ከነገው የፋሲል ከነማ ጨዋታ አስቀድሞ ወቅታዊ መረጃዎችን እናጋራችሁ

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን የሚወክለው ፋሲል ከነማን የተመለከቱ ወቅታዊ መረጃዎች እንደሚከተለው አጠናክረናል።

ፋሲል ከነማ በ2014 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመንን ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቁን ተከትሎ በአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ካፕ ሀገራችንን እንደሚወክል ይታወቃል። ካፍ ባወጣው የቅድመ ማጣርያ መርሐ-ግብር መሠረትም የመጀመርያ ጨዋታውን ከቡሩንዲው ቡማሙሩ ክለብ ጋር ያደርጋል።

 

ዐፄዎቹ ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ መቀመጫውን ጨዋታውን በሚያከናውንበት ባህር ዳር ከተማ በማድረግ ሲዘጋጅ ቆይተዋል። ምንም እንኳን ጠንከር ያሉ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ባያደርጉም በዛሬው የመጨረሻ ልምምድ ወቅት ቡድኑ በጥሩ መነቃቃት ላይ እንደሚገኝ በስፍራው ተገኝተን ለመረዳት ችለናል።

በጉዳት ምክንያት ሀብታሙ ተከስተ ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ሲረጋገጥ አዲስ ፈራሚው ጋምቢያዊ አጥቂ ጋይራ ጁፍ የመኖርያ ፍቃድ ያላለቀለት በመሆኑ ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር ያልተረጋገጠ መሆኑ ተመላክቷል ፤ የቡድን መሪው ሀብታሙ ዘዋለም የተጫዋቹን የመኖርያ ፍቃድ ለማስጨረስ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ሰምተናል።

ከዚህ ውጭ አብዛኛው የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል። የኋላው ደጀን አስቻለው ታመነ ነገ አዲሱ የዐፄዎቹ አንበል በመሆን ቡድኑን እየመራ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል። አራቱም ዳኞች ከሱዳን መሆናቸው ሲታወቅ የጨዋታው ኮሚሽነር ከዩጋንዳ በመሆን ዛሬ ማለዳ ባህር ዳር መድረሳቸውን ተገንዝበናል። የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አብዮት እንዳደረሱን መረጃ ከሆነ ክቡር ትሪቩኑ ሙሉ ለሙሉ ለእንግዶች ብቻ የተፈቀደ ሲሆን በተቀረው የስታዲየም ክፍል የመግቢያ ዋጋ 100፣ 50 እና 30 ብር ነው።

ነገ ባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዘጠኝ ሰዓት ጨዋታው ሲካሄድ ዐፄዎቹ ይህንን የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚያልፍ ከሆነ በሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ከቱኒዚያው ሴፋክሲን (ቱኒዚያ) ጋር የሚፋለሙ ይሆናል።