መቻል የመስመር ተጫዋች አስፈርሟል

በቀጣዩ የውድድር ዓመት ተጠናክሮ ለመቅረብ በዝውውሩ እየተሳተፈ የሚገኘው መቻል የመስመር ተጫዋች የግሉ አድርጓል።

በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው መቻል የቀጣይ ዓመት ስብስቡን እንደ አዲስ እያዋቀረ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከዚህ ቀደም ዘጠኝ ወሳኝ ተጫዋቾችን በይፋ ወደ ስብስቡ የቀላቀለው ቡድኑም ከደቂቃዎች በፊት ፈጣኑን የመስመር ተጫዋች ግርማ ዲሳሳን በአንድ ዓመት ውል የግሉ አድርጓል።

የቀድሞ የዳሞት ከተማ እና አማራ ፖሊስ ተጫዋች ያለፉትን ዓመታት በትውልድ ከተማው ክለብ ባህር ዳር ከተማ ሲጫወት ያሳለፈ ሲሆን ውሉ መገባደዱን ተከትሎ ከቀድሞ አሠልጣኙ ፋሲል ተካልኝ ጋር አብሮ ለመስራት ጦሩን ተቀላቅሏል። በሁለቱም መስመሮች በአጥቂ፣ አማካይ እና ተከላካይ ቦታ መሰለፍ የሚችለው ተጫዋቹ ለቡድኑ ጥሩ አማራጭ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።