የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በሁለተኛው ፅሁፋችን በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች ተካተውበታል።

👉 የሚገባውን ያህል ያልተደነቀው አላዛር ማርቆስ

ወጣቱ ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ ላለመውረድ እየታገለ በሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ውስጥ እጅግ አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ ቀጥሏል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም ቡድኑ ባህር ዳር ከተማን 2-0 በረታበት ጨዋታ ዳግም ድንቅነቱን ያሳየበት ነበር።

ከስድስት የሚልቁ ጥራታቸው የላቁ ሙከራዎችን ያዳነው ግብ ጠባቂው በተለይ ደግሞ በ58ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ከተነሳ የባህር ዳር ማጥቃት መሳይ አገኘሁ ፣ ሄኖክ ኢሳያስ እና ተመስገን ደረሰ አከታትለው ያደረጓቸውን ሦስት ሙከራዎች ያዳነበት መንገድ እጅግ አስደናቂ ነበር። ምንም እንኳን ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ስላሸነፈ አነሳን እንጂ ቡድኑ በተሸነፈባቸውም ሆነ ነጥብ በተጋራባቸው ጨዋታዎች የአላዛር ማርቆስ በቋሚዎቹ መካከል ያደርግ የነበረው ጥረት ግሩም የሚባል ነው።

በሊጉ በአሁኑ ሰዓት ስለሚገኙ የተሻሉ ግብ ጠባቂዎች ስናስብ በቅድሚያ ወደ አዕምሯችን የሚመጡተ በተነፃፃሪነት የተሻለ ግባቸውን ሳያስደፍሩ የውጡ (Clean Sheet) ያስመዘገቡ ግብ ጠባቂዎች ናቸው። በዚህም ሂደት ለአብነትም የቅዱስ ጊዮርጊሱን ግብ ጠባቂ ቻርልስ ሉኩዋጎን ማንሳት እንችላለን። ይህ ግብ ጠባቂ በጨዋታዎች በአማካይ የሚሞከሩበት ሙከራዎች ቁጥር አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ግብ የማስተናገድ ዕድሎም ጠባብ እንደሆነ ግን መረዳት ተገቢ ነው። በተጨማሪም ግብን ሳይስደፍሩ መውጣት ከግብ ጠባቂው ባለፈ የቡድኑን የመከላከል አወቃቀር (በተለይም የተከላካይ መስመሩን) ጥንካሬ ጋር በቀጥታ የሚተሳሰር ነው።

ነገር ግን እንደ ጅማ አባ ጅፋር ባሉ ለተጋጣሚ ቡድን በቀላሉ ዕድሎችን በሚሰጡ ቡድኖች የሚጫወቱ ግብ ጠባቂዎች በጨዋታ የሚጋፈጧቸው ሙከራዎች በመጠንም (Volume) ሆነ በጥራት (Quality) የላቁ እንደመሆናቸው መጠን ግቦችን የማስተናገድ ዕድላቸው ሊጨምር ቢችልም በዚህ ውስጥም ግን ብቃታቸውን በደንብ መመርመር ይገባል።

አላዛር በባህር ዳሩ ጨዋታ ብቻ ስድስት ጥራታቸውን የጠበቁ መከራዎችን ማዳን ሲችል በቀደሙት ጨዋታዎችም እንዲሁ በርካታ ሙከራዎችን ሲያድን ተመልክተናል። ይህም ምናልባት የራሱ የሆነ ውስንነቶች ቢኖሩትም በማዳን ንፃሬ ከተመለከትነው በጣም የተሻለ የሚባል ነው። ወጣቱ ግብ ጠባቂ በተለይ የእግር አጠቃቀሙን ጨምሮ ሌሎች ሊያሻሽላቸው የሚገቡ ነገሮች ቢኖሩም ላሁኑ ግን በሊጉ ካሉ ድንቅ የግብ ዘቦች ተርታ የሚያስመድበውን ብቃት እያሳየ ይገኛል።

👉 አሁንም በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘው መስዑድ መሀመድ

መስዑድ መሀመድ አሁንም በሊጉ በወጥ ብቃት እየተጫወተ ይገኛል። ጅማ አባ ጅፋር ባህር ዳርን ሲረታ እንዲሁ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች እንደሆነ ዳግም አስመስክሯል።

በጨዋታው ለወትሮው ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ለተቸገረው ጅማ አባ ጅፋር ጨዋታውን እንዲያሸንፍ የረዱት ሁለት ግቦች ሲቆጠሩ ኳሶቹን አመቻችቶ በማቀበል የአንበሳው ድርሻ ተወጥቷል።

ከቆሙ ኳሶች መነሻቸውን ባደረጉት ሁለት ግቦች ላይ አስጨናቂ ፀጋዬ ላስቆጠራት ኳስ ጊዜውን የጠበቀ ኳስ በማድረስ እንዲሁም ደግሞ ሱራፌል ዐወል ያስቆጠራት ሁለተኛ ግብ ስትቆጠር የአዕምሮ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የባህር ዳር ተጫዋቾች በተዘናጉበት ቅፅበት ያስጀመራት የቅጣት ምት ኳስ ቡድኑን ባለ ድል አድርገዋል።

በሊጉ እስካሁን በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ጅማን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ የገባው መስዑድ መሀመድ ከጨዋታ ጨዋታ በተመሳሳይ የብቃት ደረጃ ጅማን ለማገልገል ጥረት ሲያደርግ እያስተዋልን እንገኛለን። ከዚህም ባለፈ ወጣት ተጫዋቾች የበዙበትን ስብስብ ለረጅም ዓመታት የዘለቀው ልምዱን በመጠቀም በምሳሌ ለመምራት የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው።

👉 ከመስመር የሚነሳው ይገዙ ቦጋለ

በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ሳልሀዲን ሰዒድ ወደ ሲዳማ ቡና መምጣቱን ተከትሎ ከፊት አጥቂነት ይልቅ ወደ መስመር እንዲወጣ በመገደዱ ይቸገራል የተባለው ይገዙ ቦጋለ ጥሩ እምርታን እያሳየ ይገኛል።

ተጫዋቹ በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ቢያመልጠውም ዳግም ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት በመጣበት የአዳማ ከተማው ጨዋታ ከግራ መስመር እየተነሳ ያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ አስደናቂ ነበር። ተጫዋቹ ከመስመር እየተነሳ ኳሶችን እየነዳ ወደ ውስጥ ሰብሮ ለመግባት እንዲሁም በተደጋጋሚ ወደ ውስጥ ተስቦ በመግባት ከቡድኑ አጋሮቹ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል አደጋ ለመፍጠር ያደርገው የነበረው ጥረት የሚደነቅ ነው።

ከዚህም ባለፈ በመከላከሉ ወቅት እንቅስቃሴዎችን በማቋረጥ እንዲሁም ወደ ኋላ በመሄድ የመከላከሉን ሂደት በማገዝ ረገድ ያሳየው ጥረት ጥሩ የሚባል ነበር።
ከእስማኤል ኦሮ አጎሮ እና ሪችሞንድ ኦዶንጎ ቀጥሎ በዘጠኝ ግቦች በሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ ከጌታነህ ከበደ ጋር በጣምራ በሁለተኝነት ላይ የሚገኘው ይገዙ በተጠናቀቀውም የውድድር ዘመን በተለይ በሁለተኛው ዙር የኦኪኪ አፎላቢን መምጣት ተከትሎ ወደ መስመር ሲወጣ የተመለከትነው ሲሆን ከሳጥን አጥቂነት ባለፈ የመሰል ክህሎቶች ባለቤት መሆኑ ተጫዋቹ ወደ ፊት ከዚህ በተሻለ የተሟላ አጥቂ የመሆን አቅም እንዳለው ማረጋገጫ እየሰጠ ይገኛል።

👉 ጌታነህ ከበደ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክር ውስጥ

በጨዋታ ሳምንቱ ወልቂጤ ከተማ ከተከታታይ ነጥብ መጣሎች በኋላ ወደ ድል ሲመለስ ጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል።

የወልቂጤ ከተማው አምበል ጌታነህ ከበደ በጨዋታው ከፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም ሁለተኛዋን ደግሞ በግሩም አጨራረስ በማስቆጠር በአጠቃላይ የውድድር ዘመኑ ያስቆጠረውን የግብ መጠን ወደ ዘጠኝ በማሳደግ ከሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች በአንድ ግብ አንሶ ለመቀመጥ ችሏል።

በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረው ጌታነህ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለወልቂጤ ከተማ በሁሉም ጨዋታ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን ከአንድ ጨዋታ በስተቀር በተቀሩት ሁሉም ጨዋታዎች ሙሉ ዘጠና ደቂቃዎችን በሜዳ ላይ ቆይቷል።

ዘጠኝ ግቦች እና ሁለት ለግብ የሆኑ ኳሶችን ማቀበል የቻለው የሁለት ጊዜ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ለከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በሚደረገው ፉክክር ከፍተኛ የሆነ የጨዋታ ደቂቃ እና ጎል ንፃሬ ያለው ሲሆን ተጫዋቹ በቀጣይ ይህን ለማሻሻል እና ፉክክሩን በበላይነት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 አህመድ ሁሴን ኳሱን ተቀብሏል

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሊጉ እየተለመደ የመጣው እና ሐት-ትሪክ ለሰሩ ተጫዋቾች የጨዋታ ኳስ የማበርከት ልምምድ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በተለየ መልክ ተመልክተነዋል።

በ18ኛ የጨዋታ ሳምንት ድራማዊ ክስተት በተሞላው ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ሲጋራ በጨዋታው ሐት-ትሪክ መስራት የቻለው አህመድ ሁሴን በጨዋታው ወቅት ባጋጠመው ጉዳት ወደ ሆስፒታል ማምራቱን ተከትሎ የጨዋታውን ኳስ መውሰድ ሳይችል ቆይቷል።

ታድያ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ አርባምንጭ ከተማ በቀድሞ ክለቡ ወልቂጤ ከተማ 3-0 ከተረታበት ጨዋታ መጀመር አስቀድሞ የጨዋታ ኳሱን ተረክቧል። ኳሷን ሐት-ትሪክ የሰራበትን ጨዋታ ከዳኙት ኤፍሬም ደበሌ እጅ ሳይሆን ከማኑሄ ወልደፃዲቅ የመውሰዱ ጉዳይ ሌላው ትኩረትን የሳበ አጋጣሚ ነበር።

👉 አማራጭ አጥቂ ያጣው ኢትዮጵያ ቡና

ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች አቡበከር ናስርን በጉዳት መነሻነት ለመጠቀም የተቸገረው ኢትዮጵያ ቡና በተከታታይ ጨዋታዎች እንዳለ ደባልቄን በምትኩ ቢጠቀምም የሚፈለገውን ግልጋሎት ያገኘ አይመስልም።

ቡድኑ በመከላከያ ያልተጠበቀ ሽንፈትን ባስተናገደበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ 65ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው እንዳለ ደባልቄን አስወጥተው በምትኩ የተከላካይ አማካዩን አብነት ደምሴ ያስገቡት አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በተቀሩት ደቂቃዎች በፊት አጥቂነት ሮቤል ተክለሚካኤልን ሲጠቀሙ አስተውለናል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከመሀል ሜዳ እየተነሳ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው እንዲሁም አምስት ግብ የሆኑ ኳሶችን መስጠት የቻለው ሮቤልን በአጥቂነት የመጠቀማቸው ጉዳይ ቡድኑ በተለይ በአጥቂ መስመር ላይ ያለበትን የአማራጭ እጥረት ችግር ከማሳየቱ ባለፈ አሰልጣኙ በእንዳለ ላይ ያላቸው ዕምነት እየተሟጠጠ መምጣቱን ማሳያም ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።

በመሆኑም የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ አቡበከር ናስርን የሚያጣው ቡና በቀጣዩ የውድድር ዘመን ህይወት ያለ አቡበከር ናስር ምን ሊመስል እንደሚችል ከወዲሁ በበቂ መልኩ እየተመለከተ እንደመገኘቱ ከወዲሁ የፊት መስመሩን ለማጠናከር ጠንካራ ምልመላ ማድረግ ይኖርበታል።

👉 የአማኑኤል ገ/ሚካኤል ጠቃሚነት

ግቦቹን በሚፈለገው ልክ አያስቆጥር እንጂ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ለቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም ቀላል የማይባል አበርክቶ እያደረገ ይገኛል።

ተጫዋቹ በተለይም ከኳስ ውጪ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለቡድኑ ወሳኝ ጥቅም እያስገኘ ይገኛል። ይህንንም በተለይ ቡድኑ ሀዋሳ ከተማን በረታበት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ላይ በጉልህ አስተውለናቸዋል።

አማኑኤል ለቡድኑ ሁለተኛ የነበረችውን ግብ ሲያስቆጥር የነበረው ሂደት ሰሞነኛውን የአማኑኤል ገ/ሚካኤል ከኳስ ውጪ ያለውን መታተር በሚገባ የሚያሳይ ነበር። ከራሱ የግብ ክልል እየነዳ የሄደውን ኳስ በተሻለ አቋቋም ላይ ለነበረው ቸርነት ጉግሳ ካቀበለ በኋላ ፍጥነቱን ሳይቀንስ የቡድን አጋሩን ለመርዳት መሮጡን የቀጠለው አማኑኤል በቃሉ ገነነ ቸርነትን ተንሸራቶ ያቋረጠበትን ኳስ ደርሶ ማስቆጠር ችሏል።

በተመሳሳይ ሦስተኛዋ ግብ ስትቆጠርም እንዲሁ ለቡልቻ ሹራ የማቀበያ አማራጭ ለመፍጠር ያደረገው የአግድመት ሩጫ እና ኳሱን በመጀመሪያ ንኪኪ ያቀበለበት ሂደት ግሩም ነበር። በውድድር ዘመኑ ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ ሦስት ለግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል የቻለው አማኑኤል በጨዋታው የልጅ አባት በሆነ ማግስት ግብ ማስቆጠሩ ጨዋታውን በግሉ የተለየ አድርጎለታል።

በ2011 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው አማኑኤል በግብ ማስቆጠሩ ረገድ በቀደመው ደረጃ ተደጋጋሚ ግቦችን በማስመዝገብ ረገድ አሁንም ብዙ ስራዎች የሚጠብቁት ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በ21 ጨዋታዎች ካስቆጠረው የግብ ብዛት (2) የተሻለ ግብ ከወዲሁ ማስቆጠር ችሏል።

👉 የጊት ጋትኩት ጉዳት…

ቀስ በቀስ እየተሻሸለ በመጣው የሲዳማ ቡና የውድድር ዘመን ጉዞ ውስጥ በተለይ በመከላከሉ ረገድ የቡድኑ አይነኬ ተጫዋች እየሆነ የመጣው ወጣቱ ጊት ጋትኩት ከፍ ያለ ድርሻን እየተወጣ ይገኛል።

በፋሲል ከነማ አሰቃቂ ሽንፈት እስካስተናገዱበት የ7ኛ የጨዋታ ሳምንት ድረስ በሰባት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦችን ያስተናገደው ቡድኑ በቀጣይ ባደረጋቸው አስራ አራት ጨዋታዎች ያስተናገደው የግብ መጠን ሰባት መሆኑ ምን ያህል በመከላከሉ እንደተሻሻለ ማሳያ ነው።

ከዚህ መሻሻል በስተጀርባ የተለያዩ ምክንያቶችን መጥቀስ ቢቻልም በተለይ ደግሞ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በተደጋጋሚ ጉዳት ቡድኑን ማገልገል ተቸግሮ የነበረው ወጣቱ ጊት ጋትኩት አሁን ላይ በተሻለ የጤንነት ሁኔታ ቡድኑን ማገልጋል ላይ መገኘቱ ተጠቃሽ ነው።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በ16 ጨዋታዎች በድምሩ ለ1298 ያህል ደቂቃዎች በሲዳማ ቡና መለያ ተሰልፎ የተጫወተው ጊት ቀስ በቀስ በሚቆጠሩበት ግቦች ቁጥር ሆነ በመከላከል ጥራት እየጎለበተ በመጣው የሲዳማ ቡና መከላከል ውስጥ እጅግ ቁልፍ ሚናን እየተወጣ ይገኛል።

በተለይም ደግሞ ከያኩቡ መሀመድ ጋር የፈጠሩት ግሩም ጥምረት ለቡድኑ መከላከል አስተማማኝ ደጀን የሆነ ሲሆን ከዚህ ባለፈ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ያለው የበላይነት የሚደንቅ ነው። ሜዳ ላይ ያለውን ለመስጠት የማይሰስተው ጊት በተለይ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ለቡድኑ ሲል ራሱን ለአደጋ በሚዳርግ መንገድ ሁሉ ቡድኑን ለማገዝ ይጥራል። የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በማቋረጥ ወደር የማይገኝለት ተጫዋቹ በዚህ ሂደት ቡድኑ ከአዳማ ከተማ ጋር አንድ አቻ በተለያየበት ሂደት ኳስ ለማስጣል ባደረገው ጥረት ባጋጠመው ጉዳት ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል።

ከወቅታዊ ብቃቱ አንፃርም በ72ኛው ደቂቃ በተስፋዬ በቀለ ተቀይሮ የወጣው ተጫዋቹ በፍጥነት ወደ ሜዳ መመለስን ሲዳማ ቡናዎች አጥብቀው ይጠባበቃሉ ።