ማላዊ ወሳኝ ተጫዋቿን በኢትዮጵያው ጨዋታ ታጣለች

ከነገ በስትያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ወሳኝ ጨዋታ የሚጠብቃት ማላዊ በጉዳት የምታጣቸው ተጫዋቾች ሦስት ደርሰዋል።

የአህጉሩ ትልቁ የሀገራት ውድድር በቀጣዩ ዓመት በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት የሚከናወን ሲሆን በዚሁ ውድድር ለመሳተፍ ብሔራዊ ቡድኖች የምድብ የማጣሪያ ፍልሚያቸውን ማከናወን ጀምረዋል። በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከነገ በስትያ እሁድ ሊሎንግዌ ላይ ከማላዊ ጋር የሚያደርግ ሲሆን ዛሬ ረፋድም ወደ ስፍራው አቅንቷል።

በሩማኒያዊው አሠልጣኝ ማሪዮ ማሪኒካ የሚመራው የማላዊ ብሔራዊ ቡድንም 25 ተጫዋቾችን በመለየት ዝግጅቱን እየከወነ የሚገኝ ቢሆንም የጉዳት ዜናዎች በርክተውበታል። ነበልባሎቹ በሚል ቅፅል ሥም የሚጠሩት ማላዊዎች ቀደም ብሎ አምበላቸው ሊምቢካኒ ምዛቫ እና ተከላካያቸው ማርክ ፎድያን በጉዳት ማጣታቸው ሲገለፅ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ የሌላኛውን ወሳኝ ተጫዋች ፒተር ባንዳን ግልጋሎት እንደማያገኙ የሀገሪቷ ብዙሃን መገናኛዎች የፌዴሬሽኑን የውድድር እና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጎሜዝጋኒ ዛካዛካን ዋቢ እያደረጉ እየዘገቡ ይገኛሉ።

በታንዛኒያው ሲምባ የሚጫወተው የ21 ዓመቱ አማካይ ከሦስት ቀናት በፊት የቡድን አጋሮቹ በፊትነስ ስቱዲዮ አሬና 6 የጂምናዚየም ሥራዎችን እየሰሩ በነበሩበት ሰዓት ተቀላቅሏቸው ልምምድ ሲሰራ የነበረ ሲሆን በልምምድ ላይ ጉዳት በማስተናገዱ የእሁዱ ጨዋታ እንደሚያልፈው ተመላክቷል።