ጎፈሬ ከዩጋንዳ ክለብ ጋር የትጥቅ ስምምነት ፈፅሟል

ሀገር በቀሉ ትጥቅ አምራች ኩባንያ ጎፈሬ ከኢትዮጵያ አልፎ ምርቱን ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማቅረብ ከጀመረ ሰንበትነት ያለ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ከዪጋንዳ ክለብ ጋር ስምምነት ፈፅሟል።

ከጎፈሬ ጋር ውል ያሰሩት በቅፅል ስማቸው አናብስት ተብለው የሚጠሩት ዩፒዲኤፍ በአሁኑ ወቅት በዩጋንዳ የመጀመሪያ እርከን እየተጫወቱ ሲገኝ በ3 ጨዋታዎች 4 ነጥቦችን በመሰብሰብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በፊርማ ሥነስርዓቱ ወቅት የጎፈሬ መስራች ሀሰን መሐመድ ሀሰን በሰጡት መግለጫ ስምምነቱ ጎፈሬ የምስራቅ አፍሪካ ጉዞውን ያጠናከረበት እና ለ6ኛ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ ጥራቱ ተወዶ እየሰራ ያለበት ሁኔታ እንዳለ ገልፀዋል። ” እስካሁን በሰራነው ስራ ብዙ ነገሮችን አሳክተናል። ሆኖም ግን ገና ህልማችን ላይ አልደረስንም። ይህ ጥሩ ጅማሮ ነው። ደስ የሚል እና ታሪካዊ ቀን ነው” በማለት ሀሳባቸውን አክለዋል።

ዩፒዲኤፍን ወክለው የተገኙት የክለቡ አሰልጣኝ ብራየን ሴንዮንዶ በበኩላቸው ” ከጎፈሬ ጋር እዚህ ስምምነት ላይ በመድረሳችን ደስተኛ ነን። ከተለመደው ነገር ወጣ ብሎ አዲስ ነገሮችን መሞከር ጥሩ ነው። ይሄ ስምምነት ደግሞ ፓንአፍሪካኒዝም እንድናሳይ ይጠቅመናል” ብለዋል። አክለውም ስምምቱ ከትጥቅ አቅራቢነት በዘለለ ጎፈሬን በዩጋንዳ ብሎም በመላው ምስራቅ አፍሪካ ለማስተዋወቅ ክለቡ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ጎፈሬ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ቁጥር አንድ ትጥቅ አምራች ለመሆን ያለውን ዕቅድ ከዳር ለማድርስ እየስራ ሲገኝ ነገሮች ከታሰበላቸው ጊዜ ይልቅ በፍጥነት እየሄዱ መሆኑን አቶ ሀሰን አስረድተዋል።

ዩፒዲኤፍ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ላይኛው እርከን ያደገ ሲሆን በመጀመሪያው ዓመት ከ16 ክለቦች 10ኛ በመሆን አጠናቋል። በብሔራዊ መከላከያ ኃይል ስር የሚገኘው እና ስያሜውንም ከዛ የወሰደው ክለብ ዋና መለያው አረንጓዴ ሲሆን ተቀያሪው ደግሞ ነጭ እና ጥቁር ቀለማትን የያዘ ነው። ጎፈሬ ለክለቡ ከሚያቀርበው ትጥቅ በተጨማሪ 5000 የደጋፊ ማልያዎችን እንደሚያዘጋጅ ተገልጿል። ስምምነቱ ከማልያ በተጨማሪ ቱታዎችን እና የልምምድ መለያዎችን ያካተተ ነው። ጎፈሬ በቀጣይም የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖችን ስፖንሰር ማድረግን ያስባል።