ቅድመ ዳሰሳ | የ27ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

በደረጃ ሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ ትልቅ ትርጉም የሚኖራቸውን የነገ የሊጉ ሦስት ጨዋታዎች እንደሚከተለው ቃኝተናል።

አዳማ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

በዋንጫ ፉክክሩም ሆነ በወራጅነት ትንቅንቁ ላይ የሚገኙ ክለቦች እኩል በትኩረት የሚያዩት የነገ ረፋድ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል። ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥቦች ብቻ ርቆ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አዳማ ከተማ ከ10 ጨዋታዎች በኋላ በ25ኛ ሳምንት ድል ቢያደርግም ባሳለፍነው ሳምንት እየመራ ለኢትዮጵያ ቡና ሦስት ነጥብ አስረክቧል። ዋና አሠልጣኙ ፋሲል ተካልኝ ከመንበሩ ተነስተው ምክትሉ ይታገሱ እንዳለ ቦታውን ከያዙ በኋላ በተደረገው የሰበታ ጨዋታ ሁሉንም የጨዋታ ምዕራፎች በፍላጎት በማከናወን ረገድ የተሻለ ብርታት የነበረው ቡድኑ በቡናው ፍልሚያ አጀማመሩ ጥሩ ሆኖ ከግብ ጋር ገና በጊዜ ቢገናኝም ከግማሽ ሰዓት በኋላ እየወረደ እየወረደ መጥቶ ሁለት ጎሎች አስተናግዷል። በጨዋታው ቡድኑ የቡናን የኳስ ቅብብል በመሐል ሜዳው አካባቢ አፍኖ በማቋረጥ የግብ ምንጭ ለማድረግ ተንቀሳቅሶ ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት ዕድሎችን ቢያገኝም በደካማ አጨራረስ የግቡን መረብ ማግኘት አልቻለም። ምናልባት በነገው ጨዋታ እነዛ የጠሩ ዕድሎች ላይደጋገሙ ስለሚችሉ የሚገኙትን መጠቀም ጥያቄ የማይነሳበት ጉዳይ ነው።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት በርከት ያሉ ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ቀዳሚ የሆነው ፋሲል ከነማ የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር በእግር እየተከተለ አንገቱ ላይ እየተነፈሰበት ይገኛል። በዚህ ሳምንት ግን ጊዮርጊስ ማሸነፉ በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ለተዐምር የተጠጋ ውጤት እየጠበቀ ውድድሩን እንዲቀጥል ያደርገዋል። በእጁ ያለውን ዕድል እየተጠቀመ የበላዩን ውጤት በአፅንኦት ከመከታተል ውጪም አማራጭ የለም። የሆነው ሆኖ ባሳለፍነው ሳምንት በተሟላ ሁኔታ ልምምድ ሳይሰሩ ወደ ሜዳ በገቡት ሰበታ ከተማዎች ተፈትኖ የነበረው ፋሲል ነገ ደግሞ በሌላኛው ላለመውረድ እየታገለ በሚገኘው አዳማ ከተማ ሥራዎች ይበዙበታል። በእንቅስቃሴ ደረጃ ግን አሁንም የመውረድ ምልክት ባይታይበትም ስብስቡ የበላዩን መከተል ከሚፈጥርበት ጫና ራሱን ነፃ አድርጎ የሚፈጠሩ ዕድሎችን መጠቀም ይገባዋል። በሰበታው ጨዋታም በድምሩ 21 ሙከራዎች ተደርገው አንዱን ብቻ ነው በግብ በረቶቹ መሐከል ያሳለፉት። ምንም እንኳን አዳማ ወሳኝ ተከላካዮቹን በነገው ጨዋታ ባያሰልፍም እንደ ቡድን ክፍተት የማይሰጥ ስለሆነ ሊቸገሩ ይችላሉ። በተቃራኒውም በፈጣኖቹ አጥቂዎቹ መልሶ ማጥቃቶችን ሊያዘወትር ስለሚችል ጥንቃቄ ግድ ነው።

በፋሲል ከነማ ቤት ምንም የጉዳት እና ቅጣት ዜና የለም። አዳማ ከተማ በበኩሉ ዳዋ ሁቴሳ እና ሚሊዮን ሰለሞን አሁንም ቅጣታቸው ያልጨረሱ ሲሆን ሌላኛውም ወሳኝ ተጫዋች ቶማስ ሰምረቱም የእነርሱን ጎራ ተቀላቅሎ ጨዋታው ላይ አይሳተፍም።

የጨዋታው ዳኞች – ማኑኤ ወልደፃዲቅ፣ ዳንኤል ጥበቡ፣ ትንሳኤ ፈለቀ፣ ተካልም ለማ

ተጨማሪ ዳኞች – ሸዋንግዛው ከበደ እና ሙሉነህ በዳዳ

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን አስር ጊዜ ተገናኝተዋል። በውጤቶቹ 5 ጊዜ አቻ ሲለያዩ 3 ጊዜ ፋሲል 2 ጊዜ ደግሞ አዳማ አሸንፏል። ዐፄዎቹ 10 ግቦችን ሲያስቆጥሩ አዳማዎች ደግሞ 7 አግብተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ


አዳማ ከተማ (4-3-3)

ሴኩምባ ካማራ

ጀሚል ያዕቆብ – ኢዮብ ማቲዮስ – አዲስ ተስፋዬ – ደስታ ዮሐንስ

አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው

አቡበከር ወንድሙ – አብዲሳ ጀማል – አሜ መሐመድ

ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)

ሚኬል ሳማኪ

ሰዒድ ሀሰን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ይሁን እንዳሻው

ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው- በረከት ደስታ

ሙጂብ ቃሲም

ሰበታ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በሚቋረጥበት ጊዜ ተጫዋቾቹን በተሟላ ሁኔታ ሳያገኝ የቀረው ሰበታ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት በጨዋታ ቀን ከያሉበት የተሰባሰቡ ተጫዋቾቹን መልበሻ ክፍል አግኝቶ ወደ ሜዳ ቢያስገባም የወቅቱን የሊጉን አሸናፊ ፋሲል ከነማ የፈተነበት መንገድ ከብዙዎች አድናቆት እንዲቸረው ያደረገ ነበር። በተለይ አብዝቶ ሲተገበር የዐምሮ እና የአካል መዛል የሚያስከትለው የኳስ ውጪ እንቅስቃሴን በተቻለ መጠን በጥሩ ሁኔታ ለመተግበር እና በመልሶ ማጥቃቶች አንዳች ነገር ለመተግበር ሲያደርጉት የነበረው ጥረት መልካም ነበር። ጥቂት ቀናት ቢሆንም አሠልጣኝ ብርሃን ደበሌ ስብስባቸውን በተሟላ ሁኔታ ማግኘታቸውን ተከትሎ ነገ ተዐምር የሚፈልገውን ሥራ ምናልባት ለመጨረሻ አንድ ብለው ይጀምራሉ። ይህ ቢሆንም ግን 21 ቀኑን ቡድኑ ከልምምድ መራቁ ለዚህ ጨዋታ ዝግጅትም ከፍተኛ እንቅፋት ሆኗል። የሆነው ሆኖ ‘የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም’ በሚለው ብሂል ማጥቃት ላይ የተንተራሰ አጨዋወት ተከትለው ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ ይታሰባል። ይህንን ደፍሮ ለማድረግ ደግሞ በቀጥተኛም ሆነ ከኳስ ጋር ለሚደረግ እንቅስቃሴ የሚመቹ ተጫዋቾች ስላሉ ቡድኑ ሊጠቀም ይችላል።

ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ በማሸነፍ በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታዎች ራሱን የመውረድ ስጋት ውስጥ እየከተተ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና የደረጃ ሰንጠረዡን አካፋይ ለመያዝ እና ከስጋቱ ለመላቀቅ ነገ እንደሚታትር ይገመታል። ከወጥነት ጋር በተያያዘ ክፍተቶች ያሉበት ቡድኑ የባህር ዳር ስታዲየም ውጤት እየቀናው ባይመስልም በእንቅስቃሴ ደረጃ ግን ለክፉ የሚሰጥ ነገር የለውም። ከዛ ከድሬዳዋ ጨዋታ ውጪም ብዙም ብልጫ በተጋጣሚ ሲወሰድበት አይታይም። ነገርግን በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ያለበት ችግር ከጨዋታዎቹ አንዳች ነገር ይዞ እንዳይወጣ እያረገው ይመስላል። በተለይ ደግሞ የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ግብነት የመቀየር አይናፋርነት በትልቁ ይታይበታል። ባሳለፍነው ሳምንት እንኳን ከፋሲል ከነማ እና መከላከያ ጋር በጣምራ በርካራ ሙከራዎችን (21) በማድረግ አንደኛ ሆኖ የተቀመጠው ቡድኑ አንድም ግብ ሳያስቆጥር መውጣቱ ሲታወስ ጎል ፊት ያለውን ዱልዱምነት ይመሰከራል። ምናልባት ነገ በሊጉ በርካታ ግቦችን በማስተናገድ ደረጃውን የሚመራው ሰበታን ማግኘታቸው ግን በድግግሞሽ ክልሉን እንዲጎበኙ ሊያደርግ ይችላል።

ሰበታ ከተማ ቅጣቱን ካልጨረሰው በረከት ሳሙኤል በተጨማሪ ገዛኸኝ ባልጉዳ እና ለዓለም ብርሀኑን በጉዳት ሲያጣ ዛሬ ቡድኑን የተቀላቀለው ዘካሪያስ ፍቅሬም ለነገው ጨዋታ አይደርስለትም። ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ተስፋዬ አለባቸውን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ ፍሬዘር ካሣ ግን ቅጣቱን ባለመጨረሱ ከጨዋታው ውጪ ነው።

የጨዋታው ዳኞች – አባይነህ ሙላት፣ ተመስገን ሳሙኤል፣ አበራ አብርደው፣ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ

ተጨማሪ ዳኞች – ትግል ግዛው እና ሀብተወልድ ካሣ

እርስ በርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ እስካሁን በሦስት ጨዋታዎች የተገናኙ ሲሆን አንዴ አቻ ተለያይተው አንድ አንድ ጊዜ ደግሞ ተሸናንፈዋል። በተመጣጣኝ ፉክክራቸው እንዲሁ ሦስት ሦስት ግቦች አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ


ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ሰለሞን ደምሴ

ጌቱ ኃይለማሪያም – ወልደአማኑኤል ጌቱ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

በኃይሉ ግርማ – ጋብርኤል አህመድ

ሳሙኤል ሳሊሶ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ዱሬሳ ሹቢሳ

ዴሪክ ኒስባምቢ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ብርሃኑ በቀለ – ግርማ በቀለ – ቃለአብ ውብሸት – እያሱ ታምሩ

ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን

ሀብታሙ ታደሠ – ባዬ ገዛኸኝ – ዑመድ ዑኩሪ

ኢትዮጵያ ቡና ከ አዲስ አበባ ከተማ

ቀስ በቀስ የሊጉን ደረጃ ሰንጠረዥ ሽቅብ እየወጣ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛል። በተለይ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ቀድሞ ግብ ተቆጥሮበት ወደ ጨዋታው በትዕግስት የተመለሰበት እና ሦስት ነጥብ ይዞ የወጣበት መንገድ አስገራሚ ነበር። እርግጥ ቡድኑ አሁንም የተዐምረኛው አቡበከር ናስር ጥገኛ ቢሆንም መጫወት በሚፈልገው መንገድ ተጫዋቹን ለማጉላት የሚሄድበት ርቀት እና ክፍተቶችን በማየት አደጋ የሚፈጥርበት ሂደት ለተጋጣሚ ተጫዋቾች ፈተና ናቸው። ነገም በዚሁ መንገድ እንደሚጫወት ቢታሰብም እንደ እርሱ ከኳስ ጋር ማሳለፍ የሚሻ ቡድን ስለሚገጥም የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ለማግኘት መበርታት አለበት። እንደጠቀስነው አቡበከር ግን በቡና በኩል የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ይሆናል ብሎ መናገር ቀጣፊ የሚያስብል አይመስልም። ይህ በእንዲህ አንዳለ ግን ሽግግሮች ላይ አደገኛ የሆኑትን የአዲስ አበባ ተጫዋቾች መቆጣጠር ወሳኝ መሆን እንዳለበት መጠቀስ ይኖርበታል።

በ26ኛ ሳምንይ እንደ ሰበታ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ከደሞዝ ጋር በተገናኘ የተሟላ ልምምድ ሳይሰሩ ወደ ሜዳ ገብተው ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር የታረቁበትን ውጤት ይዘው የወጡት አዲስ አበባዎች ዘለግ ላለ ጊዜ ከቆዩበት አስጊ ቀጠና ለመውጣት ነገ ትክክለኛው ጊዜ ይመስላል። ባሳለፍነው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር ሲጫወት ጨዋታን ለማሸነፍ ግብ ማግባት ብቻ በቂ እንዳልሆነ የተማረ የሚመስለው ቡድኑ ሰከን ብሎ በአራቱም የጨዋታ ሂደቶች ብልጫ እንዳይወሰድበት ጥሮ ነበር። ሙሉ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ውዷን ሦስት ነጥብ ያስገኘች ግብ አግኝቷል። ይህ ነገ ትልቅ ተነሳሽነት እንደሚፈጥርለት ሲታሰብ ከበላዮቹ የሚገኙት ክለቦች ነጥብ መጣል እና መሸነፍ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ብርታት ሰጪ ምክንያት ይሆንለታል ተብሎ ይታሰባል። አዲስ አበባ በእንቅስቃሴ ደረጃ አብዛኞቹ ቡናን የሚገጥሙ ቡድኖች እንደሚያደርጉት የቅብብል ስህተቶችን በማነፍነፍ እንደሚንቀሳቀስ ሲገመት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ሲወሰድበት ሪችሞንድን ያማከለ እንዲሁም የመስመር አጥቂዎቹን ፍጥነት የተንተራሰ የግብ ፍለጋ ሂደት እንደሚከተል ይገመታል።

የሳምንቱን የመዝጊያ ጨዋታ የሚያከናውኑት ሁለቱ የመዲናይቱ ክለቦች ኢትዮጵያ ቡና እና አዲስ አበባ ከተማ ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና እንደሌለባቸው ተጠቁሟል።

የጨዋታው ዳኞች – ቴዎድሮስ ምትኩ፣ ሸዋንግዛው ተባበል፣ ወጋየሁ አየለ፣ አዳነ ወርቁ

ተጨማሪ ዳኞች – ዘሪሁን ኪዳኔ እና ለዓለም ዋሲሁን

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱን ቡድኖች ከዚህ ቀደም ያገናኙት ሦስት ጨዋታዎች በሙሉ አራት ግቦችን ባስመዘገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የበላይነት ሲጠናቀቁ አዲስ አበባዎች እስካሁን ድልም ሆነ ግብ የላቸውም።

ግምታዊ አሰላለፍ


ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

በረከት አማረ

ኃይሌ ገብረተንሳይ – አበበ ጥላሁን – ወንድሜነህ ደረጄ – አስራት ቱንጆ

አማኑኤል ዮሐንስ – አብነት ደምሴ – ታፈሠ ሰለሞን

አቤል እንዳለ – አቡበከር ናስር – አላዛር ሽመልስ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ልመነህ ታደሰ – አዩብ በቀታ – ሮቤል ግርማ

ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሩባኑ – ኤሊያስ አህመድ

እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን