆይታ በኋላ ወደ ቀዳሚ አሰላለፍ የመጣው ኦቼንግ ጥሩ ብቃት አሳይቷል። ተጫዋቹ ፋሲሎች በፈጣን ሽግግር ይሰነዝሩ የነበሩትን ጥቃት ከማቋረጥ ባለፈ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ላይ ንቁ ሆኖ ሲታይ የኦኪኪ አፎላቢን እንቅስቃሴን በመገደቡም በኩል የተሳካ ጊዜን ማሳለፍ ችሎ ነበር።

ቴዎድሮስ ሀሙ – አዲስ አበባ ከተማ

የአዩብ አጣማሪ በመሆን የተጫወተው ቴዎድሮስም የምርጥ ቡድናችን አካል ሆኗል። በሁለተኛው ዙር ራሱን እያጎለበተ ወሳኝ ተጫዋች የሆነው ቴዎድሮስ በዐየር እና መሬት የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች አሸናፊ በመሆን ለአዳማ አጥቂዎች አልቀመስ ብሎ ነበር። ከኳስ ውጪ በጥሩ ጥሩ ሸርተቴዎች ግቡን ካለማጋለጡ በተጨማሪም በኳስ ምስረታ ወቅት ምቾት ተሰምቶት ዕድገት ያላቸው ኳሶችን ሲያሳልጥ ይታያል።

አማካዮች


ብርሃኑ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

በሳምንቱ በርካታ ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ ጎልቶ የወጣው ተጫዋች የመስመር ተመላላሹ ብርሃኑ በቀለ ነው። ከራሱ ሳጥን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ሳይደክም በመሮጥ ወሳኝ ቅፅበቶች ላይ የሚገኘው ተጫዋቹ በቁጥር በዛ ያለውን የሀዋሳን ተከላካይ በመዘርዘር የተዋጣለት ጊዜ አሳልፏል። በመከላከሉም ለተጋጣሚ ተጫዋቾች የመጫወቻ ሜዳን በቀላሉ ላለመፍቀድ ጥሯል።

ጋቶች ፓኖም – ቅዱስ ጊዮርጊስ

መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከበድ ያለ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል በተጠበቀበት የሲዳማ ቡናው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር አድርጎ ሲያሸንፍ እጅግ ወሳኝ የሆነችው ግብ የተገኘችው ከጋቶች ፓኖም ነበር። በቡድኑ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ራሱን ያደላደለው ተጫዋቹ ከጎሏ ባሻገር ለተከላካይ መስመሩ ቡድኑ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ሲገደድ ጭምር ጥሩ ሽፋን በመስጠት እና ማጥቃትን በማስጀመሩም ረገድ ጥሩ የጨዋታ ቀንን አሳልፏል።

አበባየሁ ዮሐንስ – ሀዲያ ሆሳዕና

ከሀዲያ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ የገባው ሌላኛው ተጫዋች አበባየሁ ዮሐንስ ነው። አይደክሜው ተጫዋች የመጨረሻ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን ከሚሰለፍበት አማካይ መስመር በማመቻቸት ቡድኑን እያገለገለ ይገኛል። የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ አሲስቱን ከቆመ ኳስ ያቀበለው አበባየሁ ለሁለተኛው የፍቅረየሱስ ጎል አይነተኛ ሚና በረጅም ኳሱ ተጫውቷል። ከኳስ ውጪም በመታተር የሀዋሳን ሽግግር ለማምከን ተንቀሳቅሷል።

ጋዲሳ መብራቴ – ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ከወልቂጤ ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ በመስመር ተመላላሽነት ጨዋታውን የጀመረ ሲሆን በሁለተኛ አጋማሽን ደግሞ በመስመር አማካይነት ጨዋታውን አድርጓል ፤ ታድያ በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ በጠንካራ ሰራተኝነቱ የማይታወቀው ተጫዋቹ ከማጥቃት ባለፈ ለመከላከል ያሳየው ጥረት ጥሩ የሚባል ነበር። ከዚህ ባለፈው ለቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ ላይ የነበረው ተሳትፎ መልካም የሚባል ነበር።

ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን – ሀዲያ ሆሳዕና

የሀዲያው አማካይ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከወትሮው በተለየ ወደ ፊት በተጠጋ ሚና በጀመረበት ጨዋታ ቡድኑ ሀዋሳ ከተማን ሲረታ ከሳጥን ጠርዝ ግሩም ግብ ከማስቆጠር ባለፈ የዘገዩ ሩጫዎችን ወደ ሳጥን በማድረግ ሀዋሳ ላይ አደጋ ሲደቅን አስተውለናል። በነፃ ሚናም የሀዋሳን ተከላካዮች ሲረብሽ የነበረበት መንገድ በቡድናችን ቦታ እንዲያገኝ አድርጓል።

በዛብህ መለዮ – ፋሲል ከነማ

ከአምናው አንፃር ደከም ያለ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ፋሲል ከነማ ግብ ማስቆጠር በሚቸገርባቸው ጨዋታዎች ላይ ካልታሰበ ምንጭ የተነሱ ኳሶች ከመረብ ሲያርፉ መነሻቸው በዛብህ ሆኖ ይታያል። ተጫዋቹ አሁንም ለቡድኑ ቁልፍ ሰው መሆኑን ባሳየበት ሳምንት ያስቆጠራት ጎል ፋሲል ከነማ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ካለው አርባምንጭ ጋር ገጥሞ በቀላሉ ግብ ለማግኘት ቢቸገርም ከፉክክሩ ያለው ርቀት ይበልጥ እንዳይሰፋ እጅግ ወሳኝ ነበረች።

አጥቂ


ሀብታሙ ታደሰ – ሀዲያ ሆሳዕና

የነብሮቹን የፊት መስመር ተመራጭነት እያጣ የነበረው ሀብታሙ ዳግም በቦታው ልዩነት ፈጣሪ እንደሆነ ያሳየበትን ብቃት ሊያውም በ67 ደቂቃዎች የሜዳ ላይ ቆይታ ማሳየት ችሏል። በዚህም ቡድኑ የፊት መስመር አስፈሪነቱን መልሶ እንዲያገኝ ባደረገው እንቅስቃሴው ቅብብሎችን በመከወን እና የመጨረሻ ውሳኔን በመወሰን ወሳኝ ሚና ሲወጣ የመክፈቻውን ጎል አስቆጥሮ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ከመረብ ያገናኘውን ሁለተኛ ጎልም ማመቻቸት ችሏል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና

ሦስት ቡድኖች ብቻ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት በቻሉነት የሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አንዱ ባለድል የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና ሆኗል። ወጣቱ የቡድኑ አሰልጣኝ ደከም ብሎ የነበረውን የቡድኑን የውድድር ዘመን አካሄድ በማስተካከል በሀዋሳ ከተማ ላይ ተከታታይ የሆነለትን ድል ሲያስመዘግብ በጨዋታ ዕቅዱ በተጋጣሚው ላይ ተፈላጊውን የበላይነት በመውሰድ በሁለት ግቦች ልዩነት ያሸነፈ ብቸኛው የሳምንቱ አሰልጣኝ ሆኗል።

ተጠባባቂዎች

ዳንኤል ተሾመ – አዲስ አበባ ከተማ

መልካሙ ቦጋለ – ወላይታ ድቻ

እንየው ካሣሁን – ድሬዳዋ ከተማ

ቻርለስ ሪባኑ – አዲስ አበባ ከተማ

የአብስራ ተስፋዬ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቢኒያም በላይ – መከላከያ

አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ሰበታ ከተማ

ሄኖክ አየለ – ድሬዳዋ ከተማ