የጣና ሞገዶቹ አይቮሪያዊ የግብ ዘብ አግኝተዋል

በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመራው ባህር ዳር ከተማ ወጣቱን አይቮሪኮስታዊ ግብ ጠባቂ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት 12ኛ ደረጃን ይዞ ያጠነቀቀው ባህር ዳር ከተማ በቀጣዩ የውድድር ዓመት ተጠናክሮ ለመቅረብ በዝውውር መስኮቱ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል። ድረ-ገፃችን አሁን ባገኘችው መረጃ ደግሞ ክለቡ አይቮሪኮስታዊውን ግብ ጠባቂ ኤሊዘር ኢራ ቴፕን አግኝቷል።

1 ሜትር ከ 92 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ግብ ጠባቂው ከአስፓየር አካዳሚ የተገኘ ሲሆን ከ2015 ጀምሮም ለሀገሩ ክለቦች ሲጫወት አሳልፏል። በሀገሩ የኦሎምፒክ ቡድን እና ዋናው ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ የተጫወተው ኤሊዘር ትናንት አመሻሽ ኢትዮጵያ የገባ ሲሆን በቅርብ ሰዓት ለጣና ሞገዶቹ ፊርማውን እንደሚያኖር ይጠበቃል።