ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

አዲስ አዳጊው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም የአራት ነባር ተጫዋቾችንም ውል አድሷል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና አማካኝነት የተመለሰውና ከቀናት በፊት የአሰልጣኙን ውል እንዲሁም የነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት በማደሰ ለቀጣዩ ዓመት ዝግጅቱን የጀመረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም የአራት ነባሮችን ኮንትራት ማደሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ታፈሰ ሰርካ አዲሱ የክለቡ ፈራሚ ተጫዋች ነው፡፡ የቀድሞው የደቡብ ፓሊስ ፣ መከላከያ እና መቐለ 70 እንደርታ የመስመር ተከላካይ አዳማ ከተማን ከለቀቀ በኋላ የ2014 የውድድር ዘመንን በሰበታ ከተማ በመጫወት ቆይታን አድርጎ በመጨረሻም በደቡብ ፓሊስ ካሰለጠኑት አሰልጣኝ ጋር የተገናኘበትን ዝውውር አጠናቋል፡፡

ወጣቱ አማካኝ ሙሴ ካቤላም የክለቡ አዲሱ ተጫዋች ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ቡና የተገኘው እና የተጠናቀቀውን ዓመት በውሰት በጅማ አባጅፋር ያሳለፈው አማካይ አሁን መዳረሻውን ኤሌክትሪክ አድርጓል፡፡

ክለቡ ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ በተጨማሪ የአራት ነባሮችን ውልም አራዝሟል፡፡ ክለቡ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ካሳደገ በኋላ በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በውሰት ውል በኢትዮጵያ ቡና ያሳለፈው የተከላካይ አማካዩ አብነት ደምሴ ፣ አጥቂው ኢብራሂም ከድር ፣ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ስንታየው ዋልጬ እና ያሬድ የማነህም በቡድኑ ውስጥ ለተጨማሪ ዓመት ውላቸው የታደሰላቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡