የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሊያደርግ ነው

የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከፊቱ ያሉበት ዋልያው በሁለት ቀናት ልዩነት ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ያደርጋል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2023 በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር ለመብቃት የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ለማድረግ በዛሬው ዕለት ዝግጅት ጀምሯል። ከሜዳ ውጪ ለሚደረጉት ሁለት የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ከሚደረገው ልምምድ በተጨማሪ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ ፌዴሬሽኑ እንቅስቃሴ ላይ የነበረ ሲሆን ውጥኑ እንደተሳካ ይፋ ሆኗል።

ፌዴሬሽኑ በድረ-ገፁ ባጋራው መረጃ መሠረት ቡድኑ ከሌሶቶ ጋር የመጀመሪያውን ጨዋታ ግንቦት 20 ሲያደርግ ቀጣዩን ጨዋታ ደግሞ በተመሳሳይ ከሌሶቶ ጋር ከሁለት ቀናት በኋላ እንደሚያከናውን ተጠቁሟል። ሁለቱ ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እንደሚደረጉም ታውቋል።