ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

አራተኛው ፅሁፋችን በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ሌሎች ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች የቀረቡበት ነው።

👉 የኮከብ ግብ አግቢነት ዝርዝሩ ለውጦችን ሲያሳይ በርከት ያሉ ተጫዋቾችም ሁለት ያስቆጠሩበት ሳምንት ሆኗል

የሊጉ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክር ረዘም ላሉ ሳምንታት በቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ እና በሲዳማ ቡናው ይገዙ ቦጋለ መካከል የሚደረግ ፉክክር መስሎ ቢቆይም በዚህው ሳምንት ግብ ከፍተኛ ለውጦችን የተመለከትንበት ነበር።

የቶጎ ዜግነት ያለው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ በሁለተኛው ዙር ከሜዳ መራቁን ተከትሎ 10 ግቦች ላይ እስካሁን ረግቶ ቢገኝም ባልነበረባቸው ሰባት የጨዋታ ሳምንታት የአስቆጣሪዎችን ዝርዝር ከመምራት የሚከላክለው አልተገኘም ነበር። ነገር ግን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ኦሮ-አጎሮ ቦታውን አስረክቧል።

ሳምንቱ ከሌሎች ሳምንታት በተለየ መልኩ ሰባት ተጫዋቾች በጨዋታ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር የቻሉበት ነበር። የድሬዳዋ ከተማዎቹ ሄኖክ አየለ እና አብዱረህማን ሙባረክ ሀዲያ ሆሳዕና ላይ ሁለት ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ፣ ጌታነህ ከበደ እና አቡበከር ናስር በድራማዊ ክስተቶች በተሞላው የኢትዮጵያ ቡና እና ወልቂጤ ጨዋታ ላይ ለቡድኖቻቸው ሁለት ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል። ብሩክ በየነ አዲስ አበባ ላይ እንዲሁም ተሾመ በላቸው እና ይገዙ ቦጋለ ደግሞ በግብ በተንበሸበሸው የሲዳማ ቡና እና መከላከያ ጨዋታ የተጋጣሚ መረብን ሁለቴ የፈተሹ ተጫዋቾች ነበሩ።

ታድያ ይህ ሂደት በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪት ዝርዝሩ ላይ ለውጦች እንዲፈጠሩ አድርጓል። በዚህም መነሻነት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ተጨማሪ ሁለት ግቦችን በስማቸው ያስመዘገቡት ይገዙ ቦጋለ ፣ አቡበከር ናስር ፣ ጌታነህ ከበደ እና ሀዋሳ ከተማ ላይ አንድ ግብ ያስቆጠረው ሪችሞንድ አዶንጎ የሊጉን ከፍተኛ አስቆጣሪነት በ11 ግቦች በጣምራ እየመሩ ይገኛሉ። እነሱን ተከትሎ በሁለተኛው ዙር እስካሁን ጨዋታ ማድረግ ያልቻለው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ በ10ግቦች ሲከተል ሀብታሙ ታደሰ እና ብሩክ በየነ ደግሞ በ8 ግቦች ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል።

23ኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የሊጉ ውድድር የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ገና 11 ግቦች ላይ የመገኘታቸው ነገር የሚያነጋግር ቢሆንም ውድድሩ ሲጠናቀቅ ማን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቅቃል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 ጠንከር ያሉ ጉዳቶች የበረከቱበት የጨዋታ ሳምንት

እግርኳስ ከፍተኛ የሆኑ አካላዊ ንክኪዎች ያሉበት የስፖርት ዓይነት እንደመሆኑ በውድድር ሆነ በልምምድ ስፍራዎች ላይ ጥሩ የህክምና ዝግጁነት የመኖሩ ጉዳይ ጥያቄ የሚቀርብበት ጉዳይ አይደለም።

በጨዋታ ሳምንቱ በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ ጠንከር ያሉ ጉዳቶችን የተመለከትንበት ነበር። በተለይም የከነዓን ማርክነህ የትከሻ ጉዳት እና ተካልኝ ደጀኔ ያጋጠመው የጭንቅላት ጉዳት በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ጠንከር ያሉ ጉዳቶች ነበሩ። ጉዳቶቹ ሁለቱን ተጫዋቾች ለተጨማሪ የህክምና እርዳታ ወደ ጤና ተቋማት እንዲያመሩ ያስገደዱ ሲሆን በዚህ ሂደት ግን በተለይ ተጫዋቾቹን ወደ ጤና ተቋማት ለመውሰድ የሚረዳ የመኪና አቅርቦት ጋር በተያያዘ መጠነኛ ክፍተቶችን ታዝበናል።

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተለይ በሜዳ ላይ ለሚከሰቱ አደጋዎች ፈጠን ያለ ምላሽ በመስጠት ረገድ በስታዲየሞች የሚታዩ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም ግን በቂ ነው የሚያስብል ደረጃ ላይ አይገኙም። ለሚከሰቱ ጉዳቶች የመጀመሪያ እርዳታም ሆነ ተጨማሪ የህክምና ሂደት የሚፈልጉ ጉዳቶችን ለማከም በስታዲየሞቻችን ያሉት የመሰረተ ልማት እና የዝግጁነት ደረጃ አሁንም ቢሆን በሰፊው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ጤንነት ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደመሆኑ በዚህ ረገድ “አስከፊ ሁኔተዎችን” ታሳቢ ያደረጉ ዝግጁነቶች በሁሉም ስታዲየሞች አካባቢ ሊፈጠር ይገባል።

👉 ፈጠን ያሉ ግቦች መበራከት

በጨዋታ ሳምንቱ በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች መካከል በአምስቱ ጨዋታዎች በርከት ያሉ ግቦች በመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች የተስተናገዱባቸው ነበሩ።

በጨዋታ ሳምንቱ ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ድሬዳዋ ከተማዎች ሀዲያ ሆሳዕናን በ11 ደቂቃዎች ውስጥ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች መምራት ሲችሉ ወልቂጤም በተመሳሳይ በ20 ደቂቃ ውስጥ ሁለት ግቦች አስቆጥሮ ነበር። መከላከያ እና ሲዳማ ባደረጉት ጨዋታም መከላከያ በ18 ደቂቃዎች ውስጥ በ2-1 ውጤት ቀዳሚ መሆን ችሏል።

በተጨማሪም ሰበታ እና ጅማ ያደረጉት ጨዋታ በ20 ደቂቃዎች ውስጥ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግብ የተቆጠረበት ሲሆን አዲስ አበባዎችም ሀዋሳን ገና በ8ኛ ደቂቃ በተቆጠረች ግብ መምራት የቻሉበትን አጋጣሚ ፈጥረዋል።

በድምሩ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከተቆጠሩ 26 ግቦች ውስጥ አስሩ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች የተቆጠሩ ነበሩ።

👉 በተንኝ የተወረረው ጨዋታ

በጨዋታ ሳምንቱ የመጀመሪያ ዕለት የመጨረሻ የነበረው የአዳማ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ በሜዳ ላይ ከነበረው እንቅስቃሴ ይልቅ በሜዳው ላይ የነበሩት ትንኞች ጉዳይ ትኩረት የሳበ ነበር።

የዕለቱ የመጨረሻ ከነበረው የአዳማ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ መጀመር አስቀድሞ ለጥቂት ደቂቃዎች የጣለውን ዝናብ ተከትሎ በሜዳው ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ትንኞች ሜዳውን ወረው የታዩ ሲሆን በዚህ ሂደት ተጫዋቾች እና ዳኞች በተለይ ደግሞ አሰልጣኞች በጣሙን ሲቸገሩ ታይተዋል። በጨዋታው በአንድ አጋጣሚም የአርባምንጭ ከተማው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በሜዳው ጠርዝ ሆኖ ቡድኑን እየመራ በሚገኝበት ወቅት ትንኝ አፉ ውስጥ በመግባቱን ማስተዋል ችለናል።

ትንኞች በተፈጥሮ የነፋስን ተፅዕኖ ለመቋቋም በሳሮች ውስጥ መደበቅን እንደመምረጣቸው ምናልባት በስታዲየሙ ከፍ ያለ ዝናብ የመጣሉ ጉዳይ ትንኞቹ በዚህ ደረጃ በሜዳው እንዲታዩ አድርጓል። በ2018 የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ በተለይ ቮልጎግራድ ላይ እንግሊዝ እና ቱኒዚያ ያደረጉት ጨዋታ በተመሳሳይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ትንኞች የጨዋታ መነጋገርያ ርዕሰ ጉዳይ እንደነበሩ አይዘነጋም።

👉 ማሻሻያ የተደረገበት ወልቂጤ ከተማ መለያ

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሀገር በቀሉ “ጎፈሬ” የትጥቅ አምራች ኩባንያ የተመረተን የመጫወቻ መለያ እየተጠቀሙ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች መለያቸው ላይ መጠነኛ ማሻሻያን አድርገዋል።

ከዚህ ቀደም በመለያው የግራ እጀታ ላይ ሀገራዊ አንድምታ ያለውን “Visit Ethiopia” የሚል ፅሁፍ በመለያው ላይ የሰፈረ ሲሆን አሁን ደግሞ በቀኝ እጀታው ላይ የቡድኑ አጋር የሆነው ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ስም እና መሪ ቃል የሰፈረ ሲሆን ለዕይታ አስቸጋሪ በሆነ መንገድ ሆነ እንጂ የዩኒቨርስቲው መለያ (Logo) እንዲሁ በመለያው ላይ ሰፍሯል።

እርግጥ የቀደመው የመለያ ንድፍ ይህን ፅሁፍ ታሳቢ ያደረገ ባለመሆኑ ፅሁፎቹን ለማስገባት ሲባል በመጠን አንሰው እንዲሁም መለያ (Logo) ደግሞ በማይታይ መልኩ በመለያው ላይ የሰፈረ ሲሆን ከሀገር በቀል የትጥቅ አምራች ድርጅት ጋር እንደመስራታቸው መለያዎቹ ላይ መጠነኛ የይዘት ማሻሻያ በማድረግ የክለቡን አጋር የተሻለ ዕይታ በሚያገኝ ሁኔታ ማስተዋወቅ እንደሚኖርባቸው ይታሰባል።

👉 ስታዲየሙን ነፍስ የዘሩበት ደጋፊዎች

በሀገራችን ከሚገኙ ስታዲየሞች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የደጋፋ መጠን ማስተናገድ በሚችለው የባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም እየተካሄደ በሚገኘው የሊግ ውድድር የባህር ዳር ከተማ እና የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ለስታዲየሙ ህይወት እየሰጡት ይገኛል። በተለይ ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሲኖራቸው በስታዲየሙ ከሌሎች ጨዋታዎች እጅግ የላቀ ቁጥር ያለው ደጋፊ በሜዳው የምንመለከት ሲሆን ይህም ለግዙፉ ስታዲየም የተለየ ድባብን ሲያላብሰው እየታየ ይገኛል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ባህር ዳር እና ፋሲል ከነማ እርስ በእርስ ባደረጉት ጨዋታ ደግሞ ይህ ድባብ ይበልጥ ገዝፎ ሲታይ በሜዳው የነበረውን የተጋጋለ የድጋፍ ስሜትም አስደናቂ ነበር። በተቃራኒው ሌሎች ቡድኖች ሲጫወቱ ግን ከሜዳው ግዙፍነት እና ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ እጅግ ጥቂት ቁጥር ያለው ተመልካች ጥላ በሚሆንባቸው አካባቢዎች ብቻ የምንመለከት መሆኑ ብዙዎቹ ጨዋታዎች ያለተመልካች የመካሄድ ስሜት ሲኖራቸው እያስተዋልን እንገኛለን።