ጎፈሬ ከፌዴሬሽኑ ጋር በሴካፋ ተሳታፊ ለሆነው ብሔራዊ ቡድን የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ፈፀመ

ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣርያ ውድድር ላይ ተሳታፊ ለሆነው ብሔራዊ ቡድን የሚሆን የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና በጎፈሬ የትጥቅ አምራች መካከል ተፈፅሟል፡፡

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከፊታችን መስከረም 22 ጀምሮ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣርያ ይደረጋል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ስምንት ሀገራት በሁለት ምድብ ተከፍለው የሚወዳደሩ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ላይ ትካፈላለች፡፡ በውድድሩ ላይ ተካፋይ ለሆነው ብሔራዊ ቡድናችን ቱታዎችን ፣ የልምምድ መለያዎች ፣ የመጫወቻ መለያዎችን ፣ ቲሸርቶች ፣ ካሶቶኒዎችን ለቡድኑ አሰልጣኞች ፣ ተጫዋቾች እና የቴክኒክ አካላት የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት የሚያደርገው ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ተቋም እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በፌድሬሽኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ በዛሬው ዕለት 9፡00 ላይ የስምምነት ውል መፈራረም እና ጋዜጣዊ መግለጫ የመስጠት ሁነት ተከናውኗል፡፡ ጎፈሬ በነፃ ያቀረበውን ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚገመት የትጥቅ አቅርቦት ስምምነትን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሀፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እና የጎፈሬ ትጥቅ አምራች ስራ አስኪያጅ እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን ፈፅመዋል፡፡ አስቀድሞ የፊርማ ስነ ስርአት የተከወነ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ሁለቱም አካላት ንግግር አድርገዋል፡፡

በቅድሚያ የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሀፊ አቶ ባህሩ “በጎፈሬ ትጥቅ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መካከል የተደረገው ይህ ስምምነት ከ17 ዓመት በታች ተሳታፊ ለሆነው ብሔራዊ ቡድናችን ሙሉ ትጥቅን ከጎፈሬ በነፃ የማቅረብ መብት እና ግዳጅንም የሚሰጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለይ የሀገር ውስጥ አምራች ተቋማት በዚህ ደረጃ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ማበረታታት ሌሎችም መሰል ድርጅቶች እንዲኖሩ ፣ እንዲበረክቱ ወይንም ደግሞ ለሌሎቹ ሞራል ይሰጣል እንደዚሁም ደግሞ ላለው ተቋም ደግሞ የበለጠ ከዚህም በላይ መስራት እንዲችል መንገዱን የሚከፍት ነውና ይሄ የውል ስምምነት ወይም ደግሞ በነፃ ሙሉ ትጥቁን የማቅረብ ስምምነቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስም ብቻም ሳይሆን በአጠቃላይ በተለያዩ ዲሲፒሊኖች ለሚደረጉ ስፖርቶችም ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥራል ማለት ነው እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ጎፈሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥራታቸውን የጠበቁ ትጥቆችን እያመረተ በፊት ከጀመረበት አሁን ላይ እየተሻሻለ እየተሻሻለ ብሎም ከሀገር ውስጥ ወደ ጎረቤት ሀገራትም ለምስራቅ አፍሪካ ለሚገኙ ክለቦችም ላይ እየተዘወተረ እየመጣ የሚገኝ ብራንድ ሆኗል ማለት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ መፈራረማችን ለእኛ በነፃ ትጥቆችን ማቅረብ ጥሩ ነገር ነው ከዛ ውጪ ደግሞ ለጎፈሬም ደግሞ ትልቅ የገበያ አቅምን ይፈጥርለታል ብለን ነው የምናስበው ይሄ ቶርናመንት በስምንት ሀገራት መካከል የሚደረግ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሁሉም ሀገራት ወይም ፌድሬሽኖች በዕድሜ ደረጃ ለሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖቻቸው ስፖንሰሮችን ማግኘት ብዙ ጊዜ እንደሚቸገሩ ይታወቃል በተለይም ደግሞ በዚህ ዞን የሚገኙ ወይንም ስፖንሰር ሺፕ ከዚህ ከትጥቅ አቅራቢዎች ጋር ሲደረግ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የሚደረገውን ነው ለዕድሜ ደረጃ ቡድኖች እየሆነም እየተሰጠም የሚገኘው እና በዚህ ደረጃ ለ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድናችን በሴካፋ ዞን ተሳታፊ ለሆነው ይሄንን ውል መፈራረማችን ሌሎችም በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲያስቡበት በይበልጥ ከዚህ ድርጅት ጋር መስራት የሚችሉበትን ዕድል ይመቻቻል እኛም ደግሞ የሀገር ውስጥ ተቋማትን ከማበረታታት አንፃር ይሄ ፈር ቀዳጅ ጅማሮአችን ነው ማለት ነው፡፡ በዕርግጥ ከጎፈሬ ጋር በተለያዩ መንገዶች አብረን እየሰራን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ አርባምንጭ ላይ ተካሂዶ በነበረው ጥቅላላ ጉባኤ ከስፖርት ኢቨንትም ጋር ተያይዞ የሚሰሩት ስራ ስላለ እዛ ላይ ከእኛ ጋር ስራ መስራታቸው ይታወቃል የልምምድ ትጥቆችን እያቀረቡልን እንደሆነም ይታወቃል፡፡ እኛ ስምምነታችን በተለይ ከዋና ብሔራዊ ቡድናችን ጋር ተያይዞ ከአምብሮ መሆኑ ይታወቃል እጥረቶች በገጠሙን ወቅት ግን ተመሳሳይ ዓይነት ዲዛይኖችን ሰርተው እያቀረቡልን ነው የሚገኘው ይሄም ትልቅ ተግባራቸው እንደሆነ መግለፅ እንወዳለን፡፡ በብዙ ሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር ስራን ነው እየሰሩልን የሚገኘው እና በዚህ አጋጣሚ ጎፈሬንም ልናመሰግን እንወዳለን እኛም ተጠቃሚ ሆነን እነርሱም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መድረክ ነው የተመቻቸው ማለት ይቻላል።”

በማስከተል የጎፈሬ ትጥቅ አምራች ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል መኮንን “ዛሬ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና በጎፈሬ መካከል የተደረገው የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ከዚህ በፊት እንደተለመደው ከተለያዩ ክለቦች ጋር የምናደርገው ስምምነት አይነት ሆኖ ይሄ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ስምምነት ነው፡፡ በአጠቃላይ ይሄ ከብሔራዊ ቡድን ጋር የምንሰራዉን የመጀመሪያ በር ይከፍታል ብለን ነው የምናስበው። በእኛ በኩል በአጠቃላይ ደግሞ ጎፈሬም እንደ ሀገረ በቀል ድርጅትነቱ ካሉት አንዳንድ ግዴታዎች አንዱን ግዴታ እየተወጣን ነው ብለን የምናስበው በጥራት ፣ በደረጃው በምስራቅ አፍሪካ መወዳደር እየቻለ ነው። ፌዴሬሽኑ ባሉት ስምምነቶች ምክንያት ከፌዴሬሽን ጋር ልንሰራ ከምንችልበት አንዱ በር ስለተከፈተ በዚህም ፌዴሬሽኑን ማመስገን እንፈልጋለን። እኛም የራሳችንን ምርት ለዓለምም ፣ ለአፍሪካም የምናስተዋውቅበት መድረክ ነው የሚሆነው። በጥራቱም በዓይነቱም ለየት ብለናል። ይሄ ሲደረግ ደግሞ ጥራቱ ታይቶ የእኛ ጥራት ከተለያዩ ብራንዶች ጋር መወዳደር ስለቻለ በዚህ መልኩ ፍቃዱን ማግኘት ችለናል ማለት ነው፡፡ ስፖንሰር ሺፕ ብቻ ስለሆነ ከፌዴሬሽኑ ጋር መስማማት ችለን ብቻ ስለሆነ አይደለም በጥራት በብዙ መመዘኛዎች ተመዝኖ ማሟላት ስለቻልን የእኛ ምርት በብሔራዊ ቡድን ከ17 ዓመት በታች ላይ መለበስ ይችላል ማለት ነው። ስለዚህ አንዱ ግዴታችን ነው ብለን የምናስበው እንደ ስራ ደግሞ ከፈጠርነው ተፅእኖ አንፃር እንደ ዕቅድ ከምንይዘው አንዱ ብሔራዊ ቡድን ላይ መታየት ነው። አፍሪካ ላይ ያሉ የተወሰኑ ብሔራዊ ቡድኖችን እያናገርን ነው ያለነው። ከምስራቅ አፍሪካ ካሉ ሀገሮች ጋር የመስራቱን በር ይከፍትልናል ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ ይሄ በሁለቱም በኩል ተጠቃሚነትን የሚፈጥር ስምምነት ነው፡፡ ስምምነቱ የሚቆይበት ጊዜ ለዚህ ውድድር ነው የሚሆነው። ቶርናመንቱ እስከሚያልቅ ጊዜ ከ17 ዓመት ቡድኑ ጋር የሚቆይ ነው፡፡ ግዴታ እና መብት አለን። በአጠቃላይ ከትንሹ ምርት ጀምሮ እስከ ትልቁ ምርት በፊት ውድድር ላይ የጎፈሬን ምርት እናያለን ማለት ነው፡፡ ከዚህ በፊት አቅርበናቸው የማናውቃቸውን እንደ አዲስ ያመረትናቸው ምርቶች ምርቶች ማሳያ ይሆናል እና ለእኛ ትልቅ በር ነው የሚሆነው ማለት ነው፡፡

ከሁለቱ ንግግር በመቀጠል ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች ተነስተው መልስ ተሰጥቷል፡፡

የዋናው ብሔራዊ ቡድን ትጥቅ አቅራቢ ኡምብሮ እያለ እነ አዲዳስ እና ጎፈሬ በ23 ዓመት እና ከ17 ዓመት በታች ላይ ስለመታየታቸው

አቶ ባህሩ “ከኡምብሮ ጋር ግዳጃችን ከዋናው ብሔራዊ ጋር ነው። ነገር ግን የትኛውም ትጥቅ አቅራቢ ብዙ ጊዜ የዕድሜ ደረጃ ቡድኖችን ትኩረት አድርጎ ለእነዚህም ስፖንሰር አደርጋለሁ የሚል የለም። ስለዚህ ኡምብሮን ነው የምንጠቀመው በዕድሜ ደረጃ የምንገደደው ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ነው፡፡ ስለዚህ በዕድሜ ደረጃ ያሉ ቡድኖቻችን ትጥቅ አቅራቢዎች ስለሌሉን ብቻ ነው ኡምብሮን እያለበስን እየተጠቀምን የዕድሜ ደረጃ ቡድኖቻችን የዋናውን ቡድን ፍጆታ እየወሰዱ ነው የሚገኙት እና በዚህ በኩል ችግር የለም። ከአዳዲስ ጋር ተያይዞ ይታወቃል ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድናችን እየተካፈለበት ያለው ማጣሪያ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድንን ወክሎ በፓሪሱ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ነው። ስለዚህ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ስፖንሰር ደግሞ አዲዳስ ነው፡፡ በዛ ምክንያት ነው አዲዳስን እየለበሰ ያለው። ባለፈውም ለብሰውት የነበረውን ያቀረበልን የኦሎምፒክ ኮሚቴ ነው ማለት ነው። ከዚህ ቀደምም ማሊ ላይ በደርሶ መልስ በተሸነፍንበት ጊዜ የለበሱት አዲዳስ ነው። በወቅቱም ኡምብሮ ነበር ስፖንሰራቸን፡፡ ጎፈሬ እንግዲህ አዲስ ስምምነት ነው እየያደረግን ያለነው።ነገ ጎፈሬ አድጎ ለዋናውስ ብሔራዊ ቡድን መሆን አይችልም ወይ? በሀገር ምርት መኩራት መጀመር አለብን። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ አይነት ስምምነቶች የሉም። አንድ ሁለት እየሆኑ እየተፈጠሩ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ ስፖርት አቅራቢ ነበር ኳሶች የተለያየ መለያዎችን በእግር ኳሱ ለኮካ ኮላ ውድድር ያቀርብ የነበረው። አሁን ላይ ድርጅቶች እየሰፉ ሲመጡ በዚህ ደረጃ ደግሞ ጎፈሬ በየጊዜው ጥራቱን እየጠበቀ ዘመኑ የሚልገውን ነገር እያደረጉ ባለፈው ዓመት ካየኸው እየተሻሻለ እየተሻሻለ ከአሁኑ ደግሞ በቀጣይ የመሻሻል ዕድሉ ይኖራል። እኛ እንኳን ስናውቃቸው ከመለያ ጥራት ጋር ተያይዞ ዕድገት ይታያል፡፡ የተለያዩ ውድድሮች ላይ ስንመለከት ማልያ የጎፈሬ ይኖር ና ካሶተኒው ላይ ናይክ ወይም አዲዳስ ይኖር ነበር። አሁን ካሶተኒውን ማምረት ጀምረዋል፤ በደንብ እያደገ ያለ ተቋም ነው። ወደፊት ቀጣይ ስራዎችን በጋራ የምንሰራ ይሆናል፡፡”

አቶ ሳሙኤል በተለይ ከማርኬቲንግ ዕቅዳቸው ጋር በተገናኘ ለተነሳ ጥያቄ “የእኛ ማርኬት ምስራቅ አፍሪካ ነው። አሁን እዚህ መጥተው የሚወዳደሩ ብሔራዊ ቡድኖች አብዛኛዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ናቸው፡፡ መቶ ፐርሰንት ታሬጌታችን የሚመታበት ሂደት ነው። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ የመጀመሪያ ምርታችን ነው የሚሆነው። ምናልባት አንድ ጊዜ የፓን አፍሪካኒዝም የትምህርት ቤት የተማሪዎች ውድድር ላይ አቅርበናል። ግን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የመጀመሪያችን ነው የሚሆነው። አሁን እንደ ጎፈሬ ስፖሰር ሺፕ የሚለው ስምምነት ስፖንሰር ሺፕ ሲባል ድርጅቱ ሙሉ ለሙሉ የሚሰጥ ነው የሚመስላቸው። አብዛኛዎቹ ክለቦቻችን ግንዛቤ አልነበራቸውም ከዶክመንቶት ጀምሮ ስፖንሰር ሺፕ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ነው ጎፈሬ ሲሰራ የነበረው፡፡ ይሄን ግንዛቤ ፈጥረን ዶክመንት አዘጋጅተን አንድ ክለብ ካለው አቋም አንፃር ተነስቶ የቡድኑን ኤክፔንስ ትጥቅ አቅራቢ የሚያቀርብ ከሆነ የደጋፊዎችን መለያ በመሸጥ ደግሞ ጎፈሬ ይጠቀማል ማለት ነው። ይሄን አይነት አሰራር ጎፈሬ ነው የጀመረው፡፡ ክለቦቻችን አሁን ይሄንን ተቀብለው ተገንዝበው አሁን የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ሲባል ደግሞ መስጠት መቀበል ነው። መስጠት ብቻ አይደለም። አሁን እኛ አሁን ስፖንሰር ሲባል በነፃ የሚለው አይገልጸውም፤ ስፖንሰር ሺፕ ነው፡፡ ስፖንሰር ስናደርግ እኛ የምናገኘው ብዙ ግብዐት አለ፤ ምርታችን ይተዋወቃል ፣ ከብሔራዊ ቡድን ጋር አብረን እየሰራን ነው ያለነው። ስለዚህ ሌሎች ብሔራዊ ቡድኖችን የመስራት አሁን በንግግር ደረጃ ያለ አራት ብሔራዊ ቡድኖች አሉ እነርሱም እዚህ ይመጣሉ ምርታችንን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አድርጎት ሲገኝ የማሳመን መንገዱ ሰፊ ነው የሚሆነው። ጎፈሬ ከትጥቅ በላይ መሸጥ ነው የምንልበት ዋናው ነገር ደግሞ ግንዛቤዎች መፍጠር ነው፡፡ ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ደረጃ ማነቃቃት ችለናል አሁን አሁን ክለቦቻችን ያሉበት አቋም አለ ከትጥቅ ጋር ያለው ግንዛቤ በትጥቅ መምጣት እንደምንችል መለያ ላይ ስፖንሰር ተደርጎ መምጣት እንደምንችል ቴክኒካሊ ይሄን መፍጠር ችለናል፡፡ በዚህምየተነሳ የጎፈሬ ስፖርት ኢቨንት የተፈጠረበት ዋናው ጉዳይ ይሄ ነው የኛን ምርት ማስተዋወቅ እና ኢንዱስትሪው አማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ላይ የነበረው የመዝጊያ ፕሮግራም አይታችሁታል፡፡ ኢቨንቶች እንዴት መዘጋት እንዳለባቸው ስፖንሰር የሚያደርጉ ድርጅቶች በምን ዓይነት መልኩ ምርታቸው መተዋወቅ እንዳለበት የሚያሳይ ነገር ነው ስለዚህ ጎፈሬ አሁን ከምናቀርበው ምርት በላይ ነው ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖር የስፖርት እንቅስቃሴ ዕድገት ላይ ባለድርሻዎች ነን ብለን የምናስበውከግንዛቤ መፍጠር አንስቶ ይሄንን የምንሰራበት ምክንያት ዋናው ይሄ ነው የሚሆነው እና ትልቅ ገበያ ነው ለእኛ፡፡ በክለብ ደረጃ ዩጋንዳ ውስጥ ከስድስት ሰባት ክለብ የኛን ምርት ይጠቀማሉ ደቡብ ሱዳን ፣ ዛምቢያ ታችኛው ሊግ ሳይቀር አካዳሚዎች ሳይቀሩ የኛን ምርት ይጠቀማሉ፡፡ ይፋዊ የሆኑት ትልልቅ ስምምነቶችን ይፋ እናደርጋለን በውስጥ ደረጃ ግን የውጪ ምንዛሬ አስቀርተናል ሀገሪቷ ላይ ምንዛሬም እያመጣን ነው ይሄ ትልቅ እምርታ ነው። ለፌዴሬሽኑም እዚህ ላለነው ለሁሉም ሰው ትልቅ ኩራት ነው።”