የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 1-1 አዲስ አበባ ከተማ

ነጥብ በመጋራት ከተጠናቀቀው የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“በራሳችን የእኛ ቡድን ጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክሯል፡፡ ነገር ግን የእኛ ተጋጣሚ ከኳስ ጋርም ከኳስ ውጪም ኔጌቲቭ እግር ኳስን ነበር ስመለከት የነበረው፡፡ ይሄ አለም የሚመለከተው እግር ኳስ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ኳስ መጫወት ከባድ ነው፡፡

የጎል ዕድል አለመፍጠራቸው

“አንደኛው ሜዳው የመጀመሪያችን ነው እዚህ ሜዳ ላይ ስንጫወት፡፡ ሜዳው እንደምታውቀው በጣም ትልቅ ነው፡፡ ከራሳችን ሜዳ ተነስተን ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ላይ ለመድረስ ረጅም ርቀት ነው፡፡ ስለዚህ እስክንላመድ ድረስ የተወሰኑ ጨዋታዎችን ልንቸገር እንችላለን፡፡

በራሱ ላይ ስላስቆጠረው ዋሀብ አዳምስ

“ዋሀብ አዳምስ በጣም ጠንካራ ተከላካያችን ነው፡፡ እዚህ ድረስ ሰንመጣ ብዙ ነገር ያደረገልን ተከላካይ ነው ፤ በጣም አዝኖ ነበር፡፡ ቡድኑን በጣም ይወደዋል፡፡ ያንን ስህተት መስራቱ በጣም እንዲፀፅተው አድርጓል፡፡ ሜዳ ላይ ተረብሾ ነበር ፤ ያንን ነው ሳፅናናው የነበረው፡፡”

የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ መሠረት ወልደማርያም – አዲስ አበባ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“ጥሩ ነው፡፡ ለማሸነፍ ነው እኛ የገባነው አጥቅቶ ለመጫወት ነበር የገባነው፡፡ ልጆቻችን ውስጥ ያለው ጉጉት ፣ አሸንፎ የመውጣት ጉጉት ጎል ባገቡ ቁጥር ወደ ኋላ የመሆን ነገር ባለቀ ሰዓት ጎል ገብቶብናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አቀያየር ላይ የኮንሰንትሬሽን ችግር ነው፡፡ ኒር ፖስት ላይ የነበረው ልጅ እዛ ቦታ ሌላ ተጫዋች እስኪተካ ዳኞች ሰዓት የገደልን ስለመሰላቸው ያንን ክፍተት እነሱ ተጠቀሙበት፡፡

የወልቂጤው አሰልጣኝ በአድስ አበባ አጨዋወት ደስተኛ ስላለመሆናቸው

“እኔ እንኳን የተቃራኒ ቡድን ስትራቴጂ በእኛ ስህተት ላይ የተመሠረተ እንጂ የተለየ ነው ብዬ አላስብም፡፡ እኛ አንድ እና አንድ አሸንፎ ለመውጣት ነው የገባነው አንድ ጎል ሁሌ ውጤት ስለማያስጠብቅ ዕድለኞች ናቸው ማለት እችላለሁ እነሱ፡፡

ከአሰልጣኝ ፓውሎስ ጋር ስለ ነበራቸው ግንኙነት

“እኔ ከዚህ በፊት በነበርኩበት የእግር ኳስ ህይወት በግብ ጠባቂነት ስላሳለፍኩ የመምራቱ ሚና ብዙም ከባድ አይደለም ግን እንደ አጋጣሚ ጥሩ ግንኙነት ፣ መግባባትም ላይ ነበርን፡፡ በይበልጥ ልጆቹንም እኔ ስለማውቅ ብዙ ኃላፊነቱን ለእኔ ሰጥቶ ነበር፡፡ ስለዚህ እየተመካከርን ስለነበር ጥሩ ነበር እንጂ የተለየ ነገር የለውም፡፡”