የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትላንት በአአ ስታድየም ባደረገው ጨዋታ አልጄርያን በሶስት አጋጣሚዎች መርቶ በመጨረሻም ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡
ዋልያዎቹን ለመጀመርያ ጊዜ በአምበልነት የመራው ሽመልስ በቀለ ስለ አምበልነቱ ፣ ጨዋታው እና የፔትሮጄት ቆይታው ቡድኑ ባረፈበት ሆቴል ከተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡
ብሄራዊ ቡድንን በአምበልነት መምራት የሚፈጥረው ስሜት ምን ያህል ነው?
“አምበል በመሆኔ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ አምበል ስትሆን ብዙ ሃላፊነት ትሸከማለህ፡፡ በዙርያህ ያለውን ሃላፊነት ስትወጣ ደግሞ ደስ ይላል፡፡”
ከከባድ ሽንፈት አገግማችሁ የትላንትናውን ጨዋታ ለማሸነፍ የተቃረባችሁበት ምስጢር ምንድነው?
“ሽንፈቱ በጣም ከባድ ነበር፡፡ የጉዞው ድካምም አልወጣልንም ነበር፡፡ ትላንት ግነን የተጫወትነው በሜዳችን እና ደጋፊያችን ፊት ነበር፡፡ ህዝቡ የሚፈልገውን ውጤት ባናሳካም ጥሩ ተንቀሳቅሰናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህም የቡድን አጋሮቼን አመሰግናለሁ፡፡
“እንደሚታወቀው አልጄርያ ትልቅ ቡድን ነው፡፡ ተጫዋቾቹም በአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ሆኖም የትላንት እንቅስቃሴያቸውም እንደተመለከታችሁት ነው፡፡ እግርኳስ እንዲህ ነው፡፡ አንዳንዴ ውጤት ይጠፋል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ድል ካንተ ጋር ይሆናል፡፡ የአልጄርያው ጨዋታ ውጤት አሳፋሪ ቢሆንም ትላንት ህዝቡን ለማስደሰት የቻልነውን ያህል ጥረት አድርገናል፡፡”
የአጨዋወት ባህሪህ በማጥቃት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በትላንቱ ጨዋታ ግን የመከላከል ሃላፊነቶችንም ስትወጣ ነበር፡፡ ይህ የሆነው በአምበልነቱ ምክንያት ከተፈጠረብህ የሃላፊነት ስሜት ነው?
“እንደሚታወቀው እኔ የማተኩረው በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን በትላንቱ ጨዋታ ቡድናችን ውጤቱ ስለሚያስፈልገው የኀላውን መስመር ማገዝ ነበረብኝ፡፡ በብቸኛ የተከላካይ አማካኝነት የተሰለፈው ጋቶች ጫና እንዳይፈጠርበት መርዳት እና ኳስ ለመቀበል ማፈግፈግ ስለነበረብኝ ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩት ውጤቱ ለኛ በጣም አስፈላጊ ስለነበር ሁልጊዜም ከኳስ ጀርባ ለመገኘት እጥር ነበር እንጂ አምበልነቱ የፈጠረብኝ ጫና አይደለም፡፡ ”
አሁን በምድባችን 2ኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫው የማለፍ ተስፋችን ምንያህል ነው ብለህ ታስባለህ?
“ሁለት ጨዋታዎች ከፊታችን ይቀራሉ፡፡ የትላንቱን ብናሸንፍ የማለፍ እድላችን የመስፋት እድል ነበረው፡፡ ነገር ግን ጥሩ ሁለተኛ ሆኖ ለማለፍ የተሻለ ነጥብ እንዳለን አስባለሁ፡፡ ይህን እድል ለማግኘት ደግሞ ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ይጠበቅብናል፡፡ አሸንፈን የአፍሪካ ዋንጫውን እንቀላቀላለን ብዬም አስባለሁ፡፡ ”
በክለብህ ፔትሮጄት አምና የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ነበርክ፡፡ የዘንድሮው ግን ወጣ ገባ ሆኗል፡፡ ምክንያቱ ምን ይሆን?
“አንተም እንዳልከው በዘንድሮው የውድድር ዘመን በፔትሮጀት ያለው ሁኔታ ወጣ ገባ ነው፡፡ አሰልጣኙ እኔን የማያሰልፍበት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ብቃቴ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ትላንት ተመልክታችኀል፡፡ ነጠር ግን አሰልጣኙ እኔን በተለያዩ ምክንያቶቾ ከቋሚ አሰላለፍ ውጪ አድርጎኝ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ግን መሰለፍ ጀምሬያለሁ፡፡
“ከአምናው አንፃር ዘንድሮ የምገኝበት ሁኔታ በክለቡ ደስተኛ እንዳለሆን አድርጎኛል፡፡ ከክለቡ ጋር ተነጋግሬ ኮንትራቴን የሚያፈርሱልኝ ከሆነ ወደ ሌሎች ክለቦች የማምራት ፍላጎት አለኝ፡፡ ይህ የማይሳካ ከሆነ ግን ኮንትራቴን አክብሬ ክለቤን አገለግላለሁ፡፡ ”