ብሄራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች በኋላ ዛሬ ለተጫዋቾቹ የማበረታቻ ገንዘብ አበርክቷል፡፡ ከቡድኑ አባላት ጋርም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ውይይት ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና የፅህፈት ቤት ሃላፊው ዛሬ ጠዋት ቡድኑ ባረፈበት ካፒታል ሆቴል በመገኘት ከተጫዋቾቹ ጋር የተወያዩ ሲሆን ከጉዞ እና ከመሳሰሉት ጋር የተያያዙ ችግሮች በተጫዋቾች ተነስተዋል፡፡ ፌዴሬሽኑም በብሄራዊ ቡድኑ የሚፈጠሩትን ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚሰራና እንደ አልጄርያው አይነት በረጅም ጉዞዎች የሚፈጠሩ መጉላላቶችን ለማስወገድ ከሚመለከተው አካል ጋር እንደሚሰራ የፌዴሬሽኑ ሃላፊዎች ከተጫዋቾቹ ጋር ባደረጉት ውይይት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ ከተጫዋቾች እና የብሄራዊ ቡድን አባላት ጋር በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ቶሎ ቶሎ በመገናኘት ችግሮች እንዳይፈጠሩ ጥረት እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለብሄራዊ ቡድን አባላት የማበረታቻ ገንዘብ ሲያበረክት ለሁሉም ተጫዋቾች እያንዳንዳቸው 20ሺህ ብር ተበርክቶላቸዋል፡፡
ፌዴሬሽኑ ከትላንትናው ጨዋታ በፊት የትኛውም ውጤት ቢመዘገብ 10ሺህ ብር ለማበርከት ወስኖ የነበረ ቢሆንም ተጫዋቾቹ በትላንትናው ጨዋታ ያሳዩት እንቅስቃሴ ፌዴሬሽኑን በማስደሰቱ ማበረታቻው ወደ 20ሺህ ብር እንዲያድግ መወሰኑ ተነግሯል፡፡