ለገጣፎ ለገዳዲ አጥቂ አስፈርሟል

አዲስ አዳጊው ለገጣፎ ለገዳዲ ሦስተኛ ፈራሚውን ሲያገኝ የነባር ተጫዋቾቹን ውልም አራዝሟል።

ከሳምንት በፊት የሁለት የመስመር አማካይ ያብቃል ፈረጃ እና አላዛር ሽመልስን ከኢትዮጵያ ቡና ወደ ቡድናቸው የቀላቀሉት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ዛሬ ደግሞ አጥቂውን ኢብሳ በፍቃዱን ማስፈረማቸው ሲታወቅ የዘጠኝ ተጫዋቾቻቸውን ውል ማራዘማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በሀዲያ ሆሳዕና፣ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በያዝነው የውድድር ዓመት በነቀምት ከተማ ያሳለፈው የከፍተኛ ሊጉ የጎል ቀበኛ አጥቂው ኢብሳ በፍቃዱ በያዝናው የውድድር ዓመት ስምንት ጎል በማስቆጠር በከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ኢብሳ ለአንድ ዓመት ለለገጣፎ ለገዳዲ ለመጫወት ስማማቱን አውቀናል።

በሌላ ዜና በያዝነው ዓመት ለገጣፎ ለገዳዲ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንዲገባ ያስቻሉትን ተጫዋቾች ውል ማራዘሙ ታውቋል። እነርሱም ግብ ጠባቂው በሽር ደሊል ፣ ተከላካዮች መዝገቡ ቶላ፣ አስናቀ ተስፋዬ፣ አቤል አየለ፣ ኪሩቤል ወንድሙ ፣ አማካዮች አንዋር አብዱልጀባል፣ ተፈራ አንለይ ፣ አጥቂዎች ፋሲል አስማማው እና በውሰት ሀዲያ ሆሳዕና አቅንቶ የነበረው ልደቱ ለማ መሆናቸው ተገልጿል።