ሀድያ ሆሳዕና ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

ነብሮቹ ሁለት ተጫዋቾችን በአንድ ዓመት ኮንትራት በዛሬው ዕለት አስፈርመዋል።

እስከ አሁን በዝውውሩ ቤዛ መድህን ፣ ዳግም በቀለ ፣ ሰመረ ሀፍታይ ፣ እንዳለ ደባልቄ እና አክሊሉ ዋለልኝ የግሉ ማድረግ የቻለው ሀድያ ሆሳዕና የተከላካይ አማካዩ በኃይሉ ግርማ እና አጥቂው ዘካሪያስ ፍቅሬን በመቀላቀል የአዳዲስ ፈራሚዎችን ቁጥር ሰባት አድርሷል፡፡

በኃይሉ ግርማ የክለቡ ስድስተኛ ፈራሚ ሆኗል፡፡ ከሙገር ሲሚንቶ ከተገኘ በኋላ በመከላከያ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በመጫወት ያሳለፈው የተከላካይ አማካዩ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በሰበታ ከተማ ማሳለፍ ከቻለ በኋላ ቀጣይ መዳረሻው ነብሮቹ መሆኑ ዕርግጥ ሆኗል፡፡

ሌላኛው የቡድኑ ፈራሚ ደግሞ አጥቂው ዘካሪያስ ፍቅሬ ነው፡፡ የቀድሞ የአክሱም ከተማ ፣ አርባምንጭ ከተማ ፣ ሀላባ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና መከላከያ ተጫዋች እንደ በኃይሉ ሰበታ ከተማን በመልቀቅ በአንድ ዓመት የውል ዕድሜ ወደ ሀዲያ አምርቷል።