ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ28ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ28ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን ያካተተ የሳምንቱ የሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ 11 ይህንን ይመስላል።

አስተላለፍ : 4-2-3-1

ግብ ጠባቂ

ፍሬው ጌታሁን – ድሬዳዋ ከተማ

መሀመድ ሙንታሪ ፣ መሳይ አያኖ እና መክብብ ደገፉ ድንቅ አቋም ባሳዩነት የጨዋታ ሳምንት ፍሬው የተሻለ ነጥብ አግኝቶ ተመርጧል። ግብ ጠባቂው አምስት ግብ የሚሆኑ ኳሶችን ያዳነበት መንገድ ድሬዳዋ ከተማን በሰፊ ግቦች ከመረታት የታደገ ነበር።

ተከላካዮች

ሱሌይማን ሀሚድ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ቡድኑ ነጥብ ይጋራ እንጂ በቀላሉ ክፍተት አልሰጥ ያለውን ተጋጣሚውን ለመፈተን የሱለይማን ተሻጋሪ ኳሶች ጥሩ እገዛ አድርገዋል። ከእነዚህም መካከል አንደኛው የተመጠነው ኳሱ በአማኑኤል ገብረሚካኤል አማካይነት ወደ ግብነት ተለውጧል።

አስቻለው ታመነ – ፋሲል ከነማ

በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲል በሀዋሳ ከተማ በተፈተነባቸው ደቂቃዎች በአንድ ለአንድ ግንኙነት ንቁ የነበረው አስቻለው ኃላፊነቱን ተወጥቷል። ከከድር ኩሊባሊ ጋር የፈጠሩት ጥምረት የሀዋሳ የኳስ ንክኪዎች ወዳ አደገኛ ሙከራነት እንዳይቀየሩ ወሳኝ ነበር።

በርናንድ ኦቼንግ – አርባምንጭ ከተማ

የአርባምንጭ ከተማ የመከላከል ጥንካሬ በ28ኛው ሳምንትም ቀጥሎ ታይቷል። የአዞዎቹ የአሸናፊ እና ኦቼንግ ጥምረት በወትሮው ጥንካሬው ላይ ተገኝቶ የታየ ሲሆን በርናንድ ኦቼንግ በተለይም አቡበከር ናስር በምቾት የመጨረሻ ውሳኔዎችን እንዳይወስን በማድረግ ቡድኑን ከግቦች መታደግ ችሏል።

አህመድ ረሺድ – ባህር ዳር ከተማ

የግራ መስመር ተከላካዩ ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን በጠባብ ውጤት እንዲያሸንፍ ምክንያት ከነበሩ ተጫዋቾች ዋነኛው ነበር። በዚህም ብቸኛዋን የመናፍ ዐወልን ጎል በግሩም ሁኔታ ማመቻቸት ሲችል የማማዱ ሲዲቤ ግብ ለመሆን የቀረበን የግንባር ኳስ ከግቡ መስመር ላይ በማውጣት ቀጥተኛ አበርክቶ አድርጓል።

አማካዮች

ይሁን እንዳሻው – ፋሲል ከነማ

በቦታው አሁን ላይ ካሉ አማካዮች ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደበው ይሁን በሀዋሳው ጨዋታ ድንቅ ነበር። የሀዋሳ የአማካይ ክፍል አቅም እንዲያጣ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት በሳል ውሳኔዎችን በማሳለፍ ጥቃቶችን ሲያቋርጥ ከፊቱ ካሉ አማካዮች ጋር ጥሩ ግንኙነትን በመፍጠር ማጥቃቱንም ሲያስጀምር ተስተውሏል።

አበባየሁ አጪሶ – ወላይታ ድቻ

ራሱን በጦና ንቦቹ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ማደላደል የቻለው ወጣቱ አማካይ በጅማው ጨዋታ ከመሀል ሜዳ እየተነሳ ማጥቃቱን ያግዝ የነበረበት ታታሪነት አስገራሚ ነበር። በዚህም ቡድኑን ወደ አቻነት ያመጣች ወሳኝ ግብ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በማደራጀት እና ሙከራዎችን በማድረግም ንቁ የጨዋታ ዕለትን አሳልፏል።

እንዳልካቸው መስፍን – አርባምንጭ ከተማ

የአዞዎቹ አማካይ ከሳምንት ሳምንት ማስገረሙን ሲቀጥል እንዳልካቸው ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ በቡድናችን ውስጥ ተካቷል። በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጪ ታታሪነቱ ያልተለየው ወጣቱ አማካይ የሰሞኑ የማጥቃት ድርሻው በዚህ ሳምንትም ከፍ ብሎ ሌላ ግብ የሆነ ኳስ ሊያመቻች ችሏል።

ሱራፌል ዳኛቸው – ፋሲል ከነማ

ሜዳ ላይ ሙሉ የጨዋታ ደቂቃዎችን አያሳልፍ እንጂ ሱራፌል የሳምንቱን ምርጥ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል። በዚህም ከመሀል ሜዳ የሚልካቸው የመጨረሻ ኳሶች የፋሲል ከነማ ዋነኛ የማጥቃት መነሻዎች የነበሩ ሲሆን የሙጂብ ቃሲምን ብቻኛ ግብም በዚሁ መንገድ እና በአስገራሚ ልኬት ማመቻቸት ችሏል።

ፍፁም ጥላሁን – አዲስ አበባ ከተማ

ከቡድን አጋሩ እንዳለ ከበደ ጋር በቦታው ተፎካካሪ የነበረው ፍፁም በሳምንቱ ምርጥ 11 ውስጥ ከግራ እንዲነሳ አድርገናል። ከወትሮው በተለየ ጥሩ የቡድን ተጫዋች ሆኖ በታየበት የሰበታው ጨዋታ የተሳካ የአጨራረስ ብቃቱን በማሳየት ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል።

አጥቂ

ሙጂብ ቃሲም – ፋሲል ከነማ

ግዙፉ አጥቂ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ተመራጫችን ሆኗል። ሁለት ሁለት ግቦች ካሏቸው ሪችሞንድ ኦዶንጎ እና ፍፁም ገብረማሪያም ጋር የተፎካከረው ሙጂብ አንድ ግብ ያስቆጥር እንጂ ከጨዋታው ክብደት እና ከግቧ ዋጋ አንፃር እንዲሁም በመጨረሻ ወደ ተከላካይ አማካይነት በመቀየር በሌላኛው የግቡ ፅንፍ ካበረከተው አስተዋፅዖ መነሻነት ልንመርጠው ችለናል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ

የአርባምንጭ ከተማው አሰልጣኝ የምርጥ 11 ደንበኛ ሆነዋል። አቡበከር ናስርን በድል ለመሸኘት ፍላጎት የነበረው ኢትዮጵያ ቡናን በመቆጣጠር ቡድኑ ባለው የራሱ ጥንካሬ መነሻነት ያሸነፈበት መንገድ ከቅያሪዎች አጠቃቀም እና ከጨዋታ ክብደት አንፃር በሳምንቱ ድል ካስመዘገቡ ሌሎች አሰልጣኞች ጋር ሲነፃፀሩ አሰልጣኝ መሳይ ተመራጭ እንዲሆኑ ምክንያት ሆነዋል።

ተጠባባቂዎች

መሐመድ ሙንታሪ – ሀዋሳ ከተማ
ፍሬዘር ካሳ – ሀዲያ ሆሳዕና
መናፍ ዐወል – ባህር ዳር ከተማ
ሀብታሙ ንጉሴ – ወላይታ ድቻ
ፍፁም ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ
እንዳለ ከበደ – አዲስ አበባ ከተማ
ሪችሞንድ ኦዶንጎ – አዲስ አበባ ከተማ
ፍፁም ገብረማሪያም – ሰበታ ከተማ