ለፕሬዘዳንትነት የሚወዳደሩት አቶ ቶኪቻ ዓለማየሁ (ኢ/ር) መግለጫ ሰጥተዋል

👉 “ደካማ የክልል ፌደሬሽኖች ባሉበት ብሔራዊ ፌደሬሽኑ ላይ ጠንካራ ሰው ቢኖር ዋጋ አይኖረውም።”

👉 “ተጨማሪ የምፈልገው ገቢ ስለሌለ በፕሬዘዳንቱ ቢሮ በኩል የሚመጣውን ማንኛውም ገቢ ላለመውሰድ ቃል ገብቻለሁ።”

👉 “በ2030ዎቹ ውስጥ የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ላይ እንዲደረግ አሁኑኑ ማመልከት አለብን።”

👉 “የሚቀጥሉትን አራት ዓመታት በእኔ ዕቅድ በሁለት ዓመት እጨርሰዋለው ብዬ ነው የማስበው። የዛሬ ሁለት ዓመት ሌላ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ይኖራል የሚል ግምት አለኝ።”

👉 “በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ፊፋ መግባት ነው የምፈልገው”

በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረገው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንት እና የሥራ አስፈፃሚዎች ምርጫ ከሰሞኑ ከፍ ያለ ትኩረት ተሰጥቶታል። በፕሬዘዳንትነት ዕጩ የሆኑት ግለሰቦችም ሊሰሩ ያሰቧቸውን ነገሮች ያብራሩባቸው መግለጫዎች የተሰጡ ሲሆን ዛሬ ከምሳ ሰዓት በኋላ አቶ ቶኪቻ ዓለማየሁ (ኢ/ር) በስካይላይት ሆቴል በተመሳሳይ መግለጫ ሰጥተዋል። የኤልኔት ግሩፕ ሥር አስፈፃሚ እና በሙያቸው የሲቪል መሀንዲስ የሆኑት አቶ ቶኪቻ በቅድሚያ ያላቸውን ዕቅድ በተመለከተ ተከታዩን ገለፃ አድርገዋል።

“በቅድሚያ ሁላችሁም ሀሳቤን ለመስማት እና ለህዝብ ለማድረስ እዚህ ስለተገኛችሁ አመሠግናለሁ። ከዜግነት ጋር በተያያዘ የተወሰኑ የሚነሱ ነገሮች አሉ። ግልፅ ለማድረግ እንደማንኛችሁም ኢትዮጵዊ ውስጥ የተወለድኩ ኢትዮጵያዊ ነኝ። በኢትዮጵያ ብዙ ከተጠቀሙት መካከል ራሴን እንደ አንዱ አድርጌ እወስዳለሁ።”

“ፌደሬሽኖች ሆነ ከደጋፊው እና ሌሎች አካላት ጋር በመሆን ያለ ልዩነት የሁሉንም ሀሳብ ማድመጥ ያስችለኛል ብዬ አምናለሁ ይህም ሁሌም የምንመኘውን ልዩነት ለመፍጠር ሆነ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ያስፈልጋል። የእግርኳስ ፍቅር ያለው እና ሙያው ያለው ሰው ወደ እግርኳስ አመራርነቱ ለመምጣት ያለው መንገድ እጅግ ጠባብ እንደሆነ የአሁኑ ዕጩዎች በራሱ በቂ ማሳያ ናቸው። በመሆኑም ይህን ለማስተካከል ገለልተኛ ሰው መጥቶ መንገዱን መጥረግ አለበት።”

“እግርኳሱን ለመለወጥ ከታሰበ በተናጠል ሊሰራ የሚችል ጉዳይ አይደለም ብዬ አምናለሁ። የቀደመውን አመራር ሆነ አዲስ ወደ እግርኳሱ ሀሳብ ይዞ ለመምጣት ያቀደውን አካልን ጨምሮ ሁሉንም ባካተተ መልኩ ገለልተኛ ሰው አማካይ ሆኖ ልዩነቶችን ባጠበበ መልኩ ሀሳቦችን አጣጥሞ መንገድ ማበጀት አለበት። ይህ ደግሞ እኔን ቀዳሚ ተመራጭ ያደርገኛል። እንደምታውቁት እግርኳሱ ውስጥ ከፍተኛ መገፋፋት እና ሽኩቻ አለ። ይህም ያልተደጋገፈ ቤት ውጤት ከብሔራዊ ቡድን አንስቶ እስከ ዝቅተኛው ደረጃ ተፅዕኖ እያሳረፈ ይገኛል።”

“ባለፉት 40 ዓመታት በእግርኳሳችን እንደው አህጉራዊ ዋንጫዎችን ማሸነፍ ይቅርና ከሀገር ወጥተው መጫወት የሚችሉ ጥሩ ተጫዋቾችን ሆነ አሰልጣኞችን ማፍራት አልቻልንም። ከዚህ ባለፈ በዳኞቻችን ላይ እንኳን በቂ የልማት ሥራዎችን አልሰራንም። ይህን ለማሻሻል በርካታ ሀሳቦችን ይዘን መጥተናል።”

“አሁን እንዳለው መንግሥታዊ መዋቅር ሁሉ እግርኳሱም ፌደራላዊ አወቃቀር አለው። ከክልሎች እና ከከተማ አስተዳደሮች በተወከሉ ሰዎች በተመረጡ አካላት የሚተዳር ነው። ስለዚህ ፌደሬሽኑ እነዚህ 12 ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ አስተዳሮች ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት። ስለዚህ የፌደሬሽኑ አጠቃላይ አካሄድ ክልሎች ላይ ትኩረት በማድረግ ተጣምሮ መስራት አለበት። ምክንያቱም እነዚህ ክልሎች የተጫዋቾች ፣ የደጋፊዎች ፣ የዳኞች እና የሌሎች ግብዓቶች ምንጮች እንደመሆናቸው ወደ 120 ሚሊየን የተጠጋውን ህዝባችንን ተደራሽ ለማድረግ ኃላፊነቶች ተከፋፍለው በጋራ መስራት የግድ ይላል።ለዚህም ክልሎች ወደ ፌደሬሽን የሚልኳቸው ሆነ የሚቀጥሯቸው ሰዎች እግርኳሱን የተረዱ መሆን አለባቸው። ይህ ካልሆነ ግን ደካማ የክልል ፌደሬሽኖች ባሉበት ብሔራዊ ፌደሬሽኑ ላይ ጠንካራ ሰው ቢኖር ዋጋ አይኖረውም። ይህን ለመለወጥ እንሰራለን። አሁን ባለው አወቃቀር የክልል ፌዴሬሽኖች በብሔራዊ ፌደሬሽኑ ላይ እምብዛም ደስተኛ አይደሉም። ከሀ
ኃላፊነት አሰጣጥ እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ቅሬታ እንዳላቸው ካነጋገርኳቸው የክልል ፌደሬሽኖች ተረድቻለሁ። ስለዚህ ይህን ጉዳይ በቅድሚያ መፍታት ይኖርብናል።”

“ይህን የምናደርገው ደግሞ እግርኳሱ በቂ መዋዕለ ንዋይ መፍጠር ባለመቻሉ ፌደሬሽኖቹ መንግሥት ላይ ተለጥፈዋል። ለምሳሌ የፌደራል መንግሥት ሆነ የክልል መንግሥት ስታዲየም ካልገነባላቸው ስታዲየም መስራት አይችሉም ማለት ነው። ስለዚህ በፌደራል ደረጃ ስታዲየም ቢገነባላቸው ጠንካራ የክልል ፌደሬሽኖች ከፈጠርን እነሱ ከክልሉ ስፖርት ቢሮዎች ጋር በመሆን ሌሎች ጥቃቅን የሚመስሉ ስታዲየሞቹን ለአህጉራዊ ውድድር የሚያበቁ ሥራዎችን መስራት ይችላሉ ብዬ አምናለሁ።”

“በየክልሉ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች የሚሆኑ የታዳጊ ማዕከላት ያስፈልጉናል። በዚህም የተመረጡ ታዳጊዎች ገና ከስምንት ዓመታቸው አንስቶ በተጠና የጨዋታ መንገድ በአመጋገብ ሆነ በሌሎች ሳይሳንዊ መንገዶች የተደገፉ ሥልጠናዎችን ሊያገኙ ይገባል።”

“እግርኳሱ እስካሁን በቂ ገንዘብ እየፈጠረ አይደለም። እንደ ዓለምአቀፍ ሀገራት የእኛም እግርኳስ ይህን የመፍጠር አቅም አለው ፤ በመንግሥት ደረጃ እግርኳሱን የማሳደግ ፍላጎት አለ። ታዳጊ ተጫዋቾችን በብዛት መፍራት አለባቸው የትምህርት ቤቶች ውድድሮችም እንዲሁ በተጠናከረ መልኩ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተመልሰው መካሄድ ይኖርባቸዋል። እግርኳስ ለመጫወት ምቹ ባልሆኑ ክልሎች ላይ እንደየአካባቢው ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎ ውድድሮች መካሄድ አለባቸው። በተጨማሪም ስፖርቱን ይበልጥ ለማነቃቃት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ክለቦች መቋቋም ይኖርባቸዋል። ከዚህም ባለፈ ውድድሮች በበቂ ሁኔታ መደረግ ይኖርባቸዋል።”

“የአፍሪካ እግርኳስ ማህበርን መስረተናል። ነገር ግን አሁን ላይ በቂ ውክልና በማህበሩ የለንም ፤ በተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያዊያን በኃላፊነት እያገለገሉ ይገኛል። ታድያ በእግርኳሱም ይህን ከማድረግ የሚከለክለን የለም። የመደጋገፍ ችግር ከሌለ በስተቀር ኢትዮጵያዊያን ካፍ ውስጥ በአመራርነት የማያገለግሉበት ምክንያት የለም። አመራር ውስጥ ከሌለን ተጠቃሚነታችንም ይቀንሳል። ስለዚህ ይህን በህብረት ማድረግ እንችላለን። ከግብፅ ደውለው ‘ኑ ካፍን ምሩ’ ብለው አይጠሩንም። ይህን ለማድረግ ሰዎችን መወቅ ያስፈልጋል ፣ እንዲመርጡን ማግባባት ያስፈልጋል 120 ሚልየን ህዝብ ላለው ሀገር በካፍ ውክልና አለመኖሩ የሚያሳዝን ነው። ከእኛ በህዝብ ቁጥር ለማነፃፀር የምታስቸግረው ጅቡቲ እንኳን ከእኛ የተሻለ ውክልና አላት። በመሆኑም እኛ የሚያቅተን ስለማንደጋገፍ ፣ የሚችለውን ወደ ፊት ስለማናመጣ ፣ የእኔ ብቻ ተሰሚነት ያግኝ የሚል ሀሳብ ያጠቃናል። ይህን ደግሞ የምንክደው አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ የውጭ ጠላት ሲመጣ እንጂ አንድ ላይ ስንቀመጥ እንደጋገፍም። ይህን አስተሳሰብ ከእግርኳስ ማስወጣት ይገባናል። የተለያዩ በካፍም ሆነ በፊፋ በኃላፊነት ማገልገል የሚችሉ ሰዎች አሉ እነሱን ወደ ፊት ማምጣት ይኖርብናል።”

“እግርኳሱን በገቢ ለማሳደግ መሰረታዊው ጉዳይ እግርኳሱ አሁን ባለበት ሁኔታ መሸጥ መቻል አለበት ፤ ይህ ደግሞ ለውጭ ሀገራት ሳይሆን በቅድሚያ ለሀገር ውስጥ መሸጥ አለበት ይህን የሚያደርገው ደግሞ ደጋፊ እና ጋዜጠኛ ነው። እኔ ፕሬዜዳንት ባልሆንም እኛ ሜዳ ላይ ጥሩ እየተጫወትን ሊሆን ይችላል። ይህን የሚነገር እና የሚያስረዳ ጋዜጠኛ ግን ያስፈልጋል። ነገር ግን ጋዜጠኛው ሜዳ ላይ እየሆነ ስላለው ነገር በግልፅ ካልዘገበ ህብረተሰቡ መረጃውን ከየት ያገኛል። ሜዳ ላይ ደግሞ ሁለት ቡድኖች ሲጫወቱ ባዶ እንደመሆኑ በትኩረት እንሰራበታለን።”

“ፌደሬሽኑ በራሱ ብዙ ገቢዎች አሉት። ያውቁታል አያውቁም የሚለው ባላወቅም ገቢዎችን ከተለያዩ ምንጮች ማግኘት ይቻላል። እነዚህን ገቢዎች የመጠቀም ፍላጎት አለ። ነገር ግን አንዳንዴ ቤት ውስጥ ብዙ እቃ ይኖራል። ነገር ግን የማንጠቀምበት ከሆነ ምንም አይሰራም ፤ እዛው ይቀመጣል ምንም አይሰራም። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽንም የምመለከተው እንደዚሁ ነው። ተጫዋቾች አሉ ፣ ራሳቸው የቻሉ ክለቦች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በርከት ያሉ የከተማ ክለቦች አሉ ፣ ትልልቅ ድርጅቶች አሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሀገሪቱን በትልቁ የሚያስጠራ ተቋም ነው። ይህ ተቋም አንድ ሀገር የሚወክሉ ተጫዋቾች የሚወጡበት ክለብ ከመያዝ ምን አገደው ? ሀገሪቱ ውስጥ በርካታ ባንኮች አሉ የገንዘብ ችግር የለባቸውም ታድያ ክለብ እንዲያዙ ማድረግ ለምን አልቻልንም ? ትላልቅ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ፣ የቡና ላኪዎች እንዲሁም ሌሎች በርካታ አቅሙ እያላቸው ወደ እግርኳሱ ያልተጋበዙ አካላት አሉ። ይህን ለምን አልሆነም ስንል ለእኔ የሚታየኝ ፌደሬሽኑ በሩን ቆላልፎ ስለሚቀመጥ ነው። ለመጠየቅ ዝግ የሆነ ቤት እንዲሁም ራሱን ወጥቶ የሚጠይቅም አካል አይደለም። ለምሳሌ ሲኤምሲ ያለው የካፍ የልህቀት ማዕከል ተቆልፎ የተቀመጠ ነው። ፌደሬሽኑ አንዳንድ ንብረቶቹንም የሚይዝበት መንገድ በራሱ ጥያቄ የሚነሳበት ነው። በመሆኑም የመዋቅር ለውጥ ካስፈለገ አጥንቶ በማድረግ ወይንም ያለውን ሠራተኛ በማብቃት የተሻለ ሥራ መስራት ይቻላል።”

በመቀጠል ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ተከታዮቹ ምላሾች ተሰጥተዋል።

ወደ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት ምርጫ ከመምጣታቸው በፊት በእግርኳሱ ስለሰሯቸው ነገሮች…

“እግርኳሱ ላይ ተፈትኖ ያለፈ ባለሙያ ቢመጣ ይሻላል በሚለው እስማማለሁ። ግን እንዴት አድርጎ ይምጣ ? ነው። እኔ ደፋር ስለሆንኩ እና ‘ወክሉኝ ፤ መቀየር አለበት ‘ ስላልኩ ነው የተወከልኩት። እግርኳሱን እንደምወድም በተግባር ባዩት ነገር ነው። ስለእግርኳስ የሚያውቅ ሰው ለምሳሌ አቶ ገዛኸኝ ከአቶ ኢሳይያስ ውጪ ከእኔ እና ከአቶ መላኩ ስለእግርኳስ ያውቃሉ ፤ ግን ዛሬ የሉም እዚህ። ስለዚህ እንዴት አድርገን እናምጣ ነው። እኔ እግርኳስ አሰልጣኝ ወይም ተጫዋች ሆናለሁ ብዬ አይደለም የመጣሁት። መዋቅራዊ ለውጥ ለማድረግ የግድ የእግርኳስ ሳይንቲስት መሆን የለብኝም ብዬ ነው የማስበው። ይሄን ለማድረግ እግርኳስን የሚወድ ሰው ሲመጣ በር የማይከፈትለት ከሆነ በሩን እንዴት አድርገን እናስከፍተው ነው። ይሄን ለማድረግ የግድ አንድ ሰው መሀል ገብቶ እግርኳስን አውቃለሁ ከሚለው አካል ጋር አብሮ መስራት አለበት ብዬ ነው የማስበው። እኔ እንደማንኛውም ሰው ውጪ ቁጭ ብዬ አስተያየት መስጠት እችላለሁ። ግን አብዛኛውን ጊዜ ለውጥ እንጠይቃለን ግን አንሳተፍበትም። ካልተሳተፍን ደግሞ የሚለወጥ ነገር የለም። ሁሉም ሰው ሲሳተፍ ነው ለውጥ የሚኖረው። ምርጫውን አሸንፌ እኔ እንደግብ ያስቀምትኳቸው ነገሮች ከግብ ካደረስኩ ዋንጫ ለማንሳት አራት ዓመቱን ጨርሳለሁ የሚል ግምት የለኝም። እግርኳሱ ላይ ልዩነት የሚፈጥሩ ሰዎች ቦታ እንዲይዙ አቅም ከፈጠርን በፌዴሬሽን ደረጃም በክልል ደረጃም ምርጫውን አሳጥሮ መጥራትም ይቻላል ለባለሙያ። ያለባለሙያም ደግሞ ሥራ አይሰራም። መዋቅራዊ ለውጥ ስናደርግ የእግርኳስ ባለሙያዎችን ሙሉ ለሙሉ አሳትፋለሁ።”

በድሬዳዋ በነበራቸው ቆይታ ከሜዳዎች ጋር በተያያዘ ስለሚነሱ ጥያቄዎች…

“ማንኛውም ለእግርኳስ የተመደበ ሜዳ ለሌላ ጥቅም እንደማይውል አረጋግጣለሁ ፤ ድሬዳዋ ላይ። ተጨማሪ ሜዳም ይፈልጋል ብዬ ነው የማስበው። አዲስ አበባ ላይም መታሰብ ያለበት ነገር ነው። ሜዳዎች ያስፈልጋሉ ፤ ሜዳዎች ላይ ያሉ ውዝግቦችም መጥራት አለባቸው። ለእግርኳስ እስከሆኑ ድረስ ለሌላ ነገር መዋል የለባቸውም። እዚህ እንደሆነው መሆን የለበት። አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ለእግርኳስ የተያዙ ቦታዎች ኮንዶሚኒየም ነው የተሰራባቸው። ያ ይደገማል ብዬ አልገምትም። እያንዳንዱ ከተማ ላይ አዲስ አበባም በእያንዳንዱ ክፍለከተማ ክፍለሀገር ላይም ደረጃቸውን የጠበቁ ሜዳዎች ያስፈልጋሉ ፤ ስዎች የሚጫወቱበት ፣ የሚለማመዱበት። እንዲሁ ስፖርት ራሱ ለጤንነት ነው። ህብረተሰቡ ራሱ ስፖርት መስራት መቻል አለበት። አሁን አብዛኛው ትናንሽ ከተሞች ላይ ሰዉ በእግሩ መሄድ አቁሟል ፤ በባጃጅ ነው የሚሄደው። በዚህም ከሰውነት እንቅስቃሴ እጥረት ጋር በፊት ያልነበሩ በሽታዎች እየመጡ ነው። ለዚህ ሜዳ ላይ ያለኝ ነገር ይህንን ነው የሚመስለው።”

ስለሴቶች እግርኳስ…

“120 ሚሊየን ስል ወንድ እና ሴት አላልኩም። የሴቶች እግርኳስም ዕኩል ማደግ ያለበት ነው። በውጤት ደረጃ ካየነው የሴቶች እግርኳስ የተሻለ ቦታ ላይ ነው ያለው። ግን የበለጠ ኢንቨስትመንት ፣ ማበረታቻ እና ግንዛቤ ማስጨበጫ ይፈልጋል ፤ ሴቶች እህቶቻችን ወጥተው እግርኳስ መጫወት እንዲችሉ በማስተማር እና ስኬታማዎቹን ሴቶች በደንብ ማስተዋወቅ ይፈልጋል። እዚህ ላይ በደንብ መሰራት አለበት።”

በሚመሩት የንግድ ድርጅት ክለብ የመመስረት ሀሳብ ያላቸው ስለመሆኑ…

“የሚመጣው ዓመት ላይ ትንሽዬ ክለብ ይኖረናል ብዬ ነው የማስበው። ትልቅ ክለብ ከታችኛው ዲቪዚዮን መጀመር አለብን የራሳችንን ክለብ እናቋቁማለን ብለን እናስባለን። ወይም ያሉት ላይ የመጨመር ሀሳብ አለን።”

በፌዴሬሽኑ ከባቢ ውስጥ ስላለው የጥቅም ሽኩቻ እና በእግርኳሱ ውስጥ ስላለው የዘረኝነት ችግር…

“ፌዴሬሽኑ ወደ መጀመሪያ ዓላመው መመለስ አለበት ብዬ ነው የማስበው። የሆነ ሀገር ላይ ሄደን ጥሩ ተጫውተን ብንመለስ ፤ ሜዳ ላይ ጥሩ ሥነምግባር አሳይተን ብንመለስ ፣ ዋንጫ አሸንፈን ብንመለስ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች የሚያደርገን ነገር ነው። ጥቅማ ጥቅም አገልግሎት በመስጠት የሚገኝ እንጂ ከፌዴሬሽኑ ላይ የሚገኝ ነው ብዬ አላስብም። ይሄንን የሰውየው የኢኮኖሚ ሁኔታ ይወስነዋል። ለሁሉም ተመሳሳይ መመዘኛ አወጣለሁ ብዬ አላስብም። በራሴ በኩል ግን ተጨማሪ የምፈልገው ገቢ ስለሌለ በፕሬዘዳንቱ ቢሮ በኩል የሚመጣውን ማንኛውም ገቢ ላለመውሰድ ቃል ገብቻለሁ። እኔ ከአሁን በኋላ እግርኳስ ተጫዋች ወይም ወታደር መሆን አልችልም። ወደ ፖለቲካም መሄድ አልፈልግም። እግርኳስ ሁሉም ማሕበረሰብ የሚገናኝበት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኳስ አይቶ ተደስቶ ወደ ቤቱ የሚገባበት ቦታ ነው እና ሁላችንንም ያማከለ ቦታ ነው ብዬ ነው የማስበው። በተለያዩ ምክንያቶች ተከፋፍለን ነው ያለነው አሁን ላይ። ይሄን ክፍፍል ያስቀራል የሚል ሀሳብ አለኝ። እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሁሉም ከተሞች ላይ መሄድ እፈልጋለሁ። ብሔር ማጥፋት አንችልም ፤ ችግሩ ዘረኝነቱ ነው። ዘረኝነቱን ማጥፋት እንችላለን። ብሔር እኛ ሳንኖርም ነበር ወደፊትም ይኖራል። እኛ እዚህ ውስጥ እየጨመርን ያለነው ዘረኝነቱን ነው። እግርኳስ ዘረኝነትን ያጠፋል ብዬ ነው የማስበው። ሁለት የማይታወቁ ቡድኖች ሲጫወቱ ቁጭ ብሎ ስለነሱ ዘር የሚወያይ ሰው አይኖርም። ወይ ደግሞ ስለሰውየው ሐይማኖት ወይ የፖለቲካ አመለካከት የሚወያይ ሰው አይኖርም። ጎበዝ ተጫዋች ከሆነ ጎል ካገባ እናጨበጭብለታለን። ከዚህ ያለፈ ነገር የለውም እግርኳስ። የሚያፎካክሩ ውድድሮች ጥሩ ናቸው። ጊዮርጊስ እና ቡና መሀል ያለው ፉክክር ለምሳሌ የእግርኳስ እንጂ የዘር ወይ የሐይማኖት አይደለም። ጥቅም ፈላጊ ካልሆንክ ልዩነት ላይ አትሰራም ፤ አንድ የሚያደርግ ነገር ላይ ነው የምትሰራው። ለእግርኳሱ የተሻለ ጥቅም ከተባለ የጎጠኝነት ነገርን ማጥፋት ይፈልጋል። ‘እኔ የማውቀው ሰው እዚህ ቦታ ካልተቀመጠ ፣ እኔ የምወደው ክለብ እንዲህ ካልሆነ’ የሚለው ለእግርኳሱ ምንም አይጠቅመውም። ”

በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ተሰይሞ የነበረው እና አሁን ላይ የተቀየረው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ስያሜን ወደነበረበት ስለመመለስ…

“ሁሉም ኢትዮጵያዊ መከራከር አለበት ብዬ ነው የማስበው። ትዊተር እና ፌስቡክ ላይ ስንሰዳደብ ነው የምንውለው ፤ የካፍ ፔጅ ላይ ሄዶ ሁሉም መፃፍ አለበት። ይሄ ውድድር በሳቸው ስም ሲሰየም አስታውሳለሁ። ከሌላ አፍሪካ ሀገር ሌላ ሰው ተመርጦ በስሙ የተሰየመ ነገር የለም። ካፍ ውስጥ የመጀመሪያው እሳቸው ናቸው። ስማቸው ወደ ቦታው እንዲመለስ ሁላችንም ከዛሬ ጀምሬ ሎቢ ማድረግ አለብን ብዬ ነው የማስበው ፤ እስከሚሰለቻቸው ድረስ መፃፍ። ለነገር ሲሆን ስንፅፍ ነው የምንውለው ፤ ለጥሩ ነገር አያቅተንም ብዬ ነው የማስበው። እኔም በግሌ ፕሬዘዳንት ሆንኩም አልሆንኩም ካፍ እና ፊፋ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በማውቀው ዳረጃ በመጫን ስያሜው እንዲመለስ በአቅሜ እሰራበታለሁ ፤ እናንተም መተባበር አለባችሁ። ”

ስለስትራቴጂክ ዕቅዳቸው እና ቅድሚያ ስለሚሰጡት ሥራ…

“ያዘጋጀነው አለ ፤ እኔ ብቻዬን ሳይሆን ሰዎች ተቀጥረው ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅታናል። ማን እንዳዘጋጀው ወደፊት እያሳወቅን እንሄዳለን። ‘የመጀመሪያ ሥራህ ምንድነው ?’ ለሚለው የሚመጣው ዓመት ዋንጫ እንበላለን የሚል ዕቅድ ይዤ አልመጣሁም። የዛሬ አራት ዓመትም ዋንጫ እበላለሁ ብዬ አልመጣሁም። የእኔ ዕቅድ ከእኔ ቀጥሎ የሚመጣው ፕሬዘዳንት በሚኖረው ተጫዋች ዋንጫ እበላለሁ ብሎ እንዲናገር የሚያስችለው መደላድል እንዲኖረው ለመስራት ነው የመጣሁት። ይህን ለማድረግ ተጫዋቾች ፣ ዳኞች ፣ አሰልጣኞች ላይ መስራት ይጠይቃል። እኔ ሁሉንም ሰው ወደ ፌዴሬሽኑ መጎተት ነው የመጀመሪያ ስራዬ። ማንኛውንም ነገር ፅፌ ብመጣ አሁን ያሉ እግርኳሱ ዓለም ላይ ካሉ ሰዎች ጋር ካልሰራሁ ምንም ልዩነት ልፈጥር አልችልም። ስለዚህ እነዚህን ሰዎች ማሳመን ላይ ነው የምሰራው። ሌላው በዕቅድ የያዝኩት የበፊት ፕሬዘዳንቶች እና ምክትል ፕሬዘዳንቶች ካውንስል አቋቁማለሁ ብዬ ነው የማስበው። ከእነሱ ምን ሰሩ ምን አልሰሩም ፣ ምን አቅደው ምን ላይ ተሳሳቱ ፣ ስኬታቸው እንዳለ ሆኖ እሱን እንዳለ ቀጥሎ የወደቁባቸው ቦታዎች ላይ ለምን ወደቁ ? እኛ ያቀድነው ውስጥ ድጋሚ እያቀድነው ነገር አለ ? የሚለውን ማወቅ አለብን። እነሱ የሰሩትን ድጋሚ ሀ ብለን መጀመር አለብን ብዬ አላስብም። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ እነሱ ራሳቸው ቢሮ መጥተው የሚረዱበት መንገድ መፈጠር አለበት ብዬ ነው የማስበው። እንደዚሁም የክለብ ባለቤቶች እና የክለብ አመራሮች ራሱን የቻለ የተለዩ ሀሳቦችን የሚያመነጭ ካውንስል አደራጃለሁ ብዬ ነው የማስበው ፤ በደጋፊዎች እና ለጋዜጠኞችም እንዲሁ።”

ስለ አጭር እና ረጅም ጊዜ ዕቅዶቻቸው…

“ልናሳካቸው የምንፈልጋቸው የአጭር ጊዜ ዕቅዶች አሉን። እኔ ያተኮርኩት እግርኳሱን ማሻሻል ይችላሉ የሚሉ ነገሮች ላይ መስራት አለብን ብዬ ያስቀመጥኳቸው ነጥቦች አሉ። እነዚህን ለመስራት ፌዴሬሽኑ ከነበረበት ባህላዊ አስተዳደር መውጣት አለበት ባይ ነኝ። አሁን ያለው የፌዴሬሽኑ አስተዳደር በተለምዶው አሁን ያለውም ከዚህ በፊት የነበረውም የፈለገውን የሚያደርግ ፌዴሬሽን ነው። ‘ለምን ይሄን አደረክ ?’ ብሎ የሚጠይቀው አካል እስካሁን አላየሁም። ተጠያቂነት እንዲኖረው ካልተደረገ መሰረታዊ ለውጥ ቢደረግም ለውጡን የሚከተል አካል አይኖርም ማለት ነው። ስለዚህ እኔ ፌዴሬሽኑ የሚተዳደርበት ህገ ደንብም ፣ ከክለቦች ጋር የሚገናኝበትም ፣ መሰረታዊ የእግርኳስ ዕድገት ላይ የሚሰራባቸውን መሰረቶች እጀምራለሁ ብዬ ነው የማስበው። እኔ ይሄንን ካሳክሁ አራት ዓመት ከወሰደ አራት ዓመት ፤ ሁለት ዓመት ከወሰደ እና እነዚህ እግርኳስ ላይ ሙያ ያላቸው እና ፌዴሬሽነን መምራት ያለባቸው አካሎች ወደ ፌዴሬሽኑ እንዱገቡ ዕድል ከሰጠን እኛ በፍላጎት የመጣን ሰዎች ዞር ማለት አለብን ብዬ ነው የማስበው። ሌላ የሚሰራ ብዙ ስ
ሥራ አለ። ክለብ መስርቶ የክለብ ባለቤት መሆን ይቻላል ፣ ውጪም ሆኖ በኢኮኖሚ መርዳት ይቻላል።”

ፌዴሬሽኑን በገቢ ከማጠናከር አንፃር ስላላቸው ሀሳብ…

“እግርኳሱ እንደቢዝነስ መታየት አለበት። የፈለገውን ቢዝነስ መስራት የሚከለክለው ነገር የለም። መንግሥት የሰጠው ህግ አለ። የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችን ማቋቋም ይችላል ፌዴሬሽኑ። መነገድ የሚከለክለው ነገር የለም። እንዲያውም ግብር አይከፍልም ቢነግድ። የራሱን ምርቶች መሸጥ ይችላል ፣ ሀገሪቷ ላይ ብዙ አቋማሪ ድርጅቶች አሉ ከእነሱ ብዙ ፍላጎቶች አሉ። የኢትዮጵያ እግርኳስ በፈጠረው ሚሊየኖችን ካገኙ የተወሰነ ነገር ማዋጣት አለባቸው ብዬ ነው የማስበው። ይሄ ደግሞ መደራደር ይፈልጋል፣ መነጋገር ይፈልጋል። የፕሬዘዳንት ቢሮው ፖለቲካል ክፍሉን ፣ የእግርኳስ መዋቅሩን ከሰራ ባለሙያዎች ደግሞ ይኖሩናል። በተለይ ብሔራዊ ቡድኑን በተመለከተ እነሱን መርጦ ሌላ ሀገር ልኮ ማሰልጠን ፣ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ መሰል ነገሮችን በጎን እንሰራለን። የዛሬ አራት ወይ ሁለት ዓመት ከ16 ዓመት በላይ ያሉት ላይ አተኩረን ከሰራን ጠንካራ ተጫዋቾችን ማድረስ ይቻላል። አህጉራዊ ውድድር ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል ነገር ማድረግ እንችላለን። ሌላው በ2030ዎቹ ውስጥ የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ላይ እንዲደረግ አሁኑኑ ማመልከት አለብን ብዬ ነው የማስበው። እስከ ሀያ መጨረሻ ብትሄዱ ተይዘዋል በተለያዩ ሀገሮች። ቀደም ብለን አመልክተን ሜዳዎቻችንን ፣ ተጫዋቾቻችንን ማዘጋጀት ላይ እንሰራለን። ይሄ ለሚቀጥለው ፕሬዝዳንት ነው የሚሰራው ማለት ነው። በዚህ መሰረት የረዥም ጊዜ የ20 ዓመት ዕቅድ አለን። በየአራት ዓመቱ ሰባብረን ያስቀመጥነው አለ። በዛ መሰረት ነው አስተሳሰባችን። በዚህ መሰርት ሁሉንም ካማከልን እና ተባብረን ከሰራን እኔ የጀመርኩትን አሻሽሎ ይቀጥላል እንጂ ሀ ብሎ ይጀምራል ብዬ አላስብም። እኔ ራሴ ዛሬ አዲስ እጀምራለሁ አልልም። ከነበሩት ተቀብዬ ወደ ቀጣዮቹ አሸጋግራለሁ የሚል ሀሳብ ነው ያለኝ።”

ወደ ካፍ እና ፊፋ የመሄድ ሀሳብ ይኔራቸው እንደሆን…

“በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ፊፋ መግባት ነው የምፈልገው። ካፍ ሌሎች ኢትዮጵያዊያኖች አስገባለሁ ብዬ ነው የማስበው ፊፋም ሌሎች ኢትዮጵያዊያኖች አስገባለሁ ብዬ ነው የማስበው። የሚቀጥሉትን አራት ዓመታት በእኔ ዕቅድ በሁለት ዓመት እጨርሰዋለው ብዬ ነው የማስበው። የዛሬ ሁለት ዓመት ሌላ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ይኖራል የሚል ግምት አለኝ። መሰረታዊው ጉዳይ የእኔ ፕሬዘዳንት ሆኖ መቀመጥ ስላልሆነ። እኔ ለሰዎች መሸጋገሪያ ልሁን ብዬ ነው የመጣሁት ፤ መሀል ሜዳ ልሁን ብዬ ነው የመጣሁት። ያ የመሀል ሜዳ ጉዳይ ሲያበቃ እዛ የሚያቆየኝ ነገር አይኖርም። ከእዛ በኋላ ብቁ የሆነ ባለሙያ ቦታውን ይይዛል የሚል ሀሳብ አለኝ። ከዛ በኋላም እንደዛ መሆን አለበት። ይሄን እኔ ብቻዬን አላደርገውም። በተለይ ጋዜጠኞች የበለጠ ሚና መጫወት አለባቸው። አንድ ፌዴሬሽን ለእግርኳሱ ብቁ ያልሆነ እና ግድ የሌለው ሰው ሲልክ ለምን ? ብሎ የሚጠይቀው ሰው ከፖሊስ በላይ ከመንግሥት በላይ ጋዜጠኛ ነው። እኛም በተቻለ መጠን መረጃ እንሰጣለን። ክልሎችንም ፌዴሬሽኖችንም ሄደን እናናግራለን። እግርኳሱን የሚጠቅም ከሆነ እግር ላይ ዋድቀን መለመን ካለብንም ወድቀን እንለምናለን። ከእግርኳሱ ከሚያገኘው ጥቅም በላይ ጊዜውን የሰጠ ሰው ካገኘን አሁን የምናወራቸው ችግሮች አብዛኞቹ ይጠፋሉ ብዬ ነው የማስባው። ኢትዮጵያዊያኖችን ወደ ካፍ መላክ እፈልጋለሁ። የግድ ደግሞ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ያልያዘ ከሆነ ካፍ የሥራ ቦታ ነው ቢያንስ በኢትዮጵያዊያን ደረጃ ሰዎች እንዲቀጠሩ ማድረግ ይቻላል። የሌላ ሀገር ፓስፖርት ቢኖረውም ኢትዮጵያዊ እስከሆነ ድረስ ስለ እኛ የሚቆረቆር ሰው ካገኘው እዛ እንዲገባ ፍላጎቱ አለኝ። አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብለህ የውጪ ግንኙነት በስልክ አይሰራም። እኛን የሚወክሉ መአት ኢትዮጵያዊ ያኖች ዓለም ላይ አሉ። እነሱን መጠቀም ያስፈልጋል።”

የድርጅታቸውን አርማዎች በመግለጫው ላይ ስለመጠቀማቸው…

“እኔ ነጋዴ ነኝ። ባገኘሁት ዕድል ሁሉ ድርጅቴን አስተዋውቃለሁ። ድርጅት መምራት ላይ ልምድ እንዳለኝ ለማሳየትም ነው። እነዚህን ድርጅቶች ሁሉ እኔ አይደለሁም የምመራው። እኔ አንድ ቦታ ላይ እቀመጣለሁ። ሌላው ደግሞ ሁሉም የራሱ ሥራ አስፈፃሚ አለው። እኔ የማምነው ከሰዎች ጋር በመስራት ነው።”

በፌዴሬሽኑ እና በታክሲዬ መካከል ስላለው የስፖንሰርሺፕ ጉዳይ…

“ሄደው ስፖንሰር እንዲያደርጉ ሀሳቡን የሰጠኋቸው እኔ ነኝ። አብዛኛው ድርድር ውስጥ አልነበርኩም ፤ ድርጅቱን የሚመራው አካል ስላለው። ከማውቀው እና ከጠየኩት ስመልስ ውል ገቡ ፤ ውል የተገባበት አካሄድ አለ ፤ ፌዴሬሽኑ ሊያስተዋውቃቸው እነሱ ደግሞ ብር ሊሰጡት። እንጂ ከፌዴሬሽኑ የሚያገኙት ሌላ የተለየ ነገር የለም። ጊዜውን እርግጠኛ ባልሆንም እኛ ነን ሄደን ስፖንሰር እናድርጋችሁ የሚል ጥያቄ ያነሳነው ፤ እንጂ እነሱ መጥተው አልጠየቁም። ጠይቀውም የሚያውቁ አይመስለኝም። የእኔን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም የጠየቁ አይመስለኝም። የራሳቸው ፓኬጅ አላቸውም። ፌዴሬሽኑ የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ አንዳንድ ነገር ላይ እንረዳችኋለን በሚል ነው ንግግሩ የጀመረው። ኃላፊነቱን የሰጠሁት እኔ ነኝ ፤ ሂዱ እና ስፖንሰር አድርጉ ያልኳቸው። እግርኳስ ክለቦችን ስፖንሰር ቢያደርጉ የተሻለ ገበያ ያገኛሉ። ለዋልያ የሚሰጠውን እና ለሌሎች ክለቦች የሚሰጠውን ብር ብናስተያይ ማንኛውም ጨዋታ ላይ ድርጅቱ እንዲኖር ማድረግ ይችላል ብዬ ነው የማስበው። ግን ዋናው ውላችን የሚለው እነሱ የድርጅቱን ሊያስተዋውቁ ነው። ግዴታችሁን አልተወጣችሁም በሚል ማስተካከያ ፅፈንላቸዋል። መልስ እየጠበቅን ነው ከፌዴሬሽኑ። አንድ ሦስት ደብዳቤ ፅፈን እስከዛሬ መልስ አላገኘንም። ለጊዜው አቆምን እንጂ አላቋረጥንም። የአንድ ዓመት ኮንትራት ነው ያለን 25% በየአራት ወር ነበር የምንከፍለው። ሌላው ዓለም ላይ እኔ ስፖንሰር ሆኜ አንተ ማርኬት አደርጋለሁ ብለህ ብር ከወሰድክ በኋላ ካላረክ ካሳ ሁሉ ይጠይቃል። እኛ ወደዛም አልሄድንም። አስተካክሉ ክፍያውን እንቀጥላለን የሚል ደብዳቤ ነው የሰጠናቸው። ሌላው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ካሜሩን ሲሄድ እንደኔ አስተሳሰብ እኔንም ወክለው ነው የሚሄዱት ፤ አምባሳደር ናቸው፡፡ እዛ ለሚሄዱት ሁሉ ልብሳቸውን እኛ ነን ያሰራንላቸው፡፡ የወጣው ወጪ ወደ 1 ሚሊዮን ብር ይጠጋል፡፡ የባህል ልብስ ለተጫዋቾቹ አንድ ዓይነት ለአመራሮችና ኃላፊዎች ደግሞ አንድ ዓይነት አድርገን ነው ያሰራነው፡፡ ይሄን በራሳችን ፍላጎት ነው ያደረግነው፡፡ ቡድኑ እኛን ወክሎ ኢትዮጵያን ወክሎ እየሄደ ነው የሚለውን አስተሳሰብ ስለያዝን ነው፡፡ ከስፖንሰርሺፕ ጋር አይገናኝም ለብቻው የተሰራ ነው፡፡ ዋልያው እየሄደ ነው ብቁ ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡ ሌላ አፍሪካ ሀገር ስትሄዱ እና ከኢትዮጵያ ነን ስትሉ እንደ ንጉስ ነው የሚንከባከቧችሁ፡፡ ስንሄድም የሰው ሀገር ከፍ ባለ ሁኔታ ነው ራሳችንን ማሳየት አለብን ብዬ የምገምተው፡፡ ሰው ከፍተኛ ቦታ እየሰጠን እኛ እንደ ዝቅተኛ ከሆንን መጨረሻ ላይ የምናስንቀው ሀገሪቷን ነው፡፡ ተጫዋቾቹ ሀገሪቷን ወክለው ስለሚሄዱ አርገናል ነገም ከነገ ወዲያም እናደርጋለን፡፡ ለደጋፊዎች ደግሞ የታክሲዬ ብራንድ ተደርጎበት 700 ማልያ ታተመ፡፡ የተወሰነው ካሜሩን ለሚሄዱት መሰጠት ነበረበት ቀሪው ደግሞ እዚህ ከተማ ውስጥ መሸጥ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ለእኛም ሳይሰጡን ተቆልፎበት ነው የሄደው፡፡ እስካሁን ተቀምጧል፡፡”

ስለስታዲየም ግንባታዎች…

“ፌደሬሽኑ የገንዘብ ችግር የለበትም፡፡ እዛ ያለ ሰው ገንዘቡን እንዴት እንዲጠቀም አያውቅበትም እንጂ፡፡ ለምሳሌ የባህር ዳር ስቴዲየም መብራት የለውም ተብሎ ነው ጨዋታ እንዳያስተናግድ የተከለከለው፡፡ ጨዋታው በቀን ነው የሚካሄደው መብራት ምን ያደርጋል ብሎ ተከራክሮ የሚያሳምን ሰው ነው የታጣው እንጂ ማንኛውም የእግርኳስ ተጫዋች ሊጫወትበት ይችላል፡፡ በዶክተር አሸብር ወቅት ጭቃ ይሆናል ተብሎ ሲተች የነበረ ሜዳ ላይ ተጫውተናል፡፡ ባህር ዳር ያሉ ሀብታሞች ስለሜዳ ጉዳይ እና ማሻሻል እንደምንፈልግ ስነግራቸው የፈለግከውን እናደርጋለን ነው የሚሉት፡፡ ፕሬዝዳንት ስትሆን ደግሞ ደብዳቤ ፅፈህ መጠየቅ ትችላለህ፡፡ አለበለዚያ ቁጭ ተብሎ ገንዘብ አይመጣም፡፡ ነጋዴ ለማስታወቂያ ወጪ እንደሚያወጣ ሁሉ ባለሀብቶችን በመቅረብ ይህ ያንተ ከተማ ነው ይህን ለመስራት አስበናል ቢባል ፈቃደኛ ይሆናል፡፡ አቶ ወርቁ አይተነው ፣ አቶ በላይነህ ክንዴ ፤ ወ/ሮ ትልቅሰው ጋር ደውያለሁ እና ችግር የለውም ለስቴዲየሙ የጎደለውን እናሟላለን ነው የሚሉት፡፡ ሜዳ የለንም የሚባለው የስንፍና ወሬ ነው እንጂ እኔ አይመስለኝም፡፡ 10ኛ ዓመቱ ነው እዚህ ያለው ሜዳ… ለምን 10 ዓመት እንደፈጀበት ምክንያት መስጠት ይቻላል፡፡ እንደ ፌደሬሽን የአሁኑ የፊፋ ፕሬዚዳንት ለአፍሪካ ሀገራት ስቴዲየም አሰራለሁ ብለው በገቡት መሰረት ማመልከቻ በማስገባት ስጠኝ ተብሎ አልተጠየቀም፡፡ እኔ በሰማሁት መሰረት ፊፋ እኔ ገንዘቡን ይዤ ስቴዲየሙን አሰራለሁ ይላል ኢትዮጵያ እና ሌሎች ሴንትራል አፍሪካ ሀገራት ገንዘቡ ይሰጠን እና እኛ እናሰራለን የሚል ግብግብ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ሜዳ እንዲሰራልኝ ከፈለኩ ለምን የቻይና መንግሥት አይሆንም የሚሰራልኝ ቦታውን ማዘጋጀት ነው፡፡ እኔ ገንዘቡን ካልተቆጣጠርኩ የሚል ነገር ከየት መጣ ፊፋ የሚበጅተውን በጀት ለማውጣት እና ለመጠቀም ልምድ ያስፈልጋል፡፡ እኔም ይሄ ልምድ አለኝ እያልኩኝ ነው፡፡”

የምርጫው ቦታ ስለመቀየሩ…

“ምርጫው ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ መጣ የተባለበት ምክንያት አንድ የቢሮ ኃላፊ ጉባኤውን ረብሻለው አለ ነው የተባለው፡፡ አዲስ አበባ ላለመረበሹ ምን ዋስትና አለው ? ጎንደር ከተማን እረብሻለሁ አላለም፡፡ ጉባኤውን እስካለ ድረስ ማስቀረቱ ያን ያህል ጥቅም አለው ብዬ አላስብም፡፡ ጉባኤው እንዳይረበሽ የሚደረጉ ነገሮችን አርጎ በዛው መቀጠል ይቻላል የሚል ሀሳብ ነው ያለኝ፡፡ ስሜታዊነት የሞላበት ውሳኔ ነው የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ ይሄ ደግሞ የሚሆነው ቤቱ የአንድ ሰው ብቻ ሲሆን ነው፡፡ የተባለው ሰውዬ ወይ ይመጣል ወይ አይመጣም ወይ ሰው ይልካል የሚለውን ነገር አላወቅኩም፡፡”

ስለምርጫ ሽኩቻው…

“ማንኛውም ምርጫ ያለበት ቦታ ጭቅጭቅ አለ፡፡ ገና ብዙ ነገር ይባላል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ገደብ ቢያደርጉበት ይሻላል የሚል ዕምነት ነው ያለኝ፡፡ ለእግርኳሱ የሚቆረቆሩ ከሆነ አስተያየታቸውን በዛው ቢወስኑ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ላልመረጥ እችላለሁ እና የበፊቱ ፌደሬሽን ምንም አልሰራም ማለት እና ማጥላላት አግባብ ነው ብዬ አላስብም፡፡ አንድ ከእግርኳስ መጥፋት አለበት ብዬ የማስበው ነገር ይሄ ነው፡፡ እኔ የዚህ አካል ስላልሆንኩኝ ይደግፉኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ የትኛው አካል ከየትኛው ጋር አብሮ ይቆማል ብትለኝ ጊዜ ኖሮኝ ስላላየሁት ልነግርህ አልችልም ግን ከእኔ በኩል አይደለም፡፡ ምርጫ ባለበት ቦታ ሽኩቻዎች አሉ፡፡ እነዚህን ሽኩቻዎች እንደ ዕድል መጠቀም አስፈላጊ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ሰው እያጣን ኳስ ቢኖረን ጥቅም የለውም፡፡ አሁን የመጡት ሰዎች ኳሱን አሻሽላለሁ እንጂ አጠፋለሁ ብለው አልመጡም ስለዚህ ሌላ ነገር ውስጥ መገባት የለበትም፡፡ እነዚህ ሰዎች ምርጫ ባያሸንፉ ለእግር ኳሱ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ ነው እንጂ አልተሳካም ብሎ መሸኘት አያስፈልግም፡፡ ፕሬዝዳንት ቢሆኑም ባይሆኑም ሀሳባቸውን ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡”

በምርጫው ቢሸነፉ በቀጣይ ስለሚኖራቸው ዕቅድ…

“ባልመረጥም የትም አልሄድም፡፡ ለባለሙያዎቹ እና ለእግርኳስ አፍቃሪዎቹ ፕላትፎርም እሆናለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡ የራሳቻንን ክለብ እንደዚሁም ሌላ ክለብ ላይ ተጨምረን የክለብ ባለቤት እንሆናለን ብለን እናስባለን፡፡ ፊፋ ላይም መመረጥ እችላለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡ የግድ ኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ መሆን የለብኝም እዛ ውስጥ ለመግባት፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ብሰራ ደስ ይለኛል፡፡ በፊፋ በኩልም ኢትዮጵያን መርዳት እችላለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡”