ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

ትናንት በተጠናቀቀው የጨዋታ ሳምንት ላይ የታዩ ክለብ ነክ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አንስተናል።

👉 ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያቆም አልተገኘም

22ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የሊግ ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነጥባቸውን 50 አድርሰው ከተከታዮቻቸው በ10 ነጥብ ርቀው ሊጉን መምራታቸውን ቀጥለዋል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ከአዳማ ከተማ ከፍተኛ ፈተና ቢገጥማቸውም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከነዓን ማርክነህ ያስቆጠራትን ግብ አስጠብቀው በመውጣት መሪነታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ እንኳን በ20ኛ ሳምንት ከሲዳማ ቡና እንዲሁም በዚህኛው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ብርቱ ፉክክር የገጠመው ቡድኑ ጨዋታዎችን አሸንፎ የሚወጣበት መንገድ አላጣም። በሁለቱም ጨዋታዎች ከቆሙ ኳሶች መነሻቸውን ባደረጉ ኳሶች በተገኙ ግቦች አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ይህም አሸናፊ ቡድኖች በተቸገሩበት ጨዋታም ቢሆን አሸንፈው እንደሚወጡ ቡድኑ ዳግም ያስመሰከረበት አጋጣሚ ሲሆን ከዚህ ባለፈ ብዙዎች እንደሚስማሙበትም ሌላኛው የአሸናፊ ቡድን ባህሪ የሆነው በመከላከል እና በማጥቃት ሁለቱን ሽግግሮች ጨምሮ እንዲሁም በቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ከሌሎቹ ተፎካካሪዎቻቸው ልቀው እንደሚገኙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቁጥሮች ይናገራሉ።

ሌላኛው መነሳት የሚገባው ከሁለተኛው ዙር አንስቶ ያለ ዋነኛ ግብ አስቆጣሪያቸው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ እየተጫወቱ የሚገኝ ቢሆንም ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ደግሞ ሌላኛው በማጥቃቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነው አቤል ያለውም እንዲሁ በጉዳት ባይኖርም ጊዮርጊስ በተለያየ መንገድ እና ግለሰቦች ግቦችን እያስቆጠረ መቀጠሉ ነው። ይህም የቡድኑን የስብስብ ጥራት እና ጥልቀት ያስመለከተ ነጥብ ነው።

በቀጣዮቹ ሦስት የጨዋታ ሳምንታት በሰንጠረዡ አናት ከሚገኙት ወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ እንዲሁም በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘውን እና በመሻሻሎች ውስጥ የሚገኘውን ጅማ አባ ጅፋርን የሚገጥሙባቸውን ቁልፍ ጨዋታዎች የሚጠብቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች እነዚህን ፈተናዎች የሚወጡ ከሆነ አሸናፊነታቸውን ለማረጋገጥ ብዙ ጨዋታዎችን የሚጠብቁ አይመስልም።

👉 ፋሲል ከነማ ተፎካካሪነቱን አስቀጥሏል

ቅዱስ ጊዮርጊስን እየተከተሉ የነበሩ ቡድኖች በወሳኝ ሰዓት ነጥብ ለመያዝ ሲቸገሩ ፋሲል ከነማ ግን በፉክክሩ ለመዝለቅ እየጣረ ይገኛል።

በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በሰንጠረዡ አናት እየተፎካከሩ በሚገኙት ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ላይ እጅግ ትልቅ ዋጋ ያላቸውን ስድስት ነጥቦችን ማሳካት የቻለው ፋሲል አሁንም ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ10 ነጥብ ዝቅ ብሎ ይገኛል።

ሲዳማ ቡናን በረቱበት ጨዋታ ከፍ ባለ የደጋፊ ቁጥር ታጅበው ጨዋታቸውን ያደረጉት ፋሲሎች በቀጣይ ጨዋታዎች በባህር ዳር ከፍተኛ ቁጥር ባለው ደጋፊያቸው እየታገዙ በፉክክሩ ለመዝለቅ የቻላቸውን እንደሚጥሩ ፍንጭ ሰጥተዋል። በሲዳማ ጨዋታ በተለይ ከሰሞኑ እየተመለከትነው እንደምንገኘው ቡድኑ በክፍት ጨዋታ አሁንም በጥልቀት የሚከላከሉ ቡድኖችን ለማስከፈት እንደሚቸገር ያስተዋልን ሲሆን በዚህ ሂደት ብቸኛ አማራጫቸው የመስመር ተጫዋቾቻቸው እንዲነጠሉ በማድረግ ከበረከት እና ሽመክት በሚነሱ እና ወደ ሳጥን በሚጣሉ ኳሶች ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል።

ይህም በሊጉ ጥራታቸው የላቁ የአጥቂ አማካዮችን ለያዘው ፋሲል በክፍት ጨዋታ እየፈጠራቸው የሚገኙት ዕድሎች መጠን በጣም ዝቅተኛ መሆኑ በቀጣይ ቡድኑ ሊያሻሽለው የሚገባው መሰረታዊው ጉዳይ ሲሆን ከዚህ ባለፈ ግን ሰሞነኛ መነቃቃቱ ተስፋ የሚሰጥ ነው።

በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት በጉጉት በሚጠበቀው ጨዋታ ከባህር ዳር ጋር የሚገጥመው ፋሲል የሊጉን ዋንጫ በቀላሉ ለፈረሰኞቹ ላለመስጠት ጥረት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 የተለወጠው ጅማ አባ ጅፋር

የውድድር ዘመኑን 19ኛ ነጥባቸውን ያስመዘገቡት ጅማ አባ ጅፋሮች በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው ላይ ግለት እየጨመሩ ይገኛል። በአሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ እየተመራ መነቃቃት ላይ የሚገኘው ጅማ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ አርባምንጭ ከተማን በመርታት በውድድር ዘመኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሁለተኛ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ጅማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ግን በአርባምንጭ ከተማዎች ብልጫ ተወስዶባቸው የነበረ ቢሆንም ባልተለመደ መልኩ በአጋማሹ ወሳኝዋን ግብ አስቆጥረው አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ለወትሮው ተጋጣሚ ላይ ብልጫ ለመውሰድ የሚገዳደሩት እና በመጨረሻም ለነበራቸው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የሚናገር ውጤት መያዝ ተቸግረው የቆዩት ጅማዎች ተከታታይ ድል ባስመዘገቡባቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች በተጋጣሚ ብልጫ በተወሰደባቸው ጨዋታ እንኳን ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት እየቻሉ ይገኛሉ።

👉 የአርባምንጭ ከተማ ሰሞነኛ አቋም

በመጨረሻ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገዱት አርባምንጭ ከተማዎች ቀስ በቀስ ወደ ወራጅ ቀጠናው እየተጠጉ ይገኛሉ።

በሊጉ ከአዳማ ከተማ ቀጥሎ በአስራ አራት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት የሚመሩት አርባምንጮች ከጨዋታ አቀራረባቸው መነሻነት በጨዋታዎች ቢያንስ ማሸነፍ ባይችሉ እንኳን አቻ የመውጣታቸው ነገር የማይቀር ይመስል የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ይህን ነገር ለማድረግ እየተቸገሩ ይገኛሉ።

በተጨማሪ ሌላው ትኩረት የሚስበው ጉዳይ በጨዋታዎች በቀላሉ ግቦች የማያስተናግድ የነበረው አርባምንጭ አሁን ላይ ግን በቀላሉ ግቦች እየተቆጠሩበት መገኘቱ ነው። ለአብነትም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ቡድኑ በአማካይ ሁለት ግቦች የማስተናገዱ ነገር በመከላከሉ ረገድ ስለሚገኝበት ሁኔታ ጠቋሚ ነው።

በማጥቃቱ በኩል በተለይ በሊጉ የአዳማ ከተማ ቆይታ መሻሻሎችን አሳይቶ የነበረው አርባምንጭ አሁን ላይ ግን እንደ አጀማመሩ ሁሉ በማጥቃቱ እጅጉን ተዳክሞ እያስተዋልን እንገኛለን። ለአብነትም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ኳሱን ለጅማ አባ ጅፋር ለቆ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የፈለገው ቡድኑ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ፍቃዱ መኮንን ተቀይሮ ከገባ ወዲህ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ዕድል ለመፍጠር ጥረት ቢያደርግም በእነዚህ አጋጣሚዎች ውስጥ ተጫዋቹ ከቡድን አጋሮቹ በቂ ድጋፍ ማግኘት አለመቻሉን ተከትሎ ጥረቱ እምብዛም ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል።

ከከፍተኛ ሊግ እንዳደገ ቡድን የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ በሊጉ መቆየታቸው ብቻ በመልካምነቱ ሊመለከቱት የሚችሉት ውጤት የመሆኑ ነገር ቢታመንም በሊጉ የተሻለ ቦታን ይዞ ለማጠናቀቅ ከሰሞነኛ ማንቀላፋታቸው መንቃት ይኖርባቸዋል። በቀጣይ አራት የጨዋታ ሳምንታት ደግሞ ከአዳማ ፣ ሀዋሳ ፣ ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ጋር እንደመጫወታቸው ብቃታቸውን ማሻሻል ካልቻሉ ነገሮች እንዳይከብዱባቸው ያሰጋል።

👉 ሰበታ ከተማ አሁንም ማሸነፍ አልቻለም

በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ተጋጣሚያቸው ሀዋሳ ላይ በሁለቱም አጋማሾች በእንቅስቃሴ የበላይነት መውሰድ ቢችሉም አሁንም ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

በሁለቱም አጋማሾች ተጋጣሚያቸውን ወደ ራሱ ሜዳ እንዲገፋ በማድረግ ከመስመር መነሻቸውን ባደረጉ ኳሶች ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መሰንዘር ቢችሉም በተጫዋቾቻቸው ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ መነሻነት የነበራቸውን የበላይነት ወደ ግብ መቀየር ባለመቻላቸው ብቻ አሁንም ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል።

በጥቅሉ በጨዋታው በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በግብ ሙከራዎች ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሰበታ ከተማዎች አስፈላጊውን ሦስት ነጥብ ለማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። ይህ ሂደት ታድያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከትነው አይደለም። በተለይ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ቡድኑ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተሻለ ቢመስልም ሙሉ ሦስት ነጥብ ግን ማግኘት አልቻለም።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተመሳሳይ ነጥብ ላይ የነበሩት እና በወራጅ ቀጠና ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ ከሰበታ ከተማ ጋር አብረው ያሳለፉት ጅማ አባ ጅፋሮች አሁን ላይ በተከታታይ ባስመዘገቧቸው ሁለት ድሎች ከሰበታ ጋር የአምስት ነጥብ ልዩነት መፍጠራቸው እና ሌሎች ከአናታቸው የሚገኙ ቡድኖች ጋር እየሰፋ ያለውን የነጥብ ልዩነት ከግምት ስናስገባ ‘ሰበታ ከተማዎች እየረፈደባቸው ይሆን ?’ ብለን እንድናስብ ያስገድዳል።

በሊጉ ለመቆየት በሚያደርገው ጥረት 11ኛው ሰዓት ላይ የሚገኘው ሰበታ በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት ላለመውረድ በሚደረገው ትግል የስድስት ነጥብ ያህል ዋጋ ባለው ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋርን ሲገጥም ማሸነፍ የማይችል ከሆነ በሊጉ የመቆየቱ ነገር እያከተመለት የሚሄድ ይመስላል።

👉 ገራገሩ አዲስ አበባ አሁንም መርቶ ነጥብ ጥሏል

በአሰልጣኝ ሹም ሽር አዙሪት ውስጥ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ አሁንም አስቀድሞ ግብ ባስቆጠረበት የወልቂጤ ከተማው ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ ጎል አስተናግዶ ነጥብ ለመጋራት ተገዷል።

በሊጉ የ22 ሳምንታት ጉዞ ውስጥ ምናልባት በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ከመመራት ተነስቶ ነጥብ የጣለ ቡድን ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ይመስላል። ባሳለፈው የጨዋታ ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ሦስት ጊዜ መርተው አቻ የተለያዩበትን ጨዋታን ጨምሮ ቡድኑ ቀድሞ ግብ ባስቆጠረባቸው ሰባት ጨዋታዎች በድምሩ 16 ነጥቦችን ጥሏል። እርግጥ የትኛውም ቡድን ሁሌም ቢሆን አስቀድሞ ግብ ባስቆጠረበት ጨዋታ ያሸንፋል ማለት ሳይሆን በዚህ ደረጃ ቀድሞ ከመራቸው ጨዋታዎች ነጥብ መጣል ግን በሊጉ ለመቆየት ከሚያልም ቡድን የሚጠበቅ አይደለም።

በታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል የተሻለ የግብ ልዩነት ያለው አዲስ አበባ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እና ግቦችን በማስቆጠር አስከፊ ሪከርድ ያለው ባይሆንም በጨዋታ መሀል የሚያሳየው ባህሪ ግን አንዳንዴ ግራ የሚያጋባ ነው። በተለይም በጥሩ ብልጫ በልበሙሉነት አጥቅቶ ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ ወይ በአግባቡ የማይከላከል ወይ ማጥቃቱን በርትቶ የማያስቀጥል ሆኖ መታየቱ እስካሁን በፕሪምየር ሊግ የአዕምሮ ደረጃ ላይ መገኘቱን አጠራጣሪ ያደርገዋል።

የውድድር ዘመኑን ሦስተኛ አሰልጣኛቸውን ቅጥር የፈፀሙት አዲስ አበባ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እንዲሁም በአንድ ጨዋታ ደግሞ በግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ እየተመሩ የተመለከትናቸው ሲሆን ይህም አለመረጋጋት ቡድኑ ላይ በሚገባ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል። ይህ ሁኔታ ቡድኑ በጨዋታ ወቅት ሜዳ ላይ ከሚያሳየውን ገራገርነት ጋር ተዳምሮ አዲስ አበባን በየጨዋታው ተስፋ የሚሰጥ ነገር ግን ነጥብ ለመያዝ የተቸገረ አሳዛኝ ቡድን አድርጎታል።

የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ በሊጉ መቆየት የሚቻለው በተመዘገበ ውጤት እንጂ ሜዳ ላይ በሚታይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ባለመሆኑ ቡድኑ አሁንም በሊጉ ለመቆየት ከእጁ ያልወጣውን ዕድል በአግባቡ ሊጠቀም ይገባል።