ድሬዳዋ ከተማ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

ድሬዳዋ ከተማ ከደቂቃዎች በፊት ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፅህፈት ቤት አስፈርሟል፡፡

አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይን በዋና አሰልጣኝነት ከቀጠረ በኋላ ከሰዓታት በፊት ጫላ በንቲን የግሉ ማድረግ የቻለው ድሬዳዋ ከተማ አሁን ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን በማከል የአዳዲስ ፈራሚዎቹን ቁጥር ሰባት አድርሷል፡፡

ቢኒያም ጌታቸው በአንድ ዓመት ውል የድሬዳዋ ስድስተኛ ፈራሚ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የሀምበሪቾ ዱራሜ እና አክሱም ከተማ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለአዲስ አበባ በመጫወት ቆይታ የነበረው ሲሆን ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ደግሞ ሁለተኛ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎውን በምስራቁ ክለብ ለማድረግ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን በመገኘት ከሰዓታት በፊት ፊርማውን አኑሯል፡፡

ሌላኛው ፈራሚ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ሆኗል፡፡ ከጋሞ ጨንቻ የተገኘው እና በወሎ ኮምቦልቻ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ከከፍተኛ ሊግ እስከ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊጉ የዘለቀው የቀኝ መስመር ተከላካዩ በሁለት ዓመት ውል በይፋ በዛሬው ዕለት ድሬዳዋን ተቀላቅሏል፡፡