ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

ሊጠናቀቅ የአንድ ጨዋታ ሳምንት ዕድሜ በቀረው የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ክለብ ነክ ጉዳዮች በተከታዩ ፅሁፋችን ቀርበዋል።

👉 የዋንጫው ፉክክር ወደ መጨረሻው ዕለት አምርቷል

አሸናፊው እስካሁን ባለየለበት የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አንገት ለአንገት ተናንንቀዋል። በጨዋታ ሳምንቱ ሁለቱም ቡድኖች ነጥብ ሊጥሉ ይችሉባቸዋል በተባሉባቸው የኢትዮጵያ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታዎች ሁለቱም ወሳኙን ሦስት ነጥብ ከመውሰድ የከለከላቸው አልነበረም።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከወትሮው በተለየ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀድመው መጫወት የቻሉት ፋሲል ከነማዎች ኢትዮጵያ ቡና ከኳሱ ጋር የተሻለ ጊዜ ማሳለፍ በቻሉበት ጨዋታ ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮቻቸው ተጋጣሚያቸውን አቅም ማሳጣት ችለዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥር ወቅት ወደ መሀል ሜዳ በተጠጋ መልኩ ከሚኖራቸው የተዘረዘረ አቋቋም መነሻነት ፋሲሎች የሚነጥቋቸውን ኳሶች በፍጥነት ከተከላካዮች ጀርባ ሯጮችን በማስገባት በጨዋታው ልዩነት ፈጥረዋል። በዚህም ፋሲል ከነማዎች ኢትዮጵያ ቡናን 3-0 በመርታት ቅዱስ ጊዮርጊስ እስኪጫወት ድረስ ከ20 የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ሊጉን መምራት የቻሉበትንም አጋጣሚም መፍጠር ችለው ነበር።

አስከትለው ጨዋታቸውን ያደረጉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከአርባምንጭ ከተማ እጅግ ከፍተኛ ፈተና ገጥሟቸው ነበር። ምስጋና ከነዓን ማርክነህ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላስቆጠራት ግብ ይግባና ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቀናቸውን ለመንጠቅ አኮብኩበው ከነበሩት አዞዎቹ ሙሉ ሦስት ነጥብ በማሳካት መሪነታቸውን ዳግም መረከብ ችለዋል። በመከላከሉ ረገድ ጠጣር የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች በማጥቃቱም እጅግ አደገኛ የነበሩ አጋጣሚዎችን እንዲሁ ሲፈጥሩ ተመልክተናል። በዚህም በከፍተኛ ዝናብ ታጅቦ በውጥረት ውስጥ በተካሄደው የሁለኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኟትን መሪነት ለማስጠበቅ ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት በመጨረሻም ወሳኙን ሦስት ነጥብ አስገኝቶላቸዋል። ይህን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አሁንም ሊጉን በአንድ ነጥብ ልዩነት መምራት ቀጥለዋል። ይህም የመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።

የሊጉ ዋንጫ ፉክክር ከዚህ ቀደም በተለያዩ አጋጣሚዎች ቡድኖች አንገት ለአንገት ተያይዘው ወደ መጨረሻው የጨዋታ ዕለት ያመሩባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ውድድሩ በአዲስ ፎርማት ከጀመረ ወዲህ መሰል አጋጣሚዎች በአምስት የተለያዩ የውድድር ዓመታት የተፈጠሩ ሲሆን የዘንድሮው የፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ፉክክር በመጨረሻ አራት የውድድር ዘመናት ለሦስተኛ ጊዜ በአጠቃላይ ደግሞ ለስድስተኛ ጊዜ የዋንጫ ፉክክሩ ወደ መጨረሻ ዕለት ያመራበትን አጋጣሚ ፈጥሯል።

ለመጨረሻ ጊዜ በታዘብነው የመዝጊያ ቀን ፍልሚያ መቐለ 70 እንደርታ አሸናፊ በነበረበት የ2011 የውድድር ዘመን ሦስት ቡድኖች ማለትም መቐለ 70 እንደርታ (56 ነጥብ) ፣ ፋሲል ከነማ (56 ነጥብ) እና ሲዳማ ቡና (55 ነጥብ) ሆነው ወደ መጨረሻ ጨዋታ ሲያመሩ መጠኑ ይለያይ እንጂ ሦስቱም ቡድኖች ሊጉን የማሸነፍ ዕድል የነበራቸው ሲሆን ፤ በዚህም ፋሲል ከነማ ከስሑል ሽረ ጋር አንድ አቻ ሲለያይ በተመሳሳይ ሲዳማ ቡና ደግሞ ወልዋሎ ዓ/ዩ መርታት ቢችልም መቐለ 70 እንደርታ ድሬዳዋ ከተማን 2-1 በመርታት በ59 ነጥብ ሊጉን ማሸነፉ አይዘነጋም።

በመሆኑም ከቀናት በኋላ በሚደረገው የመጨረሻ 90 ደቂቃዎች ፍልሚያ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ካለው የአንድ ነጥብ ልዩነት አንፃር ዋንጫው ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ፋሲል ከነማ የማምራት ዕድሉ ክፍት ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሂሳባዊ ስሌት አንፃር ሰፊ ዕድልን የያዘ ቢመስልም ፋሲል ከነማዎች ግን የቅዱስ ጊዮርጊስን ነጥብ መጣልም ሆነ መሸነፍ ላይ የተንጠለጠለውን ዕድላቸው ይዘው ወደ መጨረሻዎቹ 90 ደቂቃዎች ያመራሉ።

ፈረሰኞቹ ከአራት የውድድር ዘመናት በኋላ የሊጉን ክብር ይቀዳጁ ይሆን ወይንስ ዐፄዎቹ ደግሞ ለሁለተኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን የሊጉን ዋንጫ ያነሳሉ የሚለው ጥያቄ በመጪው አርብ በተመሳሳይ ሰዓት በሚደረጉ ጨዋታዎች እልባት ሚያገኝ ይሆናል።

👉 ሦስተኛው ወራጅ ቡድን ማን ይሆን ?

ሁለቱ ወራጆች አስቀድመው በታወቁበት ሊጉ ቀጣዩ ‘ሦስተኛው ወራጅ ቡድን ማን ሊሆን ይችላል ?’ የሚለው ጉዳይ በመጨረሻው ጨዋታ የሚወሰን ይሆናል። ድሬዳዋ ከተማዎች በንፅፅር የጠበበ ዕድል ቢኖራቸውም አዲስ አበባ እና አዳማም በተመሳሳይ ስጋቱ ያጠላባቸው ቡድኖች ናቸው።

በ29ኛ የጨዋታ ሳምንት ሦስተኛውን ወራጅ ቡድን ይጠቁማል በሚል በከፍተኛ ጉጉት የተጠበቀው ጨዋታ የአዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ የነበረ ሲሆን በአንድ አቻ መጠናቀቁን ተከትሎ በሰንጠረዡ ግርጌ ያለው ነገር ይበልጥ ተሳስሯል። ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ባስመዘገቡት አዎንታዊ ውጤት ለረጅም ጊዜያት ከተጣበቁበት 14ኛ ደረጃ መላቀቅ ችለው የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በዚህ ሳምንት በሲዳማ ቡና መሸነፋቸውን ተከትሎ ቆይታቸው ዳግም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ሲያስተናግድ ፍፁም ‘አዲስ አበባን’ የማይመስል ቡድንን ተመልከተናል። ለወትሮው ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የማይቸገረው ነገር ግን በተጫዋቾች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ሲቸገር እናስተውል የነበረው ቡድኑ በሲዳማ ቡናው ጨዋታ ከሳጥን ውጪ ከሚደረጉ ሙከራዎች ባለፈ እንደቀድሞው ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገረበት ጨዋታ ነበር። በዚህኛው ጨዋታ በአምስት ቢጫ ምክንያት በሊጉ ለከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየተፎካከረ የሚገኘውን ጋናዊውን አጥቂያቸው ሪችሞንድ ኦዶንጎን ሳይዙ የገቡ ሲሆን በተመሳሳይ በቀጣይ የመጨረሻ የሊጉ ጨዋታ ደግሞ ሌላኛውን ከሰሞኑ አስደናቂ የግብ ማግባት ጉዞ ላይ የሚገኘውን ፍፁም ጥላሁንን አገልግሎት አያገኙም። ምንም እንኳን የቡድኑ አሰልጣኝ በቀጣይ ጨዋታ አሸንፈው በሊጉ እንደሚቆዩ በእርግጠኝነት ቢናገሩም በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ለሊጉ ክብር እያኮበኮበ ከሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እንደመጫወታቸው በሊጉ የመቆየታቸው ጉዳይ ከእነሱ ውጤት ይልቅ በሌሎች መሸነፍ ላይም የተመሰረተ ይመስላል።

በተመሳሳይ በጨዋታ ሳምንቱ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ በነበረው ጨዋታ አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያደረጉት እና በከፍተኛ ውጥረት የታጀበው ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በጨዋታው የተሻለ አጀማመርን አድርገው ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ገና በማለዳው ማግኘት ችለው የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ከግቧ በኋላ ግን ይህን አጀማመር ከማስቀጠል ይልቅ በሂደት ጥንቃቄ ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ተከትሎ አዳማ ከተማዎች ይበልጥ ወደ ጨዋታው እንዲመለሱ ዕድል የፈጠሩላቸው ሲሆን በዚህም አዳማ ከተማዎች አቻ መሆን ችለዋል። በሁለተኛው አጋማሽ በዝናባማው የአየር ሁኔታ የጨዋታው ሂደት ይበልጥ ጉልበት መፈለጉን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች ይበልጥ ሲቸገሩ በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች የተሻሉ ሆነው ተመልክተናል። ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች ካለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት በኋላ የመጀመሪያ ነጥባቸውን ሲያሳኩ በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ደግሞ ለሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

ያልተጠበቁ ሂደቶች ሊያስመለክቱን ይችላሉ ተብሎ በሚጠበቁት የ30ኛ የጨዋታ ሳምንት መርሐግብሮች ከሦስቱ ቡድኖች አንዱን በቀጣዩ ዓመት በሊጉ እንዳንመለከት የሚያደርጉ ይሆናሉ ተብሎ በጉጉት ይጠበቃል። የጠበበ ዕድል ያላቸው የሚመስሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ተዓምር ሰርተው በሊጉ ይቆዩ ይሆን ወይንስ የተሻለ ተስፋን ይዘው ወደ መጨረሻው ጨዋታ ያመሩት አዲስ አበባ እና አዳማ ሳይጠበቁ ከሊጉ ይወርዱ ይሆን ለሚለው ጥያቄ በመጪው አርብ ምላሽ ያገኛል። ሦስቱን ቡድኖች እና የዋንጫ ፉክክሩን የሚለዩት ሦስት ጨዋታዎች ኡርብ 04:00 ላይ እንሰሚደረጉም ታውቋል።

👉 ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም የተሳነው ባህር ዳር ከተማ

በ29ኛ የጨዋታ ሳምንት ሰበታ ከተማን የገጠሙት ባህር ዳር ከተማዎች ፍፁም የበላይ በነበሩበት ጨዋታ ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ ተለያይተዋል።

በሊጉ ቆይታቸውን ለማረጋገጥ ማሸነፍ የግድ ይላቸው የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት እጅግ ወሳኝ በነበረው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ረተው እንደመምጣታቸው ይህን የአሸናፊነት ስሜት አስቀጥለው ከሰበታ ከተማ ሙሉ ሦስት ነጥብ በመውሰድ በሊጉ መቆየታቸውን ያረጋግጣሉ ተብለው በተጠበቁበት ጨዋታ ፍፁም የሚባል በላይነትን ወስደው መጫወት ቢችሉም ወሳኙን ነጥብ ይዘው መውጣት ሳይችሉ ቀርተዋል። በጨዋታው በአጠቃላይ ጨዋታው 58% የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበረው ቡድኑ በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተሻለ የጨዋታ ቁጥጥር ተጋጣሚያቸው ላይ በመውሰድ ተጋጣሚያቸውን ወደ ሳጥኑ ገፍተው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል።

በጨዋታው የበላይ የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች በድምሩ 22 የግብ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 9 የሚሆኑት ዒላማቸውን የጠበቁ ነበሩ። በአጠቃላይ በጨዋታው ቡድኑ በተለይ መሀል ለመሀል በሚደረጉ ጥቃቶች የተሻለ የነበረ ሲሆን ከአጠቃላይ የማጥቃት ሂደቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከዚሁ አካባቢ መነሻቸውን ያደረጉ የነበረ ቢሆንም ግን ያገኛቸውን ዕድሎች ወደ ግብ በመቀየር ረገድ ውስንነቶች እንደነበሩባቸው ተመልክተናል።

በጨዋታው በመልሶ ማጥቃት ባህር ዳሮች ትተውት የሚሄዱትን የሜዳ ክፍል ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ሰበታ ከተማዎች በ16ኛ ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ አስቀድመው መምራት ቢችሉም ባህር ዳር ከተማዎች ከዕረፍት መልስ በ52ኛው ደቂቃ በተቆጠረ ግብ አቻ መሆን ችለዋል። በ65ኛው ደቂቃ በረከት ሳሙኤል በቀይ ካርድ መወገዱን ተከትሎ የመጨረሻዎቹን 25 ደቂቃዎች አንድ ተጨማሪ ሰው ይዘው የተጫወቱት ባህር ዳር ከተማዎች ጨዋታውን ለማሸነፍ የምትረዳ ተጨማሪ ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

አሁንም ቢሆን በ34 ነጥብ በነበሩበት 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች በድሬዳዋ እና አዳማ ነጥብ መጋራት የተነሳ በሊጉ መቆየታቸውን አረጋግጠዋል።

👉 ሰራተኞቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

በሊጉ ለመቆየት ከመጨረሻ ሁለት መርሐግብሮች በአንዱ ማሸነፍ የግድ ይላቸው የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በ29ኛ ሳምንት መውረዳቸውን ያረጋገጡትን ጅማ አባ ጅፋሮችን በመርታት ቆይታቸውን አረጋግጠዋል።

በጨዋታው ከሦስት ጨዋታዎች ቅጣት መልስ የአምበላቸው ጌታነህ ከበደን ያገኙት ወልቂጤዎች በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ እጅግ አስደናቂ አጋማሽን ማሳለፍ ችለዋል። ሁለት ግቦችን ማስቆጠር በቻሉበት የመጀመሪያ አጋማሽ የቡድኑ ማጥቃት ይበልጥ አስፈሪነትን ተላብሶ በተመለከትንበት አጋማሽ ቡድኑ ከወትሮው በተሻለ በርከት ያሉ ዕድሎችን የፈጠሩበት ነበር።

ምንም እንኳን ሁለተኛውን አጋማሽ በተመሳሳይ በማጥቃት ፍላጎት ቢጀምሩም ጅማዎች ግን በሁለተኛው አጋማሽ ያመከኗትን ፍፁም ቅጣት ምት አጋጣሚ ጨምሮ በርከት ያሉ አጋጣሚዎችን አከታትለው መፍጠራቸውን ተከትሎ ወልቂጤዎች ከማጥቃት ይልቅ ይበልጥ ለጨዋታ ቁጥጥር ትኩረት በመስጠት የጅማዎች የማጥቃት ማዕበል ለመቀልበስ የታተሩ ሲሆን በዚህም ይህን ሂደት ቀልብሰው በመልሶ ማጥቃት ባስቆጠሯት ሦስተኛ ግብ ከጨዋታው ወሳኙን ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል።

በ21ኛው የጨዋታ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን 3-0 በሆነ ውጤት ከረቱ ወዲህ ከድል ተራርቀው የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች ከ7 ጨዋታዎች በኋላ በሊጉ ለመቆየት ማሸነፍ የግድ ይላቸው በነበረው በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የጅማ አባ ጅፋር መርሐግብር በተመሳሳይ የ3-0 ድል በማስመዝገብ ወደ ድል በተመለሱበት ጨዋታ በሊጉ ለከርሞ መቆየታቸውን አረጋግጠዋል።

በሊጉ የማሳረጊያ መርሐግብር ወላይታ ድቻን የሚገጥሙት ወልቂጤ ከተማዎች ይህን ጨዋታ በድል መወጣት የሚችሉ ከሆነ ከሆነ በሊጉ አሁን ከሚገኙበት ደረጃ በተሻለ ሁኔታ ሊያጠናቅቁበት የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር ይችላሉ።

👉 ለሦስተኝነት እየተፎካከሩ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና

ከሌሎቹ ፉክክሮች አንፃር አነስተኛ ግምት በሚሰጠው እና የመጨረሻውን የሜዳሊያ ስፍራ ይዞ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ሲዳማ ቡናዎች ሀዋሳ ከተማ ላይ የሁለት ነጥብ ብልጫ ይዘው ወደ መጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ያመራሉ።

የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ ወዲህ በወጥነት አውንታዊ ውጤቶችን ለማስመዝገብ የተቸገሩት ሲዳማ ቡናዎች ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ መልስ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማን በመርታት ወደ አሸናፊነት የተመለሱ ሲሆን በአንፃሩ ከተከታታይ ድሎች በኋላ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከነማ ሽንፈት አስተናግደው የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በተመሳሳይ መከላከያን በመርታት ወደ ድል ተመልሰዋል። ውጤቶቹን ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎች አሁንም ቢሆን በ47 ነጥብ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በሁለት ነጥብ አንሰው በ45 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ሁለቱ ቡድኖች መቀመጫቸውን በአንድ ከተማ እንደማድረጋቸው በመካከላቸው ካለው የፉክክር ስሜት አንፃሮ በሊጉ የተሻለ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ በቀላሉ የሚታይ ስኬት አይሆንም። በመሆኑም በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡናዎች ከሀዲያ ሆሳዕና እንዲሁም ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ።