ወላይታ ድቻ የቅጣት ውሳኔ ተወሰነበት

የሊጉ አክስዮን ማህበር በ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የዲሲፕሊን ጥሰት ተፈፅሟል ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል።

በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እየተካሄደ የሚገኘው እና 24ኛ ሳምንት ላይ የደረሰው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ምክንያት ከመቋረጡ አስቀድሞ ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ጨዋታዎች ይቀሩታል። ታዲያ በ24ኛ ሳምንት በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች ዙርያ የውድድሩ የበላይ አካል የተለያዩ ጥፋቶችን መሰረት ያደረጉ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ከእነዚህም ውስጥ ወላይታ ድቻ ከ ሲዳማ ቡና ጋር ባደረገው ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱን የጨዋታ አመራሮች በተደጋጋሚ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት የቀረበ በመሆኑ እና ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥፋት አጥፍተው መቀጣታቸውን አስታውሶ ደጋፊዎቹ ከድርጊታቸው አለመማራቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ክለቡ ብር የ75,000.00 /ሰባ አምስት ሺህ/ እንዲቀጣ ወስኗል።

ከዚህ በተጨማሪ አምስተኛ የቢጫ ካርድ የተመለከቱ የስድስት ተጫዋቾች አምስት ክለቦች የገንዘብ ቅጣት ሲያስተናግዱ ተጫዋቾቹ የአንድ ጨዋታ እና የንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል። 10ኛ የቢጫ ባርድ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ቡናው ዊሊያም ሰለሞን ደግሞ ሁለት ጨዋታዎችን ሲቀጣ ተጨማሪ የገንዘብ ቅጣትም ተጥሎበታል።