ከ17 ዓመት በታች ሻምፒዮና በሀዋሳ ተጀምሯል

የ2014 ከ17 ዓመት በታች የክለቦች እና ክልሎች ሻምፒዮና ዛሬ ሲጀምር ሀዋሳ እና ባህር ዳር ድል አድርገዋል።

የ2014 የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የክለቦች እና የክልሎች ሻምፒዮና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አዘጋጅነት በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ከተማ የሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ በምድብ ሀ በሚገኙ ክለቦች መካከል በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ጀምሩን አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የፅህፈት ቤት ምክትል ፀሀፊ አቶ ሠለሞን ገብረስላሴ ፣ የውድድር ዳይሬክተሩ አቶ ከበደ ወርቁ ፣ አቶ ፍሬው አሬራ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር እና አቶ አንበሴ አበበ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በመክፈቻው የሀዋሳ ከተማ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የረፋድ 3፡00 ጨዋታን አስጀምረዋል፡፡

ከተያዘለት ደቂቃ ሰላሳ ያህሉን ዘግይቶ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ጎልቶ የታየበት ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ንግድ ባንክ ከዕረፍት መልስ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማ ብልጫን ማሳየት በቻሉበት በዚህ ጨዋታ 61ኛ ደቂቃ ላይ በሁለተኛው አጋማሽ ተፅእኖ ሲፈጥሩ የተስተዋሉት ሀዋሳዎች የማሸነፊያዋን ጎል አግኝተዋል፡፡ ኪሩቤል ዳኜ ከግራ መስመር አቅጣጫ በረጅሙ የላከለትን ኳስ ተጠቅሞ አማኑኤል ሞገስ ግሩም ጎልን ከመረብ በማሳረፍ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

እንደ መጀመሪያ ጨዋታ ሁሉ ሠላሳ ያህል ደቂቃዎች ዘግይት ብሎ የጀመረው የፋሲል ከነማ እና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ በጣና ሞገደኞቹ ታዳጊዎች አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ቡድኖቹ ሜዳ ላይ ሳቢነት የሌለው እንቅስቃሴን ሲያሳዩ መመልከት ብንችልም በሙከራ ረገድ ሻል ብለው የቀረቡት ባህር ዳር ከተማዎች ሁለት ግሩም ጎሎችን በማቆጠር የ2-0 አሸናፊ ሆነዋል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ 8ኛው ደቂቃ ናትናኤል ፍሰሀ ከሳጥን ውጪ አስደናቂ ጎል አግብቶ ቡድኑን መሪ ያደረገ ሲሆን ከዕረፍት መልስ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ሌላ አስደናቂ ግብን ካሊድ መሐመድ ለባህር ዳሮች አስገኝተዋል፡፡

በሴካፋ ተሳታፊ ለሚሆነው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የሚሆኑ ተጫዋቾች ከዚህ ውድድር ላይ የሚመረጡ ሲሆን ውድድሩ ነገም በአራት ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል፡፡

በክለቦች

ወልቂጤ ከተማ 03:00 አርባምንጭ ከተማ

ቅዱስ ጊዮርጊስ 05:00 ወላይታ ድቻ

በክልሎች

ሐረር ክልል 07:00 አዲስ አበባ ከተማ

ኦሮሚያ ክልል 10:00 ቀይ ዛላ (ደቡብ)