ተስፋ ያለመቁረጥ ተምሳሌት የሆነው ሄኖክ አየለ

👉”እግር ኳስ በቃኝ ፤ አልጫወትም። ብዬ ነበር”

👉”አሠልጣኜ ከሚሰጠኝ ልምምድ በተጨማሪ በግሌ ተጨማሪ የጥንካሬ ልምምዶችን እሰራለው”

👉”እኔ የጉዳቴን ዘመን አጠናቅቄያለው ብዬ ነው የማስበው”

👉”ዘመኑ ከተጋጣሚ ከተከላካዮች ጋር ብቻ ቆመህ የምትጫወትበት አይደለም”

👉”የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ይገባኛል አይገባኝም የሚል ነገር ውስጥ መግባት አልፈልግም”

በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ምርጥ ብቃት ላይ ከሚገኙ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው የዛሬው እንግዳችን የተወለደው ወንዶ ገነት ኬላ በምትባል ከተማ ነበር። ከልጅነቱ ጀምሮ እግር ኳስን እንደሚጫወት የሚናገረው እንግዳችን ወላጅ አባቱ ሀዋሳ ላይ ሥራቸው ስለነበር ከትውልድ ከተማው ገና በአፍላነቱ የመውጣት ዕድል አጋጠመው። በሀዋሳ ኑሮ የጀመረው የቤተሰብ ፍሬ የሆነው የአሁኑ ተጫዋች ትምህርቱን እየተማረ እንደ ማንኛውም ታዳጊ በሰፈር ውስጥ ኳስን መጫወት ይቀጥላል። ሰፈር ውስጥ ማርስቶፕስ የሚባል ቡድን ገብቶ መጫወት ከጀመረ በኋላ ራሱን ለማጎልበት በፕሮጀክት ታቅፎ መሠልጠን ያዘ። ከፕሮጀክቱ ከወጣ በኋላ ደቡብ መምህራን ለተባለ ክለብ በመጫወት የመጀመሪያ የክለብ ህይወቱን ጀምሮ በደቡብ ፖሊስ፣ አዳማ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ዲላ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ቀጥሎ በአሁኑ ሰዓት ድሬዳዋ ከተማ ይገኛል። በተከታታይ 6 ጨዋታዎች ላይ ብቻ ለቡድኑ 7 ጎሎችን በማስቆጠር ከአጠቃላይ የቡድኑ ጎል 30.4% በስሙ ያስመዘገበው ሔኖክ አየለ ከዝግጅት ክፍላች ጋር ቆይታ አድርጓል።

አንድ ሜትር ከሠማንያ ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ሄኖክ ከወቅታዊ ብቃቱ ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮችን ከማንሳታችን በፊት ከዚህ ቀደም የነበረበትን የጉዳት ታሪክ እንዲያጫውተን ጠይቀነው “ከደቡብ ፖሊስ በኋላ አዳማ ከተማ ስገባ የእግርኳስ እድገቴ በጣም ጥሩ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ነገርግን 2003 ህዳር ወር ላይ በጨዋታ ኳስ በግንባሬ ገጭቼ መሬት ሳርፍ ጉልበቴን አመመኝ። የመጀመሪያ የጉልበት ጉዳቴ መነሻ እቺ አጋጣሚ ነበረች።” በማለት አስቸጋሪውን የጉዳት ታሪክ መነሻ መተረክ ይጀምራል።

በህዳር ወር የተከሰተው ጉዳት ለሔኖክ ህይወት አሉታዊ ነገር ይዞ ቢመጣም ጠቀሜታም እኩል አምጥቷል። ተጫዋቹ ጉዳቱን ባስተናገደ ማግስት አንድ ጨዋታ እንዲያርፍ ተደርጎ ቡድኑ ወደ መቐለ በማምራት ታኅሣሥ 24 ቀን 2003 ትራንስን በ11ኛ ሳምንት አሸንፎ ሲመለስ እዳጋ ሀሙስ አካባቢ የመኪና አደጋ ያስተናግዳል። በአደጋው ሁለት የቡድኑ አባላት አልፈው በርካቶች ጉዳት ሲያስተናግዱ ሔኖክ ለህክምና አዲስ አበባ ይገኝ ነበር። ከዚህ ጉዳት ያመለጠው ተጫዋቹ ቡድኑ በሊጉ የተወሰነ እረፍት ሲሰጠው እርሱም ከጉዳቱ አገግሞ ለመጫወት የሚያስችለው ቁመና ላይ በመድረስ መጫወቱን ይቀጥላል።

በአዳማ የሁለተኛ ጊዜ ቆይታው ክለቡን እስከ አምበልነት ያገለገለው ተጫዋቹ ቡድኑን ወደ ዋናው የሀገሪቱ የሊግ እርከን ለማብቃት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እያለ ይህ የጉልበት ጉዳት መልሶ ያገረሽበታል። 2006 ነሐሴ ወር ላይ ጠንከር ያለ ህክምና ጉልበቱ ላይ በህንዳዊው ዶክተር ሳህዳት ቢያደርግም ከዶክተሩ ጋር የነበረው የክትትል ጊዜ በመቋረጡ በቶሎ ወደ ጤነኝነት መምጣት አልቻለም። በግሉ የጂምናዚየም ሥራዎችን በመስራት ለማገገም ቢጥርም እስከ 2009 ድረስ ዳግም ኳስን መጫወት ሳይችል አስቸጋሪውን ቆይታ አሳልፏል።

ገና ብዙ ሳይጫወት ተስፋ አስቆራጭ የጉዳት ታሪክ አሁንም ያጋጠመው ተጫዋቹ “ኳስን ለማቆም ልወስን ነበር” ያለበትን ጊዜ ደግሞ እንዲህ ያጋራናል። “ከጠቀስኩት ጉዳት በኋላ 2009 ላይ ወልቂጤ ከተማ ገብቼ መጫወት ጀመርኩ። ሲቲ ካፕ ላይ ዋንጫ አሸንፈን የከፍተኛ ሊጉ ውድድር ሲጀመር ከናሽናል ሲሚንት ጋር ነበር የመጀመሪያ ጨዋታችን። በዚህ ጨዋታ የግንባር ኳስ ላገባ ዘልዬ ስገጭ ተከላካዩ ኳስ አገኘው ብሎ ጭንቅላቴን ከኋላ ገጨኝ። በዚህ ሰዓት ራሴን አላውቅም። ከዛ በኋላ እንደተረዳሁት ምላሴ ተንሸራቶ (ታጥፎ) ነበር። ወደ 9 ደቂቃ ራሴን ስቼ ነበር። ምላሴንም ማውጣት አቅቷቸው ሲታገሉ ነበር። ከደጋፊ መሐል ነው አንድ ዳኛ የነበረ ሰው የመዓዘን ባንዲራ ማቆሚያውን አፌ ውስጥ ከቶ ያወጣልኝ። የምላስ መንሸራተት በእግር ኳስ ያጋጥማል ግን የእኔ ከዚህም ለየት የሚያደርገው በጣም ስላመመኝ አዲስ አበባ ለተሻለ ህክምና ሄጄ እንድታይ አስገድዶኝ ነበር። ሲቲ ስካን ተነስቼ ውጤቱ ሲታይ ቅሌ ተቀጥቅጦ ነበር። በተጨማሪም ወደ ውስጥ ትንሽ ደም ፈሶ ነበር። ይህ ከፍተኛ ህመም ነበር። በዚህ ጊዜ እግር ኳስ በቃኝ ፤ አልጫወትም። ብዬ ነበር። በጣም ከፍተኛ ህመም እና ስቃይ ነበረው። ቀን በቀን ብዙ ፍሬ መድሐኒት እወስድ ነበር።”

ሔኖክ እግር ኳስን ደግሜ አልጫወትም ቢልም የሚወደው እግር ኳስ ዳግም በዲላው አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ አማካኝነት ይጠራዋል። ከሁለቱ አሰቃቂ ጉዳቶች በኋላም 2010 ሚያዚያ ወር ላይ የክለብ ህይወቱን በዲላ ከተማ ይቀጥላል። ከዛም በድጋሜ ወደ ደቡብ ፖሊስ ካመራ በኋላ አንድ ዓመት ለሀዋሳ አንድ ዓመት ደግሞ ለወልቂጤ ተጫውቶ ዘንድሮ የምስራቁ የሀገራችን ክፍል ድሬዳዋ ደርሷል። ህይወት በብርቱካናማዎቹ ቤት እንዴት ነው? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ ጎል ፊት ደፋር የሆነው አጥቂ ሚዲያም ፊት ደፋርነቱን ባሳየበት አንደበቱ እንዲህ ይመልሰዋል።

“ድሬዳዋ የገባሁት ቡድኑ ዝግጅት ከጀመረ በኋላ ነው። አሠልጣኝ ዘማርያም ‘ያለህን ብቃት አውቃለው። ለዚህ ቡድን ታስፈልጋለህ’ ስላለኝ ነው ድሬዳዋ የፈረምኩት። ባለችው ቀን ልምምዴን ከሰራው በኋላ የመጀመሪያው ጨዋታችን ከወላይታ ድቻ ጋር ነበር። እኔ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ነበርኩ። ጨዋታው 0ለ0 እያለ 80ኛው ደቂቃ አካባቢ ተቀይሬ ገባሁ። በደቂቃዎች ልዩነት ሊያልቅ ሲል ጎል አግብቼ አሸነፍን። በሁለተኛው ጨዋታ ከሲዳማ ጋር ስንጫወትም ሁለት ለባዶ እየተመራን 82ኛው ደቂቃ አካባቢ ተቀይሬ የመግባት ዕድል ካገኘው በኋላ በድጋሜ መጫወት አልቻልኩም። እርግጥ ቡድኑም ትንሽ ጥሩ ስላልነበር ውጥረት ነበር። አሠልጣኞቹም ጋር ውጥረት ነገር ስለነበረ ነው መሰለኝ ዕድሉን ማግኘት አልቻልኩም። ድሬዳዋም ላይ ውድድሩ ከሄደ በኋላ አንድ ጨዋታ ላይ ብቻ ቋሚ ሆኜ ገብቼ እረፍት ላይ ተቀየርኩ። ከዚህ በኋላ ተቀይሬ የገባሁባቸው ጨዋታዎች ጥቂት ናቸው።”

በአንደኛው ዙር የሊጉ ውድድር ብዙ የመጫወት ዕድል አላገኘሁም የሚለው አጥቂ በሁለተኛው ዙር አሠልጣኝ ሳምሶን አየለ ከመጣ በኋላ የተሻለ የጨዋታ ደቂቃ እያገኘ ነው። መጫወት ብቻ ሳይሆን ተከታታይ ጎሎችንም እያስቆጠረ አደገኛ ቦታ ላይ የሚገኘውን ክለቡን እየጠቀመ ይገኛል። የመሰለፍ ዕድል ባገኘባቸው ጨዋታዎች ላይ የተስተዋለበትን የቦታ አያያዝ ችሎታው ያዳበረበትን መንገድ ደግሞ እንዲህ ይገልፃል። “እኔ የመሐል አጥቂ ነኝ። እንደዚህ አይነት ቦታዎች ላይ ስትጫወት መብሰል ያስፈልጋል። እንደምታውቀው ከእኛ የተሻሉ ሊጎች ዓለም ላይ አሉ። ጨዋታዎችን በማይበት ጊዜ እኔ በምጫወትበት ቦታ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ምን አይነት እንቅስቃሴ ነው የሚያደርጉት የሚለውን በጣም በትኩረት አያለው። ዘመኑ ከተጋጣሚ ከተከላካዮች ጋር ብቻ ቆመህ የምትጫወትበት አይደለም። ወደኋላ እየወረዱ መጫወት እና ክፍተቶችን መፍጠር ጠቀሜታዎች አላቸው። እነኚህን ነገሮች ማየት ነው። አሠልጣኜ ከሚሰጠኝ ልምምድ በተጨማሪ በግሌ ተጨማሪ የጥንካሬ ልምምዶችን እሰራለሁ።”

በ8 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ሔኖክ መግቢያችን ላይ ያጫወተንን የጉዳት ታሪክ በመንተራው ከ2010 በኋላ ራሱን ከጉዳቶች ጠብቆ እየተጫወተ የተገኘበትን ሚስጢር ሲናገር “እኔ የጉዳቴን ዘመን አጠናቅቄያለው ብዬ ነው የማስበው። እንደዛ ነው የሚሰማኝ። ልምምድ በደንብ መስራት ስትችል ለጉዳት የመጋለጥ ዕድልህ ይቀንሳል። ተጨማሪ ልምምዶችን በመስራት ራስን ወደ ጥንካሬ ማምጣት ይቻላል። እኔን እግዚአብሔርም እየጠበቀኝ ነው። ለሰው ልጅ ዋናው ነገር ጤና ነው። ለዚህ ወደ እግዚአብሔር እፀልያለው። በነገሮች ሁሉ እንዲያግዘኝ እፀልያለው። ይህ ነው ሚስጢሩ ብዬ ነው የማስበው።”

ለድሬዳዋ ከተማ በአማካኝ በየ85 ደቂቃው ግብ እያስቆጠረ የሚገኘው ሔኖክ በራሱ ላይ ስላለው እምነት፣ ትዕግስቱ እና ተስፋ አለመቁረጡ የሚለው ነገር አለ። “እኔ በነገሮች ቶሎ ተስፋ ቆርጦ እጅ መስጠት የሚባል ነገር አልወድም። ከሁሉም በላይ ግን እምነቴ በአምላኬ ላይ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብዬ ስለማምን አባት ደግሞ ልጅ የሚጠይቀውን ነገር ያደርግለታል። ከዚህ ባሻገር ተስፋ መቁረጥ በህይወቴ የለም። በጣም ታጋሽ ነኝ።”

2003 መጨረሻ ላይ በአሠልጣኝ ቶም ሴንትፊት የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦለት የነበረው ቢሆንም በልምምድ ወቅት በደረሰበት ግጭት ቀድሞ የደረሰበት ጉዳት ላይ ሌላ ጉዳት አስተናግዶ ከቡድኑ ተለያይቶ ነበር። ከዛ ጊዜ በኋላ ግን አንድም ጊዜ ሀገራዊ ጥሪ ሳይደርሰው የቆየ ሲሆን አሁን ብዙዎች ለቦታው እያጩት ቢገኙም እርሱ ምርጫውን ለአሠልጣኙ እንተው ሲል ይደመጣል።

“ጥሪውን የሚወስነው የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ነው። እኔ አሁን ትኩረት ማድረግ የምፈልገው ድሬዳዋ ያለበት ደረጃ አስተማማኝ ስላልሆነ ይሄንን ነገር መለወጥ ላይ ነው። በተቻለኝ አቅም ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን ክለቡን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ ነው። የተሻለ ደረጃ ላይ በማድረስ ውስጥ እየተሳካልኝ ይሆናል። የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ይገባኛል አይገባኝም የሚል ነገር ውስጥ መግባት አልፈልግም። እርሱ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ውሳኔ ነው። ውሳኔው ምንም ይሁን ምንም እቀበላለው።”

69 ኪሎ የሚመዝነው አጥቂ “እኔ ዋነኛ ሀሳቤ ድሬዳዋ ከተማን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ ነው። በግሌም ሆነ በቡድን የማስበው ይሄ ነው። እኔ ጎል ካላገባው ድሬዳዋ ከተመሰ አያሸንፍም የሚል ነገር ውስጥ የለሁም። በተቻለኝ መጠን እና በሙሉ ሀይሌ ክለቡን ማገዝ ነው ሀሳቤ። በዚህ ውስጥ ጎሎችን ማስቆጠር ይኖራል። ጎሎችን በተቻለኝ አቅም አስቆጥሬ ቡድኔ ካለበት አደገኛ ቀጠና ማውጣት ነው ህልሜ ፤ እንጂ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ የመሆን ሀሳብ ውስጥ አይደለም ያለሁት። ክለቤን በማዳን ሂደት ውስጥ ምናልባት ግን ይህ ነገር ሊኖር ይችላል።” በማለት ቀጣይ ጉዞውን በተመለከተ ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል።

“ጠንክሮ በመስራት ነገሮችን ማሸነፍ ይቻላል” የሚል መርህ እንዳለው የሚናገረው እንግዳችን በህይወቱ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረጉለትን ሰዎች ከማመስገኑ በፊት ለስፖርተኞች ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር አለ በማለት ተከታዩን ሀሳብ አጋርቶናል። “ብዙ መሰናክሎች ቢኖሩም ማለፍ እንደሚቻል ለስፖርተኞች ማስተላለፍ እፈልጋለው። የተለያዩ ነገሮች ቢከሰቱም ጠንክረው ከሰሩ ማለፍ እንደሚቻል ማመን አለባቸው። ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም። ጠንክሮ በመስራት ነገሮችን ማሸነፍ ይቻላል።”

በመጨረሻም “ፈጣሪዬ እግዚአብሔርን ማመስገን እፈልጋለው። እርሱ ባይረዳኝ አሁን ያለሁበት ቦታ አልቆምም። ተስፋ ከቆረጥኩበት ተመልሼ መጫወት እንድችል የረዳኝ እርሱ ነው። ከዚህ ባሻገር እናቴ ዘነበች ካሣ በእኔነቴ ላይ በጣም ከፍተኛ ሚና ነው የተጫወተችው። በተለይ በጉዳቴ ሰዓት እንዳልጨነቅ ከጎኔ ሆና በብዙ አግዛኛለች። ታናሽ ወንድሜ እርቅይሁን አየለም ከታናሽ በማይጠበቅ ነገር ብዙ አበረታቶኛል። በህክምና ዘርፍ ደግሞ አሁን ወልቂጤ ከተማ የሚገኘው ፊዚዮቴራፒስት ታምሩ ናሳ በአምሮም ሆነ በአካል እንድነሳሳ ያግዘኝ ነበር። በመጨረሻም በክለብ ደረጃ እንድጫወት ያደረጉኝን አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እና ዘላለም ሽፈራውን አመሰግናለው።” በማለት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር የነበረውን ቆይታ አገባዷል።