ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ወላይታ ድቻ

የሊጉ የአዳማ ቆይታ ማሳረጊያ በሆነው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

የ21ኛው ሳምንት ተገባዶ ውድድሩ ወደ ባህር ዳር ከተማ ከማቅናቱ በፊት በዕኩል 34 ነጥቦች ሁለተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ቡድኖች ያገናኛል። ይህ ጨዋታ ተጋጣሚዎቹ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ከዚህ በኋላ የሚኖራቸውን ደረጃ ብቻ ሳይሆን መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀድሞ ጨዋታውን ከማሸነፉ አንፃር የሊጉን ዋንጫ አቅጣጫ ጭምር ሊጠቁም የሚችል ነው። ሁለቱ ቡድኖች ይህንን ጨዋታ አሸንፈው ከመሪው ጋር ያላቸውን የ13 ነጥብ ልዩነት ማጥበብ ካልቻሉ ከዚህ በኋላ ባለው ጊዜ ትኩረታቸው የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ የሚያስገኘው ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንዲሆን ሊገደዱ ይችላሉ።

ከወቅታዊ አቋም አንፃር ስንመለከተው ወላይታ ድቻ ከነገ ተጋጣሚው አኳያ ሁለተኛ ግምት እንዲሰጠው ያስገድዳል። በአጠቃላይ የቡድኑ የአዳማ ከተማ ከተማ ቆይታው በላይኛው የሰንጠረዡ ክፍል ያለውን የተፎካካሪነት አቅም ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነበር። ከአምስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፈው ወላይታ ድቻ በጥሩ ጎኑ ሊነሳለት የሚችለው ከአንዴ በላይ ሽንፈት ያለማስተናገዱ ጉዳይ ነው። በእነዚህ ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያላቸው የጦና ንቦቹ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎችም ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻሉም። በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች በሀዋሳ እና በድሬዳዋ የነበራቸውን ወጣ ገባ አቋም በወጥነት ማስተካከል ባይችሉም በተሻለ ሁኔታ ነጥብ መሰብሰብ ሆኖላቸውል። በመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎቻቸው ሰባት ነጥቦችን ማሳካታቸውም ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ሲወሰድ በሦስቱ ጨዋታዎች ብቻ አምስት ግቦችን አስመዝግበዋል።

በነገው ፍልሚያ ሁለቱም ተጋጣሚዎች በመጀመሪያ ዕቅድነት ሲጠቀሙባቸው የሚታዩትን አቀራረቦች ይዘው እንደሚገቡ ይጠበቃል። ባሳለፍነው ሳምንት ከነገው ተጋጣሚያቸው ጋር ተመሳሳይ ከሆነው አርባምንጭ ከተማ ጋር ተገናኘተው 1-0 ማሸነፍ ችለው የነበሩት ፋሲል ከነማዎች የግብ ክልሉን በቀላሉ የማይከፍተው ተጋጣሚን ማስከፈት ቀላል አልሆነላቸውም ነበር። ይህንን ተከትሎ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የኳስ ምስረታ ሂደታቸውን ይበልጥ አሻሽለው መምጣት እንዳለባቸው አፅዕኖት ሰጥተው መናገራቸው በተለየም ለነገው ጨዋታ የቡድኑ ዋነኛ የዝግጅት መነሻ እንደሆነ መገመት ይቻላል።

በሁለተኛው ዙር የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የሚታይባቸው ወላይታ ድቻዎች የኳስ ቁጥጥርን ምርጫቸው ለሚያደርጉ ቡድኖች ፈታኝ መሆናቸው ግልፅ ነው። ለዚህም ተመሳሳይ ምርጫ ካላቸው ሰበታ ከተማ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማ ጋር ባደረጓቸው ሦስት የመጨረሻ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዳቸውን መመልከት ይበቃል። ሆኖም ቡድኑ ኳሶችን አቋርጦ የመጨረሻ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ያለበት ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ አሳሳቢ መሆኑን ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም መስማታችን አይዘነጋም። ከዚህ በተጨማሪም ግን እንድሪስ ሰዒድን በቅጣት አጥቶ የነበረው ወላይታ ድቻ ፈጣን ሽግግርን የሚመጥኑ የመጨረሻ ቅብብሎችን ወደ ሳጥን ውስጥ በማድረስም ረገድ ተቸግሮ ታይቷል።

የተናጠል የተጫዋቾችን አበርክቶት ስንመለከት የፋሲል ከነማው በዛብህ መለዮን አለማንሳት ይከብዳል። ጥሩ የመከላከይል አቅም ያላቸው ቡድኖች አጥቂዎችን መገደብ ቢችሉም የተሻለ የእንቅስቃሴ ነፃነት ያላቸው እንደበዛብህ ያሉ አማካዮች ዘግይተው ወደ ሳጥን ሲደርሱ ከዕይታ ውጪ በመሆን የሚያደርሱት ጉዳት ከፍ ያለ ዋጋ አለው። ከዚህ አንፃር በስድስት ጎሎች ከኦኪኪ አፎላቢ ዕኩል የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃ ላይ የደረሰው በዛበህ በነገው ጨዋታም ተጠባቂ ይሆናል። ፋሲል ሽመክት ጉግሳ እና አምሳሉ ጥላሁንን የማያገኝ በመሆኑ የማጥቃት ጉልበቱ በሚቀንስበት በዚህ ጨዋታ የበዛብህ አጨራረስ እና የሱራፌል ዳኛቸው መካከለኛ ርቀት ያላቸው ኳሶች እንዲሁም የቆሙ ኳሶች በእጅጉ ያስፈልጉታል።

ወላይታ ድቻ በበኩሉ ከፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ከሰሞኑ የተሻለ ብቃትን ማየት ይፈልጋል። ከፋሲል ከነማ የተከላካይ መስመር ጀርባ ሰፊ ክፍተት እንደሚኖር በሚጠበቅበት በዚህ ጨዋታ በተለይም ከእንድሪስ ሰዒድ መነሻቸውን ከሚያደርጉ ኳሶች አንፃር ምንይሉ ወንድሙ እና ቃልኪዳን ዘላለም ቅልጥፍና እንዲሁም መናበብ አስፈላጊ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ከሰሞኑ የተቀዛቀዘው የቡድኑ የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም በተለይም ከያሬድ ዳዊት በሚነሱ ጊዜያቸውን የጠበቁ ክሮሶች እና በእነአንተነህ ጉግሳ የግንባር ኳስ አጠቃቀም አንዳች ልዩነት መፍጠር አስፈላጊያቸው ይሆናል።

ፋሲል ከነማ አሁንም ሙጂብ ቃሲምን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን ሽመክት ጉግሳ እና አምሳሉ ጥላሁንም በአምስተኛ ቢጫ ካርድ ምክንያት ጨዋታው ያልፋቸዋል። እንድሪስ ሰዒድን ከቅጣት መልስ የሚያገኙት ወላይታ ድቻዎች ስንታየሁ መንግሥቱን ብቻ በጉዳት ያጣሉ።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ለ9 ጊዜያት ተገናኝተዋል። ፋሲል ከነማ 5 ጊዜ ድል በማግኘት ቀዳሚ ሲሆን ወላይታ ድቻ ደግሞ 3 አሸንፏል ፤ በዚህ ዓመት በተደረገው ጨዋታቸው የመጀመሪያ የአቻ ውጤት አስመዝግበዋል። በእስካሁኑ ግንኙነታቸው በአጠቃላይ 20 ጎሎች ሲቆጠሩ ዐፄዎቹ 11 የጦና ንቦቹ ደግሞ 9 አስመዝግበዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)

ሚኬል ሳማኪ

ዓለምብርሃን ይግዛው – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – ሳሙኤል ዮሐንስ

ይሁን እንዳሻው

ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው – በረከት ደስታ

ኦኪኪ አፎላቢ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ፅዮን መርዕድ

በረከት ወልደዮሐንስ – አንተነህ ጉግሳ – መልካሙ ቦጋለ – አናጋው ባደግ

ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – እንድሪስ ሰዒድ

ያሬድ ዳዊት – ምንይሉ ወንድሙ – ቃልኪዳን ዘላለም