የለገጣፎ ለገዳዲ የዝግጅት ጊዜ እና ቦታ ታውቋል

በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ የሚኖረው ለገጣፎ ለገዳዲ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሊጀምር ነው።

ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን በምድብ ሐ ከሚገኙ ክለቦች መካከል አንዱ የነበረው ለገጣፎ ለገዳዲ ባስመዘገባቸው ውጤቶች ታግዞ የምድቡ የበላይ በመሆን ወደ 2015 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ ማለፉ ይታወሳል፡፡ ለሊጉ እንግዳ የሆነው ክለቡ እስከ አሁን የአሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመን ኮንትራት ከማራዘም ይልቅ አስቀድሞ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም ከርሟል፡፡

ምትኩ ጌታቸው ፣ ታዬ ጋሻው ፣ መሐመድ ሻፊ ፣ አንተነህ ናደው ፣ ሚኪያስ ጆጂ ፣ ኢብሳ በፍቃዱ ፣ አላዛር ሽመልስ እና ያብቃል ፈረጃን የስብስቡ አካል ማድረግ የቻለ ሲሆን ከሰሞኑም ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለመቀላቀል በሂደት ላይ የሚገኝ ይገኛል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ክለቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መቼ እና የት እንደሚያደርግ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል፡፡

በዚህም መሰረት በነገው ዕለት የክለቡ ተጫዋቾች ከተሰባሰቡ በኋላ ከሰኞ ነሀሴ 9 2014 ጀምሮ ክለቡ በቢሾፍቱ ከተማ መቀመጫውን አድርጎ ዝግጅቱን በይፋ ይጀምራል፡፡