በጉዳት ምክንያት የዋልያዎቹ ስብስብ ላይ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ተደርጓል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር ባደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ተከላካዩን በሌላ ተጫዋች ተክቷል።

በአልጄርያ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የቻን ውድድር የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታው ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር ነሐሴ 20 እና 29 ለሚኖረው ወሳኝ ጨዋታ ይረዳው ዘንድ ባሳለፍነው ሳምንት ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ከዩጋንዳ አቻው ጋር ማድረጉ ይታወቃል።

በመጀመርያው የአርቡ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ተሰልፎ የተጫወተው ያሬድ ባየህ በሁለተኛው የእሁዱ ጨዋታ እያሟሟቀ ባለበት ወቅት ባጋጠመው ጉዳት ከጨዋታ ውጪ ሆኖ ነበር። ይህን ተከትሎም ትናንት እና ዛሬ በነበሩት የሁለት ቀን የብሔራዊ ቡድኑ ልምምዶች ያልተሳተፈው ያሬድ ባየህ ነገ ወደ ታንዛኒያ የማይሄድ መሆኑ ተረጋግጧል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተም በያሬድ ባየህ ቦታ አስቻለው ታመነን መጥራታቸውን እና ነገ ወደ ታንዛኒያ ከቡድኑ ጋር እንደሚጓዝ ለማወቅ ችለናል።