ቤትኪንግ  የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

በሁለተኛው የትኩረታችን ክፍል በጨዋታ ሳምንቱ የታዘብናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች ተካተዋል።

👉 ያለ አግባብ የሚመዘዙ ካርዶች እና የተጫዋቾች ቅጣት

የሊጉን ጨዋታዎች የሚከታተል ሁሉ በግልፅ መታዘብ እንደሚችለው ከበርካታዎቹ የማስጠንቀቂያ ካርዶች በስተጀርባ ያለው ምክንያት የዳኛን ውሳኔ በመቃወም የሚፈጠሩ የቃላት ልውውጦች እና አተካራዎች እንደሆኑ በቀላሉ የሚታዘበው እውነታ ነው። በዚህ መልኩ የሚገኙ ቢጫ ካርዶች የተለያዩ ቡድኖችን እየጎዱ እንደሆነ እየተመለከትን እንገኛለን።

ለአብነትም ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የቢጫ ካርድ ክምችታቸው አምስት መድረሱን ተከትሎ ግርማ በቀለ እና ተስፋዬ አለባቸውን መጠቀም ያልቻለው ሀዲያ ሆሳዕና የመከላከል መዋቅር እንዴት እንደተፋለሰ እና ቡድኑ በቀላሉ ግብ ሲያስተናግድ እንደነበር ተመልክተናል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም እንዲሁ እጅግ ጠባብ በሆነ ስብስብ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ወላይታ ድቻ እንዲሁ ያለ ሁለገቡ ያሬድ ዳዊት ለመጫወት መገደዱን ተመልክተናል።

በሳምንቱ በነበሩ ሌሎች ጨዋታዎችም በኢትዮጵያ ቡና በኩል አቡበከር ናስር (5ኛ ቢጫ) እና ዊልያም ሰለሞን (10ኛ ቢጫ) ፣ የባህር ዳር ከተማው ፉአድ ፈረጃ (5ኛ ቢጫ) ፣ የአዳማ ከተማው ዮሴፍ ዮሐንስ (5ኛ ቢጫ) ካርዳቸውን በተመሳሳይ ባልተገባ ድርጊት መመልከታቸውን ተከትሎ በቀጣይ ጨዋታ ቡድኖቻቸውን ማገልገል አይችሉም።

እነዚህን ተጫዋቾች ለአብነት ማንሳታችን ለቡድናቸው ካላቸው አበርክቶ አንፃር በቀጣይ ጨዋታ የእነሱን ግልጋሎት ቡድናቸው ማግኘት አለመቻሉ የሚፈጠረው ጫና በቀላሉ የሚገለፅ ስለማይሆን እንጂ ሰፋ ያለ ጥናት ቢደረግ በሁሉም ቡድኖች ውስጥ ተጫዋቾች ውጤት ቀያሪ የሆኑ አስገዳጅ ጥፋቶችን ሰርተው የማስጠንቀቂያ ካርድ የሚመለከቱባቸው አጋጣሚዎች ከአጠቃላይ የቢጫ ካርዶች ቁጥር አንፃር ሲታዩ ዝቅተኛ መሆናቸው የማይቀር ነው።

በመሆኑም ተጫዋቾች ሜዳ ላይ በሚቆዩባቸው ደቂቃዎች በሙሉ የኃላፊነት ስሜት ጨዋታዎችን በማድረግ እና ረብ የለሽ በሆኑ እና ለቡድን ምንም ጠብ የሚል ጥቅም በማያስገኙ ያልተገቡ ንትርኮች የሚመጡ ካርዶችን በማስወገድ ቡድናቸውን ከጉዳት ሊታደጉ ይገባል።

👉 ከፍ ብሎ እየበረረ የሚገኘው ሄኖክ አየለ

በመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎች በአጠቃላይ ሰባት ግቦችን ያስቆጠረው ሄኖክ አየለ ምናልባት የእግርኳስ ህይወቱን ምርጥ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።

ተደጋጋሚ አስከፊ ጉዳቶችን ቢያስተናግድም ተስፋ ባለመቁረጥ ተንገራግጮ የነበረውን የእግርኳስ ህይወቱን ዳግም ወደ መስመር እያስገባ የሚገኘው ሄኖክ በውድድር ዘመኑ በድምሩ ስምንት ግቦችን ለድሬዳዋ ከተማ ማስቆጠር ችሏል። በአማካይ በ85 ደቂቃዎች አንድ ግብ እያስቆጠረ የሚገኘው አጥቂው ቡድኑ በውድድር ዘመኑ ካስቆጠራቸው ግቦች ውስጥ 34.78℅ የሚሆኑትን በስሙ አስመዝግቧል።

እነዚህም ግቦች ላለመውረድ እየታገለ የነበረውን ቡድን በአሁኑ ወቅት በመጠኑም ቢሆን ከዚህ የስጋት ቀጠና ሸሽቶ በ28 ነጥቦች ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ እንዲል አስችለውታል። ቡድኑን ከወራጅ ቀጠና ውስጥ የማውጣት ቀዳሚ አላማ ሰንቆ እየተጫወተ እንደሚገኝ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበረው ቆይታ የተናገረው አጥቂው ‘ያለበት ድንቅ አቋም ድሬዳዋን በሊጉ የተሻለ ቦታ ይዞ ለማጠናቀቅ ያስችለው ይሆን ?’ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 የጋቶች ፖኖም ወሳኝ ግቦች

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካመራ ወዲህ በቡድኑ አስደናቂ የሊግ ጉዞ ውስጥ ዓይነተኛ ድርሻ እየተወጣ የሚገኘው ጋቶች ፖኖም በወሳኝ ጨዋታዎች ቡድኑን መታደግ ቀጥሏል።

በ20ኛ የጨዋታ ሳምንት በዋንጫ ፉክክሩ እጅግ ወሳኝ በነበረው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና ጠንካራ ፈተና በገጠመው ጊዜ ግዙፉ አማካይ በመጀመሪያ አጋማሽ መገባደጃ ደቂቃ ላይ በጨዋታው ልዩነት የፈጠረችውን ግብ ከቆመ ኳስ መነሻውን ባደረገ ሂደት ማስቆጠር ችሏል። በተመሳሳይ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከጅማ አባ ጅፋር እንዲሁ ጠንካራ ፈተና ቢገጥመውም በተመሳሳይ ጋቶች ፖኖም በ57ኛው ደቂቃ በቀጥታ ከቆመ ኳስ አክርሮ ባስቆጠራት ግብ ጊዮርጊስን ባለ ድል አድርጓል።

በድምሩ ለቡድኑ በ1693 የጨዋታ ደቂቃዎች ላይ ተሳትፎ ያደረገው ጋቶች ፖኖም ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫ የሚያነሳ ከሆነ ያስቆጠራቸው ግቦች ከፍተኛ ዋጋ የሚያሰጡት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

👉 የተቻለውን እያደረገ የሚገኘው አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ

በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘውን ሰበታ ከተማ በሊጉ እንዲቆይ ለማድረግ በደካማው ስብስብ ውስጥ ጎልተው እየወጡ ከሚገኙ ወጣት ተጫዋቾች መካከል አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ቀዳሚው ነው።

እንደ ቡድን በተለይ መሀል ለመሀል በሚደረጉ ማጥቃቶች ውጤታማ ያልነበረው ሰበታ ሁነኛ የጨዋታ አቀጣጣይ ለማግኘት በርካታ ተጫዋቾችን ቀያይሮ ሲጠቀም አብዱልሀፊዝ ተገቢው ዕምነት ተጥሎበት ነበር ለማለት ያስቸግራል። ሆኖም በተለይ አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ ወደ ዋና አሰልጣኝነት ከመጡ በኋላ ዋነኛ የፈጠራ ኃላፊነት የተጣለበት ወጣቱ አማካይ የተቻለውን ጥረት እያደረገ ይገኛል። በዚህም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከሊጉ ግርጌ የተላቀቀበትን ውጤት ሲያስመዘግብ ወሳኟን የማሸነፊያ ግብ ዱሬሳ ሹቢሳ ሲያስቆጥር የአብዱልሀፊዝ ቶፊቅ አስደናቂ ኳስ የማቀበል ሂደት ትልቅ ዋጋ ነበረው።

በተጨማሪም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አማካዩ በመጀመሪያው አጋማሽ እንዲሁ ከሰሞኑ በስፋት እያደረገ እንደሚገኘው ዘግይቶ ወደ ሳጥን በመድረስ ያደረገው የግብ ሙከራ በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ጅማ አባ ጅፋርን ሲረታ ወሳኟን የማሸነፊያ ግብ ከፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ተጫዋቹ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች በጣም በተሻለ ብቃት ሰበታን ለማገልገል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

በውድድር ዘመኑ በ20 ጨዋታዎች ተሰልፎ መጫወት የቻለው ወጣቱ አማካይ የመጀመሪያ ግቡን ባለፈው የጨዋታ ሳምንት እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ የመጀመሪያውን ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል የቻለ ሲሆን ቡድኑ በሊጉ እንዲቆይ ለማድረግ ግን የሰሞኑን ብቃቱን በተከታታይ ጨዋታዎች መድገም ይኖርበታል።

👉 ፍፁም ቅጣት ምት መቺዎቹ የመሀል ተከላካዮች

መከላከያ በፋሲል ከነማ በተሸነፈበት ጨዋታ መከላከያዎች ቀዳሚ የሆኑበት ግብ የተገኘው የመሀል ተከላካያቸው አሚን ነስሮ ወደ ግብነት በቀየራት የፍፁም ቅጣት ምት አጋጣሚ ነበር። ይህም በዘንድሮ የውድድር ዘመን በሁለተኛው ዙር ቡድኑን በተቀላቀለው ተጫዋቹ ስም የተመዘገበች ሁለተኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ እንድትሆን አድርጓል።

የተለየ የአዕምሮ ጥንካሬ በሚጠይቀው በዚህ ኃላፊነት ላይ በሊጋችን የመሀል ተከላካዮች በአንዳንድ ክለቦች ጥቅም ላይ ሲውሉ እያስተዋልን እንገኛለን። አሚን ነስሩም ወደዚህ ዝርዝር የተካተተ ሌላኛው ተጫዋች ሆኗል። መከላከያዎች የፍፁም ቅጣት ምት መቺነት ኃላፊነቱን ቢኒያም በላይን ጨምሮ ለተለያዩ ተጫዋቾች በመስጠት ቢሞክሩም አሁን ላይ ግን አስተማማኝ አማራጭ ያገኙ ይመስላል።

ያሬድ ባየህ ሜዳ ላይ በሚኖርባቸው ጊዜያት የፋሲል ከነማ ቀዳሚ የፍፁም ቅጣት ምት መቺ ሲሆን ከዚህ ባለፈ የሰበታ ከተማው የመሀል ተከላካይ በረከት ሳሙኤል እና አሁን በፋሲል የሚገኘው አስቻለው ታመነ በቀድሞ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የፍፁም ቅጣት ምት ኃላፊነትን ሲወጣ ተመልክተናል።

👉 ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ በዚህ ሳምንት ደግሞ አስቆጥሯል

ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማ ባህር ዳርን ሲረታ ተቀይሮ በመግባት ፍቃዱ ዓለሙ ላስቆጠራት ግብ መንስኤ የነበረው ናትናኤል በዚህ ሳምንት ደግሞ ወሳኟን ግብ አስገኝቷል።

በባህር ዳር ከተማው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ፍቃዱ ዓለሙ ላስቆጠራት ፍፁም ቅጣት ምት መገኛ የነበረ ሲሆን በዚህኛውም የጨዋታ ሳምንት በተመሳሳይ ቡድኑ መከላከያን ሲረታ እንዲሁ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባ ሲሆን በዚህም በአንድ አቻ ውጤት በቀጠለው ጨዋታ በ74ኛው ደቂቃ ላይ ወሳኟን የማሸነፊያ ግብ አስቆጥሯል።

በዘንድሮ የውድድር ዘመን በ18 ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ የቻለው ተጫዋቹ ለ13ኛ ጊዜ ተቀይሮ ገብቷል። በዚህ ረገድ በሊጉ ብዙ ጨዋታዎች ከተጠባባቂነት እየተነሳ ያደረገ ተጫዋች ፈልጎ ማግኘት ከባድ ይመስላል። ነገር ግን ተጫዋቹ በሜዳ ላይ በቆየባቸው ደቂቃዎች ለቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን ቀጥሏል።

በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ይህን ያስመሰከረው ተጫዋቹ ቡድኑ ወላይታ ድቻን ከመመራት ተነስቶ ሲያሸንፍ እንዲሁ ውጤቱን በመቀየር ረገድ የነበረው አስተዋጽኦ ቀላል አልነበረም።

👉 ሙጂብ ቃሲም ወደ ቀደመው ሚናው ተመልሷል

በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ከአልጄሪያው ክለብ መልስ ፋሲል ከነማን የተቀላቀለው ሙጂብ ቃሲም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ዳግም በመሀል ተከላካይነት ሚና ተሰልፎ ሲጫወት አስተውለናል።

ወደ ፋሲል ከተመለሰ ወዲህ ይህን የመከላከያውን ጨዋታ ሳይጨምር በሦስት ጨዋታዎች ለ210 ደቂቃዎች ብቻ ተሰልፎ መጫወት የቻለው ሙጂብ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የያሬድ ባየህ በቅጣት አለመኖርን ተከትሎ ትክክለኛ ተተኪዎቹ አስቻለው ታመነ እና ዳንኤል ዘመዴ እንዲሁም ከሰሞኑ በሚና ሽግሽግ ቡድኑን እያገለገለ የሚገኘውን ሰዒድ ሀሰንን በተጠባባቂ ወንበር አስቀምጦ ከከድር ኩሉባሊ ጋር ተጣምሮ ቡድኑን በመሀል ተከላካይነት ማገልገል ችሏል።

እርግጥ በጨዋታው ይህ ነው የሚባል ፈተና ባይገጥመው ከረጅም ጊዜያት በኋላ ወደ መሀል ተከላካይነት እንደመመለሱ ጥሩ የሚባል ጊዜን ማሳለፍ ችሏል። ምናልባት በቀሪዎቹ ጨዋታዎች በተለይ ከወገብ በታች ባሉ ተጫዋቾች የአቋም መውረድ እየታማ ለሚገኘው ቡድኑ ሙጂብ ቃሲም ዓይነተኛ መፍትሄ ይሰጥ ይሆን የሚለውን በቀጣይ የምንመለከተው ይሆናል።

ከጨዋታው በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡት የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ተከታዩን ብለዋል

“ሙጂብ ከዚህ በፊት የነበረበት ቦታ ስለሆነ የሚከብደው አይደለም። ልጆች በቅጣት እና በህመም ስታጣ ያለህ አማራጭ ይሄ ነው። ስለዚህ እሱን ነው ያለፉት ሦስት ቀናት ልምምድ ስንሰራ የነበረው ፤ ገብቶም ጥሩ ነገር ነው ያደረገው። በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲሉ ተደምጠዋል።

👉 ወላይታ ድቻ አሁንም ፊቱን ወደ ወጣት ተጫዋቾች ያዞር ይሆን

በሊጉ ምናልባት “ስስ” ስለሆኑ የቡድን ስብስቦች ስናስብ ቀድመው ወደ አዕምሯችን ከሚመጡ ቡድኖች አንዱ ወላይታ ድቻ ነው።

ከወራት በፊት አጥቂው ስንታየሁ መንግሥቱን በጉዳት ያጣው ቡድኑ ከሰሞኑ ደግሞ ምንይሉ ወንድሙን እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሌላኛውን የአጥቂ መስመር ተሰላፊ የሆነው ቃልኪዳን ዘላለምን በጉዳት ምክንያት አጥቷል። በዚህ የተነሳ በጉዳት የሳሳውን የቡድኑን የፊት መስመር ለመጠገን ዳግም ፊቱን ወደ ወጣት ተጫዋቾች ያዞረ ይመስላል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በውድድር ዘመኑ እምብዛም የመሰለፍ ዕድል ያላገኙት መሳይ ኒኮል እና ዮናታን ኤልያስ ተቀይረው በመግባት ተጫውተዋል። ይህ አካሄድ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በተመሳሳይ ቡድኑ በጉዳት እና በኮቪድ በተቸገረበት ወቅት ፊቱን ወደ ወጣት ተጫዋቾች በማዞር በንፅፅር የተሻለ የውጤት ጉዞን ማድረግ ችሎ የነበረበትን ጊዜ ያስታውሰናል። በዛ ወቅት ለቡድኑ ከደረሱለት ተጫዋቾች ውስጥ መልካሙ ቦጋለ እና አበባየሁ አጪሶ ዘንድሮ ይበልጥ አድገው ከፍ ያለ ኃላፊነት እየተሰጣቸው ተመልክተናል። በመሆኑም ይህ የችግር ወቅት ለወጣቶች ዕድል በመስጠት የማይታማው ወላይታ ድቻ አዳዲስ ፊቶችን እያስተዋወቀ ለቀጣይ ዓመታት ጎልብተው የሚወጡ ሌሎች በልኩ የተሰፉ ተጫዋቾችን ሊያገኝ የሚችልበት አጋጣሚ ውስጥ ያለ ይመስላል።