ቡናማዎቹ ዝግጅታቸውን በሀዋሳ ከተማ ያደርጋሉ

ተመስገን ዳናን አዲሱ አሰልጣኝ አድርገው የቀጠሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች የቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚጀምሩበት ቦታ እና ቀን ታውቋል፡፡

በክለቡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ከቆየው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር ከተለያየ በኋላ በምትኩ ተመስገን ዳናን በቦታው መተካት የቻለው ኢትዮጵያ ቡና በርካታ የክለቡ ነባር ተጫዋቾችን ካሰናበተ በኋላ በምትኩ አዳዲስ ወሳኝ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡ ሔኖክ ድልቢ ፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ መስፍን ታፈሰ ፣ ብሩክ በየነ ፣ ራምኬል ጀምስ ፣ ሀይለሚካኤል አደፍርስ ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊት ፣ አብዱልከሪም ወርቁ እና ጫላ ተሺታን ወደ ስብስቡ በማካተት እንዲሁም ውላቸው የተጠናቀቁ የነባር ተጫዋቾችን ቆይታ ያደሰ ሲሆን የ2015 የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መቼ እና የት እንደሚያደርግ ክለቡ ዛሬ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫው አሳውቋል፡፡

የፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 30 የክለቡ አዳዲስ ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ከደጋፊዎች ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ትውውቅ ካደረጉ በኋላ በሀዋሳ ከተማ በይፋ ከነሀሴ 2 ጀምሮ ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ ተገልጿል፡፡