ፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ ቅጣት ተላልፎባቸዋል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ሲያያቸው በነበሩ ሁለት ጉዳዮች ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ወስኗል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ረቡዕ ሰኔ 29 2014 ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ከዳኞች እና ታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት በመመርመር እንዲሁም በኮሙኒኬ 30 ጥሪ የተደረገላቸው የጨዋታ አመራሮች እና የክለብ አባላት ካነጋገር በኋላ የተለያዩ የዲሲፕሊን ውሳኔዎችን ማሳለፉን ይፋ አድርጓል።

በ28ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ከባህርዳር ጋር በነበረው ጨዋታ ግጥሚያው ከተጠናቀቀ በኋላ የክለቡ ደጋፊዎችና የቡድን አመራሮች አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት የቀረበበት ሲሆን የክለቡ ደጋፊዎችና የቡድን አመራሮች በዕለቱ ባጠፉት ጥፋትና ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ጥፋት ከተቀጡት ቅጣትም ሊታረሙ ባለመቻላቸው ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 4 አንቀፅ 66 በተቁ 4(ሀ) መሰረት ብር 75000 /ሰባ አምስት ሺህ/ እንዲከፍል ተወስኗል ።

በ30ኛ ሳምንት ደግሞ ፋሲል ከነማ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ከ68ኛው ደቂቃ ጀምሮ ስፖርታዊ ጨዋነትን ያልተከተለ ድጋፍ ስለመስጠታቸው እና ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የጥበቃ ኃይሎች ሊቆጣጠሩት ባልቻለ ሁኔታ ወደ መጫወቻ ሜዳ ጥሰው ስለመግባታቸውና ስለማወካቸው እንዲሁም ለሜዳሊያ አስጣጥ ስነስርዓት አፈጻጸም እንቅፋት ስለመሆናቸው ሪፖርት ቀርቦበታል በማለት የክለቡ ደጋፊዎች በዕለቱ ባጠፉት ጥፋትና ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ጥፋት ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 አንቀፅ 66 በተቁ 3(ሀ) ና ለ(1) መሰረት ብር 100000 /አንድ መቶ ሺህ/ እንዲከፍልና በሜዳቸው የሚጫወቱትን ቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች ያለደጋፊ በዝግ ስታዲየም እንዲያደርጉ ወስኗል።