ጋምቢያዊው አጥቂ ዐፄዎቹን ተቀላቀለ

በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የሚወክለው ፋሲል ከነማ ጋምቢያዊ ዜግነት ያለውን አጥቂ በዛሬው ዕለት የግሉ አድርጓል፡፡

የተጠናቀቀውን የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ በመቻሉ በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያን የሚወክለው ፋሲል ከነማ ለዚህ ውድድር እና ለቀጣዩ የሀገር ውስጥ ውድድር አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ እየቀላቀለ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለት የ24 ዓመቱን ጋምቢያዊ አጥቂ ጋይራ ጆፍን በአንድ ዓመት ውል ማስፈረሙን በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

የፊት መስመር አጥቂው አብዛኛዎቹን የእግር ኳስ ህይወቱን በእስራኤሎቹ ቤን ይሁዳ ፣ ራማት ሀሻሮን ፣ ሀፓል ቤንሎድ እና ኡማ አል-ፋሀም በተባሉ ክለቦች ተጫውተ ያሳለፈ ሲሆን ወደ ጆርጂያ አምርቶ ኤፍ ሲ ዲላ በተባለ ክለብም ቆይታን አድርጓል፡፡ ያለፈውን የውድድር ዘመን ወደ ሀገሩ ጋምቢያ በመመለስ ለዋሊዳን ክለብ ሲጫወት ያሳለፈ ሲሆን ከሰዓታት በፊትም ወደ ሀገራችን መጥቶ የፋሲል ከነማ ተጫዋች ሆኗል፡፡

ዐፄዎቹ በአሰልጣኝ ሀይሉ ነጋሽ እየመሩ በባህርዳር ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ላይ መሆናቸው ይታወሳል፡፡