ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ3ኛ ሳምንት ምርጥ 11

ሰባት ጨዋታዎችን ካስተናገደው 3ኛው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጨዋታ ሳምንት ምርጥ 11 እና አሰልጣኝ መርጠናል።

አሰላለፍ – 4-3-3

ግብ ጠባቂ

በረከት አማረ – ኢትዮጵያ ቡና

የቡናው ግብ ጠባቂ የተረጋጋ 90 ደቂቃን ማሳለፍ ችሏል። በሳምንቱ ግብ ካላስተናገዱ ሁለት ግብ ጠባቂዎች መካከል አንዱ የነበረው በረከት በተለይም በመጨረሻ ደቂቃ ያመከነው ያለቀለት የግብ አጋጣሚ ቡና ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት ሊገደድ የደረሰበት በመሆኑ ቡድኑ ባሳካው ሦስት ነጥብ ላይ ቀጥተኛ አስተዋፅዖ ነበረው።

ተከላካዮች

ጀሚል ያዕቆብ – አዳማ ከተማ

ታታሪው የመስመር ተከላካይ ቡድኑ ሀዋሳ ከተማ ላይ ወሳኙን ድል ሲያስመዘግብ የዳዋ ሆቴሳ ጎል እንዲገኝ የመጨረሻ ኳስ አመቻችቶ ከማቀበሉ በተጨማሪ በዋና የመከላከል ኃላፊነቱ ለወትሮ የተጋጣሚ ቡድን ጠንካራ ጎን የነበረውን የመስመር አጨዋወት ለማምከን ሲጥር ተስተውሏል።

ሚሊዮን ሰለሞን – አዳማ ከተማ

ከጨዋታ ጨዋታ እየበሰለ የመጣው ሚሊዮን ባሳለፍነውም ሳምንት የቡድኑ ወሳኝ የኋላ ደጀን መሆኑን ያስመሰከረበትን የጨዋታ ቀን አሳልፏል። ፈጣን እና ቀልጣፋ የሆነው ተከላካዩ ቡድኑ በተከታታይ ጨዋታ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ እና ግብ ሳይቆጠርበት እንዲወጣ የበኩሉን ተወጥቷል።

ግርማ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ሀዲያ ሆሳዕና ድሬዳዋን 3-1 በረታበት ጨዋታ ቡድኑን ዳግም መሪ ያደረገች ወሳኝ ግብ ያስቆጠረው ግርማ የመሀል ተከላካይ ቦታ ላይም መጫወት በመቻሉ ወደ ኋላ ስበን ተጠቅመነዋል። በጨዋታው በተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ የተሰለፈው ግርማ የድሬዳዋ አማካዮችን እንቅስቃሴ በማቋረጡ ረገድ የተሳካ የጨዋታ ዕለት አሳልፏል።

ሳሙኤል ዮሐንስ – ኢትዮጵያ መድን

በአዲሱ ክለቡ መድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ሁለገቡ ተጫዋች ሳሙኤል በግራ መስመር ጥሩ ሲንቀሳቀስ ተመልክተናል። ምንም እንኳን ተጫዋቹ በዕለቱ ተቀይሮ ቢወጣም በዋናነት በማጥቃት እንቅስቃሴ የቡድኑ የግብ ምንጭ ለመሆን አማራጭ ሲፈጥር ነበር።

አማካዮች

ናትናኤል ዘለቀ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከቆይታ በኋላ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ የተመለሰው ባለልምዱ ናትናኤል ጥሩ ግልጋሎት ሰጥቷል። መሀል ላይ ከበረከት ወልዴ ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር የሲዳማን አማካይ ክፍል ከመቆጣጠር ባለፈ በመካከለኛ እና ረዥም ኳሶች እንዲሁም ለሳጥኑ ቀርቦ በመንቀሳቀስ የቡድኑን ማጥቃት አግዟል።

ባሲሩ ዑመር – ኢትዮጵያ መድን

እንደ ሳሙኤል በመድን መለያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ጋናዊው አማካይም ኳሶችን በማጨናገፍ እና በማደራጀት እንዲሁም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተደጋጋሚ ሩጫዎችን በማድረግ የተሳካ ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን በሊጉ የመጀመሪያ ጎሉንም በ23ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል።

ቡጣቃ ሸመና – አርባምንጭ ከተማ

ወጣቱ የአዞዎቹ አማካይ እጅግ ውጤታማ የሆነ የጨዋታ ቀንን አሳልፏል። የቡድኑ ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ ሆኖ በታየበት ጨዋታ ያገኛቸውን ኳሶች በቶሎ ወደ ማጥቃት ወረዳ ያደርስ የነበረ ሲሆን በዚህም ተሳክቶሎት የእይታውን ጥራት የሚያሳዩ እና የቡድኑ ሁለት ጎሎች ሆነው የተመዘገቡ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።

አጥቂዎች

ቸርነት ጉግሳ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቸርነት ገና በሦስተኛ የጨዋታ ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ በምርጥ ቡድናችን እንድናካትተው ያደረገ ብቃት ባሳየበት የሲዳማው ጨዋታ ለተከላካዮች ከባድ ፈተናን ሲሰጥ ነበር። በተለይ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች አደገኛው ተጫዋች በጨዋታው ከእስማኤል ኦሮ-አጎሮ በመቀጠል በክለቡ ብዙ ግቦች ላይ ተሳትፎ ያደረገበትን ቁጥር አስመዝግቦ ወጥቷል።

ዳዋ ሆቴሳ – አዳማ ከተማ

አዳማ ከተማ በከባዱ የሀዋሳ ጨዋታ ወሳኙዋን ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ እርሱ ያስቆጠራት ጎል ያስፈልገው ነበር። ወደ መስመር ወጥቶ እንዲጫወት በአሠልጣኙ ኃላፊነት የተሰጠው ተጫዋቹ በእንቅስቃሴዎች እየተሳተፈ ቡድኑን ከግብ ማስቆጠር በዘለለ ሲጠቅም ታይቷል።

ኢስማኤል አሮ አጎሮ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቶጓዊው አጥቂ ከመጀመሪያው ሳምንት በኋላ በድጋሚ ወደ ምርጥ 11 ስብስባችን ተመልሷል። የተጋጣሚን ተከላካዮች እንቅስቃሴ በመረበሽ የቡድኑን ጥቃት አስፈሪነት ያላበሰው አጎሮ ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶችን በአግባቡ በመጠቀም እና በጨዋታ አንድ በማከል ሐት-ትሪክ ሰርቶ የከፍተኛ ግብ አግቢ ፉክክሩን መምራቱን ቀጥሏል።

አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ሀዲያ ሆሳዕና

የነብሮቹ አሰልጣኝ ወደ ዋና ኃላፊነት በመጡበት አዲሱ የውድድር ዓመት ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን ባሳኩበት ሳምንት ምርጡ አሰልጣኝ አድርገን መርጠናቸዋል። በድሬዳዋው ጨዋታ የተጫዋች ለውጦችን ቢያደርጉም ድላቸውን ለማስቀጠል በመረጡት መንገድ የተጋጣሚያቸውን የመስመር ጥቃቶች በመቋቋም ቀጥተኝነትን የቀላቀለ ጥቃት ላይ ተመስርተው በሁለት ጎሎች ልዩነት ቡድናቸው አሁንም ጠንካራ ጎኖቹን ይዞ መቀጠል እንደሚችል በሚያሳይ አኳኋን ማሸነፍ ችለዋል።

ተጠባባቂዎች

ኩዋሜ ባህ – አዳማ ከተማ
ኃይለሚካኤል አደፍርስ- ኢትዮጵያ ቡና
ኩዋኩ ዱሀ – ኢትዮጵያ ቡና
አቤል አሰበ – ድሬዳዋ ከተማ
ባዬ ገዛኸኝ – ሀዲያ ሆሳዕና
ኪቲካ ጅማ – ኢትዮጵያ መድን
መስፍን ታፈሰ – ኢትዮጵያ ቡና