የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መግለጫ ሰጥተዋል

በቀጣዩ ነሀሴ በጎንደር ከተማ ለሚደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የፕሬዚዳንታዊ እና የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ አስፈፃሚ የሆነው ኮሚቴ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በቀጣዩ ወር ነሀሴ 22 በጎንደር ከተማ ለሚደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የፕሬዚዳንታዊ እና የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫን በተመለከተ ለምርጫው የተመረጡት አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ዛሬ ከሰዓት በኋላ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ኮሚቴዎቹ አምስት አባላት ያሉት ቢሆንም አራቱ ማለትም አቶ ሀይሉ ሞላ ፣አቶ መንግስቱ ማሩ ፣ አቶ በለጠ ዘውዴ እና አቶ ኢሳያስ ደንድር ተገኝተዋል፡፡ አስቀድመው የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሀይሉ ሞላ በሰጡት የስራ ክንውን ዙሪያ ዘለግ ያለ ማብራሪያ በመስጠት መግለጫው ጀምሯል፡፡

“በቀጣዩ ነሀሴ 22 ለሚደረገው የፌዴሬሽኑ የፕሬዚዳንታዊ እና ስራ አስፈፃሚ ምርጫን ለማስፈፀም ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓመተ ምህረት በተደረገው አስቸኳይ ጉባኤ የተሰየመ የምርጫ ኮሚቴ አለ እኔ እና ባልደረቦቼ የኮሚቴው አባል ነን የዛሬው አላማችን በምርጫው ሂደት እየተካሄዱ ያሉ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት ነው፡፡ ግንቦት 7 በኢሲኤ ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ መተዳደሪያ ደንብ የምርጫ ማስፈፀሚያ ህግን የጠቅላላ ጉባኤ አመራር ደንብ እና የተገቢነት ማረጋገጫ መጠይቁን አፅድቆት ጉባኤው አንዳንድ ሀሳቦች ሰጥቶ ከዛ በኋላ የጉባኤው ሀሳብ ማሻሻያ በማድረግ ተሻሽሎ እንዲፀድቅ ተወስኗል፡፡ የምርጫ ኮሚቴ አስፈፃሚ አባላት እኔ እና ባልደረቦቼ መተዳደሪያ ደንቡን ፣ የምርጫ ደንቡን ፣ የተገቢነት ማረጋገጫ መጠይቁን እነዚህን በዋነኛነት ይዘን ነው ስራችንን የጀመርነው በተጨማሪ የፊፋ እና የካፍን የምርጫ ሂደትን ፅህፈት ቤቱ አቅርቦልን ነው ስራችን የጀመርነው የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት እነዚህን ነገሮች በሚገባ አሟልቶልን በጥልቀት ኮሚቴው ከተወያየ በኋላ የመጀመሪያ ስራ ያደረግነው የኮሚቴያችንን የስራ ኮድ ኦፍ ኢቲክስ መቅረፅ ነው የዛሬ አራት አመት የነበረው ታውቃላችሁ እና ከእነዛም ትምህርት በመውሰድ እንዴት ነው የሚመራው ይሄ ኮሚቴ በምን አይነት መንገድ ነው ስራውን የሚሰራው የሚለውን መስራት አለብን ብለን አፅድቀናል፡፡ በኮድ ኦፍ ኢቲክስ ውስጥ የኮሚቴው ግዴታዎች ፣ የመልካም አስተዳደር በዝርዝር ተቀምጧል እንዲሁም የምርጫ ኮሚቴ የስራ ክፍፍል ኮሚቴው ሰብሳቢ አለው ምክትል ሰብሳቢ አለው ዋኛ ፀሀፊ አለው እነኚህ ሰዎች ምንድነው የሚሰሩት የሚለውን ከምርጫ ኮዱ በተጨማሪ እሱም በዝርዝር ተቀምጧል ኮዱ ላይ ሌላው ሚስጥራዊ እና ፍትሀዊ ጉዳዮች በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ እንደ ቀድሞው አንዱ እየተነሳ መግለጫ የሚሰጥበት አሰራር ከዚህ በኋላ የለም እናንተም አትቀየሙንም ብለን እናስባለን ኮሚቴው ሲወስን እና ሲስማማ መረጃ ለህዝብ መድረስ አለበት ብለን ካመንን እናደርሳለን ምክንያቱም ወጥ የሆነ ፎርማል የሆነ ስራ መስራት ስላለብን በዛ አይነት መንገድ ነው የምናስኬደው፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር እንዴት ሆነን ነው የምንገናኘው የሚለውን የሚደነግጉ ጉዳዮች አሉ በዋነኛነት መረጃን ለሚዲያም ሆነ ለማንኛውም አካል እንዴት እንደሚሰጥ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ በኮሚቴው ትኩረት ተሰጥቶ የተሰራበት ሌላው ጉዳይ የስራ መርሃግብር ማዘጋጀት ነው፡፡ በዚህም መሠረት 23 አይተም ተዘርግቶ መቼ ምን እንደሚሰራ መቼ እንደሚጠናቀቅ በዝርዝር ሰርተን እሱንም ጨርሰናል፡፡ ለፊፋ የዚህ ኮሚቴ አባላት ስም ዝርዝር እና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ስም ዝርዝር መላክ አለበት እሱ በፅህፈት ቤት በኩል እንዲሰራ ተነጋግረን እየተሰራ እንዳለ ገምታለሁኝ፡፡ የምርጫ ኮዱ ተተርጉሞ በእንግሊዝኛ ወደ ሚመለከታቸው አካላት በተለይ አለም አቀፍ እና ወደ አፍሪካ እግር ኳስ ፌድሬሽን እንዲሄድ እየሰሩት እንዳለ እናውቃለን ትልቁ ከዛሬ ጀምሮ የምንሰራው ፅህፈት ቤቱ እያገዘን ያለው መተዳደሪያ ደንቡን እነ የምርጫ ኮዱን የተገቢነት ማረጋገጫ ፎርሙን ለአባላት ያለቀውን ከዛሬ ጀምሮ እንዲበተን ተስማምተናል፡፡ ዋናው እኛ የምንሰራው እጩዎች ከፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት የእጩ ፎርሞችን ከዛሬ ጀምሮ እንዲወስዱ እና ለክልል እና ለከተማ ፌድሬሽኑ ፅህፈት ቤቱ እንዲያደርስ ተስማምተናል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሀምሌ 18 እስከ 11 ሰዓት ድረስ እጩ እንቀበላለን፡፡ ሲሉ ሰብሳቢ በንግግራቸው የገለፁ ሲሆን እስከ ሀምሌ 26 ድረስ ሙሉ በሙሉ ተወዳዳሪዎች በመቀበል ይፋ ለማድረግ አስባለሁ፡፡

ከሰብሳቢው ንግግር በመቀጠል በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን ሰብሳቢው አቶ ሀይሉ ሞላ እና ምክትል ሰብሳቢው መንግስቱ ማሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እኛም የተነሱ ዋና ዋናዎቹን አቅርበንላችኋል፡፡

ለሚዲያ መረጃን ከመስጠት ጋር በተገናኘ ለተጠየቀው ጥያቄ አቶ ኃይሉ “ከሚዲያ ጋር በተገናኘ አስፈላጊ በሆነው ሁሉ ኮሚቴው መግለጫ ይሰጣል ግን በተናጥል እየተወጣ ከዚህ ቀደም እንደነበረው አይሰጥም በስነ ምግባር ህጉ አንቀፅ ዘጠኝ ላይ ብታዩ አስፈላጊ ሆኖ ባመነበት ሁኔታ ላይ ኮሚቴው ይሰጣል በየቀኑም ሊሰጥ ይችላል፡፡ ግን ሀይሉን ናና መልስልኝ ብባል አላውቅም ለሁሉም ዕኩል ነው የምናደርሰው መረጃ እኛ ለሁሉም ዕኩል ሲደርስ ነው ስርአት ጠብቆ ሊሄድ የሚችለው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሚል ነው ያስቀመጥነው አሰራሮችን በተቻለ መጠን ግልፅ አድርገን የእግር ኳስ ቤተሰቡም የኢትዮጵያ ህዝብም በአግባቡ ሂደታችንን እየተከታተለ የት ደረጃ እንደደረስን እያወቀ ተወዳዳሪዎችም ምን ደረጃ እንዳሉ እኛም ምን እየሰራን እንዳለን እንዲያውቁ አድርገን ነው በተቻለ መጠን ስራችንን የምንሰራው፡፡

በምርጫው ላይ ፓለቲካዊ ጫና በምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴው ላይ ቢመጣ በምን ዐይነት መልኩ ለመቋቋም እንደተዘጋጁ ለተነሳው የጋዜጠኞች ጥያቄ ምክትል ሰብሳቢው አቶ መንግስቱ “ግልፅ የሆኑ የተቀመጠ አቅጣጫዎች አሉ አላስፈላጊ የሆነ በመንግስት እና በመሳሰሉ አካላት የሚመጣ ጫና ሲኖር በአፋጣኝ እንዴት ሪፖርት እንደሚደረግ ጭምር ተቀምጧል፡፡ ይሄ ስለተፃፈ ብቻ ሳይሆን ቁርጠኝነትም ይጠይቃል፡፡ በእኛ በኩል ጠቅላላ ጉባኤው አምኖን ይሄንን ነገር ማስፈፀም ትችላላችው ባለን በተፃፈው መሠረት ብቻ ብንቀበለውም ባንቀበለውም በተፃፈው ብቻ ለመሄድ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ሌላ ውጫዊ ጫናን ለመቀበል ውስጣችን ዝግጁነት የለም ካቃተን የመሄድ ጉዳይ ነው የሚሆነው እንጂ ሌላ ግፊት አንቀበልም ብዬ አስባለሁ፡፡

ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ከፌዴሬሽኑ የተወሰደ ነው ወይንስ አዲስ የተቋቋመ ነው በሚል ለተነሳው ጥያቄም አቶ መንግስቱ “በአስመራጩ ዕለት ተመርጧል ሶስት ሰዎች ያሉበት ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አለ እኛ እስከ 26 አጣርተን እነማን ብቃት አላቸው የላቸውም በደንቡ መሠረት እናሳውቃለን በዛ መሀል የማይስማማ ሰው ሲኖር ከ26 እስከ ነሀሴ 2 ደግሞ ይግባኙ አይቶ አጥርቶ ምላሽ ይሰጣል ከዛ በኋላ ነው የመጨረሻ ዕጩዎች ግልፅ የሚሆኑት፡፡

ሶስት የምርጫ ዘመን የተወዳደሩ እና ስራ አስፈፃሚ የነበሩ አሁንም ለአራተኛ ጊዜ ለመወዳደር አቅደዋል ከደንቡ አንፃር የተለየ ነገር አለው አቶ ሞላ ☞”ሶስት የምርጫ ዘመንን በተመለከተ ይሄ የመተዳደሪያ ደንቡ ግልፅ ነው፡፡ ይሄ ጥያቄ የሚነሳው አሁን አይደለም ወቅት አለው ይሄ ኮሚቴ በነገራችን ላይ የሚሰራው ሶስት ነገሮችን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ የመጀመሪያው መተዳደሪያ ደንቡ ነው እንደዚህ አይነት ጥያቄ ሲቀርብ መተዳደሪያ ደንቡ ምን ይላል የሚለውን ይሄ ኮሚቴ የሚመረምረው ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ሶስት የምርጫ ዘመን ነው አይደለም ብለን የምንሰጠው ማብራሪያ አይኖርም፡፡ ስለዚህ ጊዜው ወቅቱ ሲደርስ የሚቀርቡ ዕጩዎችን ፕሮፋይል እየመረመርን አስመራጭ ኮሚቴው ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ በአስመራጭ ኮሚቴው ውሳኔ የማይስማማ ካለ ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ያቀርባል የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የወሰነው ውሳኔ የመጨረሻ ነው ይግባኝም የለውም ከዚህ ውጪ፡፡

ተወዳዳሪ የሆነ ግለሰብ የምረጡኝ ቅስቀሳ በምን አይነት መልኩ ሊያደርግ ይገባዋል አቶ ሀይሉ ☞”አንድ ተወዳዳሪ ከምርጫ ኮዱ ውጪ ስራ የሚሰራ ከሆነ አቁም እንለዋለን፡፡ ምክንያቱም ኮዱ ምርጫው እንዴት ተጀምሮ እንዴት እንደሚጠናቀቅ በዝርዝር ያስቀመጠው ነገር አለ፡፡ ባልተገባ መንገድ የሚኬድ ከሆነ ግን እንደዚህ አይነት ድርጊት የሚፈፅሙ ተወዳዳሪዎችን የምርጫውን ታማኝነት እና ሂደቱን የመጠበቅ ግዴታ ስላለብን እኛ እሱን ኮሚቴው እየነጋገረ ከዕጩዎች ጋር እየተነጋገርን መስመር የምናሲዘው እንጂ ዝም ብለን አንለቅም፡፡ አንዱ ወገን የአንደኛውን ስም እያጠፋ ሲሄድ ዝም ብለን የምናየው ከሆነ መረን እየለቀቀ የሚሄደው እሱ ላይ በሂደት የምናያቸው ይሆናል፡፡