የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ወሳኝ ድል አሳክተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በተደረጉ አራት መርሐግብሮች ጅምሩን ሲያደርግ መከላከያ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ተጋጣሚዎቻቸውን ሲረቱ አዳማ እና ቦሌ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡

መከላከያ 4-1 አዲስ አበባ ከተማ

የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ላይ ከፍ ለማለት ዕድል ያለው መከላከያ እና ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች የወጥነት ችግር ካለበት አዲስ አበባ ከተማ የተገናኙበት ጨዋታ 4-1 ፍፃሜውን አድርጓል፡፡

የመከላከያ አጥቂዎች በስልነት ለመጫወት በሞከሩበት እና የአዲስ አበባ ከተማ ደካማ የመከላከል ብቃትን ባየንበት ጨዋታ 36ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር ስራ ይርዳው ወደ ሳጥን ኳስ ስታሻግር የአዲስ አበባዋ ተከላካይ ሀና እና ግብ ጠባቂዋ ቤተልሄም ዮሐንስ መግባባት በተሳናቸው ቅፅበት ረሂማ ዘርጋው አፈትልካ ወጥታ ወደ ጎልነት ቀይራው መከላከያን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ በድጋሚ 42ኛው ደቂቃ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች በስራ ይርዳው ጎል የጎል መጠናቸውን ከፍ አድርገዋል፡፡

ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ተጨማሪ ግብ ለማከል ጥረታቸውን የቀጠሉት ዕንስት ጦረኞቹ 76ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ሴናፍ አሻምታ በተከላካዮች ሲመለስ ከሳጥን ውጪ የነበረችው ቤዛዊት ተስፋዬ ማራኪ ሦስተኛ ጎል ከመረብ አዋህዳለች፡፡ ወደ ጨዋታ ለመመለስ በተወሰነ መልኩ ከ80 ደቂቃዎች በኋላ መዳከር የጀመሩት አዲስ አበባዎች ከቅጣት ምት በሻዱ ረጋሳ ስታሻማ ነፃነት ፀጋዬ በራሷ ላይ ባስቆጠረችው ጎል 3-1 መሆን ቢችሉም ሴናፍ ዋቁማ ከሳጥን ውጪ አክርራ አስደናቂ አራተኛ ጎል ለመከላከያ በማስቆጠር ጨዋታው 4-1 ተጠናቋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ

5፡00 ሰዓት ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ከቀናት በፊት የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን አሳክቶ የነበረውን አቃቂ ቃሊቲን ያገናኘው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ አስደናቂ የሜዳ ላይ የኳስ ፍሰት ታጅቦ በአቃቂ ቃሊቲ ወጥነት በጎደለው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ቀጥሎ ዕንስት ፈረሰኞችን ቀስ በቀስ ባለ ድል አድርጓል፡፡ 25ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል አጥቂዋ እየሩስ ወንድሙ ጊዮርጊስን መሪ ያደረገች ግብ ከመረብ አሳርፋለች፡፡ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ በቅጣት ምት ፍቅርተ ብርሀኑ አቃቂን አቻ ማድረግ ብትችልም ፈጣን የሽግግር የጨዋታ መንገድን ሲከተሉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሁለት ደቂቃ ቆይታ በኋላ በእየሩስ ወንድሙ አማካኝነት ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል፡፡

ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ቀጥሎ ፊት ለፊት ላይ የተዋጣላት አጥቂዋ እየሩስ ወንድሙ በድንቅ አጨራረስ 60ኛው ደቂቃ ላይ ለራሷ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ጎል በማስቆጠር ጨዋታው 3-1 ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

ሀዋሳ ከተማ 2-1 ጌዲኦ ዲላ

ከክፍያ ጋር በተያያዘ ለተጫዋቾቹ ደመወዝ ባለመክፈሉ በተደጋጋሚ ሮሮ የሚሰማበት ጌዲኦ ዲላ አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ከሀገር ውጪ መሆኑን ተከትሎ በምክትል አሰልጣኙ ዓለማየሁ ተስፋዬ እየተመራ ሁለተኛ ጨዋታውን አድርጎ በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ እንደ አጀማመሩ ከሆነ ተመጣጣኝ ፉክክር ባየንበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሀዋሳን መሪ ያደረገው ገና በጊዜ ነበር፡፡ 6ኛው ደቂቃ ላይ ፈጣኗ አጥቂ ቁምነገር ካሳ በመልሶ ማጥቃት ከመስመር ከተገኘ አጋጣሚ ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ 

አሰልጣኝ መልካሙ ታፈረን በቅጣት ያጣው እና በረዳቱ ሙጫላ ዲላ እየተመራ ጨዋታውን የከወነው ሀዋሳ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ኪፊያ አብዱራህማን በአግባቡ ያቀበለቻትን ኳስ ነፃነት መና የጌዲኦ ዲላ ተከላካዮችን አምልጣ በመውጣት ኳስ እና መረብን አዋህዳለች፡፡ በተወሰነ መልኩ የጌዲኦ ዲላን የመልሶ ማጥቃት እና ተሻጋሪ ኳሶችን የመከላከል ውስነት ይታይባቸው የነበሩት ሀዋሳዎች 13ኛው ደቂቃ ላይ የዲላዋ አምበል አዲስ ንጉሴ ከቅጣት ምት ስታሻማ ብዙሀን እንዳለ በግንባር በመግጨት በራሷ ላይ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው ወደ 2-1 ተሸጋግሯል፡፡

ከዕረፍት በፊት ጨዋታው ያለቀ በሚመስል መልኩ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ከሜዳ ላይ በውበት ካልታጀቡ እንቅስቃሴዎች ውጪ ተጨማሪ ጎል ሳንመለከት ጨዋታው 2-1 ሀዋሳን አሸናፊ በማድረግ ተፈፅሟል፡፡

አዳማ ከተማ 2-2 ቦሌ ክፍለ ከተማ

የአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የዕለቱን የመጨረሻ እና አራተኛ ጨዋታውን 10፡00 ሰዓት ሲል አስተናግዷል፡፡ አዳማ ከተማን ከቦሌ ክፍለ ከተማ ያገናኘው እና ማራኪ የጨዋታ ሂደትን በተለይ በቦሌዎች በኩል አይሎ የቀረበበት እና በተሻጋሪ ኳሶች በአንፃሩ አዳማዎች ጥቃት ለመሰንዘር የታተሩበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ 11ኛው ደቂቃ ላይ ሄለን እሸቱ ከሳጥን ውጪ አክርራ ስትመታ ግብ ጠባቂዋ ሊንጎ ኡማን ኳሱን በአግባቡ መያዝ ባለ መቻሏ ኳስ እና መረብ ተገናኝቶ አዳማ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ በአንድ ሁለት አጨዋወት በይበልጥ ለአጥቂዋ ንግስት በቀለ በመጣል መልስ ለመስጠት የሞከሩት ቦሌዎች በሜላት ጌታቸው ጎል አቻ መሆን ችለዋል፡፡

ከዕረፍት መልስ ለአስር ደቂቃዎች ያህል ጨዋታውን ለመቆጣጠር ቦሌዎች በሞከሩበት ቅፅበት በአማካዩዋ ጤናዬ ለታሞ ጎል ዳግም ወደ መሪነት መሸጋገር ቢችሉም በሂደት ደካማ በነበረው የመከላከል አፈፃፀማቸው ተቀይራ በገባችው መሰሉ አበራ የግንባር ግብ ተቆጥሮባቸው ጨዋታው 2-2 ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡