የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 1-3 ሲዳማ ቡና

የረፋዱ ጨዋታ በሲዳማ ቡና ካሸነፈ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ አጋርተዋል።

አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ- ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው

“ጨዋታው አዝናኝ እና በጎል የታጀበ ነው። የመጀመርያው አጋማሽ የምንፈልገውን ጨርሰናል፣ ሁለተኛው የታክቲክ ለውጥ አድርገን ውጤታችንን አስጠብቀን ወጥተናል።

ስለአጥቂዎቹ ብቃት

“እጅግ በጣም የምንፈልጋቸውን ልምምድ ላይ የሰራነውን ሜዳ ላይ አሳይተውኛል። ስለዚህ አጥቂዎቼ በሚገባ ጨዋታውን ይዘውልኝ ወጥተዋል።

ስለ ጊት ጋትኩት

“እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ልጁ ከዚህ በላይ የመሄድ አቅም አለው። ለብሔራዊ ቡድን መመረጡ ከዚህ በላይ እንዲሰራ ያነቃቃዋል፣ ለቀጣይ ጨዋታዎች ትልቅ ጥቅም አለው። አቅሙ በየቀኑ እየጨመረ ነው።

ስለቀጣይ ጨዋታ

“ ቅድምም ብያለው ዋናው የሲዳማን የማሸነፍ ስሜቱን መመለስ ነው። ከአራት ጨዋታ በኋላ ነው ዲቻን ያሸነፍነው፣ በቀጣይም ቡድኑን ወደ አሸናፊነት ማስገባት ነው የምንፈልገው።”

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ስለጨዋታው

“በመጀመርያው አጋማሽ ሀያ አምስት ደቂቃዎች ብልጫዎች ነበሩን። ጎል መሆን የሚችሉ ዕድሎችን አምክነናል። እነዚህን ወደ ግብነት ቀይረን ቢሆን የጨዋታው መልክ ይቀየር ነበር። ከዚህ ውጭ በቆመ ኳስ የገባብን የተጫዋቾቻችንን መነሳሳት አውርዶብናል። ይሄን ለማስተካከል እየሞከርን በታክቲክ ስህተት ሁለተኛ ጎል ተቆጠረብን፣ ከዕረፍት በኋላ ግን በተቻለ መጠን የአጨዋወት መንገዳችንን ወደ አራት ሦስት ሦስት በመቀየር በተሻለ ተጭነን ጎል አስቆጥረን ነበር። አሁንም በተከላካዮች የጥንቃቀቄ ስህተት ጎል ተቆጥሯል። ተጫዋቾቹ ካለው ግፊት በመነሳት ውጤት ለመቀየር የተቻለውን አድርገዋል። ግን አልተሳካልንም።

ስለበቡድኑ ጫና

“ሁሉም ጋር ጫና አለ። የደጋፊው ፣ ያለንበት ደረጃ አስተማማኝ ካለመሆኑ ጋር ተተያይዞ በእግርኳስ ጫና ይኖሯል። ትልቁ ነገር ያለውን ጫና ተቋቁሞ ጨዋታዎችን መቆጣጠር የምንችልበት ጠንካራ የሥነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ ከተቻለ ጥሩ ነገር ይገጥመናል ብዬ አስባለው።”