የሱዳኑ ክለብ ኤል-ሜሪክ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታውን ባህር ዳር ስታዲየም ላይ ያከናውናል

የሱዳኑ ክለብ ኤል-ሜሪክ ከጅቡቲው አርታ ሶላር ጋር የሚያደርገውን የሜዳ ላይ ጨዋታ በባህር ዳር ስታዲየም እንደሚያደርግ ታውቋል።

የቀጣዩ ዓመት የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከቀናት በኋላ መደረግ ይጀምራሉ። የሀገራችን ተወካዮች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማም ለውድድሮቹ እየተሰናዱ የሚገኙ ሲሆን የሜዳ ላይ ጨዋታቸውንም በባህር ዳር ስታዲየም እንደሚያከናውኑ ይፋ መሆኑ ይታወሳል። አሁን ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት የሱዳኑ ክለብ ኤል-ሜሪክ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከጅቡቲው አርታ ሶላር ጋር የሚያደርገውን የሜዳው ላይ ጨዋታ በሀገራችን ለማከናወን ወስኗል።

የሱዳኑ ክለብ አል-ሂላል ኡንዱርማን ላይ አል-ሂላል ስታዲየምን ለመጠቀም ካፍ ፍቃድ ቢሰጠውም የከተማው ተቀናቃኝ ክለብ ሜሪክ ግን እንዲጠቀምበት አለመፈለጉን ተከትሎ ሜሪክ የሜዳ ላይ ጨዋታውን ከሀገር ውጪ ለማከናወን ግዴታ ውስጥ ገብቷል። ይህንን ተከትሎም ክለቡ የባህር ዳር ስታዲየምን ለመጠቀም እንደወሰነና ለካፍ እንዳሳወቀ አረጋግጠናል። ሜሪክ በባህር ዳር ስታዲየም ጨዋታውን የሚያደርገው መስከረም 7 ነው።

ክለቡ በነገው ዕለት ከሂላል አል-ሳሂል ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን ሀገሩ ላይ አድርጎ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ዝግጅቱን እንደሚያከናውን ታውቋል። ምናልባትም ከወሳኞቹ ጨዋታዎች በፊት የዝግጅቱን ጊዜ ኢትዮጵያ ላይ ሲያደርግ ከአንድ የሀገራችን ክለብ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ እየተጣረ እንደሆነ ተገልጿል።