ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 24ኛ ሳምንት ምርጥ 11

እንደ ሁልጊዜው ባሳለፍነው ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ ጎልተው የወጡ ተጫዋቾችን ያካተተ ቡድን ሰርተናል።

አሰላለፍ (4-3-2-1)

ግብ ጠባቂ

አቡበከር ኑራ – ባህር ዳር ከተማ

ባህር ዳር ከተማ ርቆት የነበረውን ወሳኝ ድል እንዲያገኝ በተከላካይ መስመሩ የተሰሩ ግልፅ ስህተቶች ግብ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ግብ ጠባቂ ያስፈልገው ነበር። አቡበከር ለዳዋ ሆቴሳ ተፈጥረው የነበሩ እነዚህን ዕድሎች ጨምሮ አራት ኢላማቸውን የጠበቁ ኳሶችን ማዳኑ ለጣና ሞገዶቹ የነበረው ወሳኝነት ከሚኬል ሳማኬ እና ይስሀቅ ተገኝ ልቆ እንዲመረጥ አድርጎታል።

ተከላካዮች

ጌቱ ኃይለማሪያም – ሰበታ ከተማ

የሰበታ ከተማው የቀኝ መስመር ተከላካይ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ በምርጥ ቡድናችን ውስጥ መካተት ችሏል። በዚህም ሳምንት እንዳለፉት ጨዋታዎች ሁሉ የተመጠኑ ኳሶችን ወደ አደጋ ይልክ የነበረ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ሳሙኤል ሳሊሶ ላስቆጠረው ጎል ያመቻቸው ቁልፍ ኳስ ተጠቃሽ ነው።

ወልደአማኑኤል ጌቱ – ሰበታ ከተማ

በሳምንቱ ከታዩ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች ወልደአማኑኤል አሳማኙ ተመራጭ ነበር ማለት ይቻላል። የወልቂጤን ወደ ቀኝ ያደላ ጥቃት ቡድኑ እንዲቋቋም የተጫዋቹ ጥሩ ቀን ማሳለፍ አንድ አስፈላጊ የነበረ ሲሆን ኳሶችን ከማቋረጥ ባለፈ ለማጥቃቱ በነበረው አበክቶት ከነጠቀው ኳስ ለወሳኟ ሁለተኛ ግብ ጥቃት መነሻ መሆን ችሏል።

አሸናፊ ፊዳ – አርባምንጭ ከተማ

በሳምንቱ በተደረጉ ጨዋታዎች ሁለተኛውን የመሀል ተከላካይ ማግኘት ቀላል አልነበረም። በቦታው ከባህር ዳሩ መናፍ ዐወል ጋር የተፎካከረው የአርባምንጩ ተከላካይ ጥቃቶችን ያቋረጥ ከነበረበት መንገድ ባሻገር በቀጥታ ስህተት ቡድኑን ለአደጋ ካለመጋረጡ እንዲሁም ቀዳሚዋን የአርባምንጭን ጎል ከማስቆጠሩ ጋር ተደምሮ ተማራጭ ሆኗል።

ዓለምብርሀን ይግዛው – ፋሲል ከነማ

በሳምንቱ በልዩነት የደመቀ የግራ መስመር ተከላካይ ለማግኘት ከባድ የነበረ በመሆኑ በሁለቱም በኩል መጫወት የሚችለው ዓለምብርሀንን ከቀኝ ወደ ግራ አምጥተነዋል። በወትሮው የተመጣጠነ ተሳትፎ የፋሲልን የመስመር ጥቃት ሲያግዝ የነበረው ዓለምብርሀን ወሳኟን የቡድኑን የማሸነፊያ ጎል ማመቻችት ችሏል።

አማካዮች

ተስፋዬ አለባቸው – ሀዲያ ሆሳዕና

የነብሮቹ ያለፈው ሳምንት ከባድ ሽንፈት እና የተከላካይ ክፍላቸው መጋለጥ ከተስፋዬ አለመኖር ጋር እንደሚገናኝ የዚህ ሳምንት የተጫዋቹ ብቃት እማኝ ነው። በዚህ ሳምንት ዋናውን ኃላፊነቱን በአግባቡ ከመወጣት ባለፈ ከጥልቅ የአማካይ ክፍል ይጥላቸው የነበሩ ኳሶች ለሀዲያ ሆሳዕና የተከላካይ መስመር ጀርባ ጥቃት ጥሩ እገዛ ነበራቸው።

ጋቶች ፓኖም – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የሊጉ መሪ ከነገ በስቲያ ላለበት ወሳኝ ጨዋታ ከተከታዩ ጋር ያለውን ልዩነት ጠብቆ እንዲደርስ የጋቶች ፓኖም የቅጣት ምት ጎል መቆጠር ነበረባት። ተጫዋቹ የዕለቱ የመሀል ሜዳ ፍልሚያ ለቡድኑ ከፍ ባለ ደረጃ ስጋት እንዳይሆንበትም በሁለቱ ሳጥኖች መሀል መልካም እንቅስቃሴ አድርጓል።

እንዳልካቸው መስፍን – አርባምንጭ ከተማ

የአዞዎቹ የመሀል አማካይ ቡድኑ መሀል ለመሀል የሚሰነዝራቸውን አብዛኞቹን ጥቃቶች እስከተጋጣሚ ሳጥን በማድረስ ጥሩ ተንቀሳቅሷል። በዚህም ሁለተኛውን ወሳኝ ግብ በጥሩ እይታ ማመቻቸት ሲችል የመጀመሪያውን ጎልም ከማዕዘን ምት ያደረሰው እሱ ነበር።

ኤልያስ አህመድ – አዲስ አበባ ከተማ

አዲስ አበባ እንደተለመደው ቀድሞ ግብ አስቆጥሮ ነጥብ በተጋራበት የድሬዳዋው ጨዋታ የአጥቂ አማካዩ በትጋት ተጫውቷል። በተደጋጋሚ ወደ ሳጥን እየደረሰ ዕድሎችን ከመፍጠር ባለፈ ራሱም እጅግ አደገኛ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችሎ ነበር።

አብዱልሀፊስ ቶፊቅ – ሰበታ ከተማ

የሰበታ ከተማው የአጥቂ አማካይ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ ከፍ እያለ የቡድኑ ዋነኛ ጨዋታ ቀማሪ እየሆነ ይገኛል። ይበልጥ ለግብ እየቀረበ ያለው አማካዩ አንድ ሙከራ በግብ አግዳሚ ሲመለስበት አስደናቂ በሆነ የማጥቃት ልኬት የዱሬሳ ሹቢሳን የማሸነፊያ ጎል ማመቻቸት ችሏል።

አጥቂ

ጌታነህ ከበደ – ወልቂጤ ከተማ

ጌታነህ የአጥቂ ደመነፍሱን በግልፅ ባሳየበት በዚህ ሳምንት ጨዋታ ግማሽ የሚባሉ የማጥቃት ዕድሎችን ደጋግሞ ወደ ግብ በመሞከር ነፍስ ሲዘራባቸው ነበር። ቡድኑ ድል ባይቀናውም አንድ ጎል ያስቆጠረው ጌታነህ በጨዋታው የተጋጣሚውን የተከላካይ መስመር በጠንካራ ምቶቹ ፈትኗል።

አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ – ሰበታ ከተማ

በሰንጠረዡ ግርጌ የነበረው ቡድናቸውን ለሁለተኛ ተከታታይ ድል በማብቃት አንድ ድረጃ ከፍ ያደረጉት አሰልጣኝ ብርሀን ያሳኩት ድል ከመመራት ተነስቶ የተገኘም ነበር። በሂደት ቡድኑ ላይ ካሳዩት የእንቅስቃሴ መሻሻል ባለፈ በጥሩ የሥነ ልቦና ዕድገት ወደ አሸናፊነትም እየመለሱት እነደሆነ የዚህ ሳምንት ውጤታቸው ማሳያ ነበር።

ተጠባባቂዎች

ሚኬል ሳማኬ – ፋሲል ከነማ
መናፍ ዐወል – ባህር ዳር ከተማ
ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ
ወንድምአገኝ ኃይሉ – ሀዋሳ ከተማ
ቢኒያም በላይ – መከላከያ
ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ – ፋሲል ከነማ
ሄኖክ አየለ – ድሬዳዋ ከተማ