ከፍተኛ ሊግ | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ዝውውር ገብቷል

ሁለተኛውን የውድድር ዓመት በከፍተኛ ሊጉ የሚያሳልፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር አገባዷል፡፡

ከፈረሰበት በድጋሚ ከተመሠረተ በኋላ ባሳለፍነው ዓመት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ስር በመደለል ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ከምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የፈፀመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀናት በፊት አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድን በመንበሩ ከሾመ በኋላ ተጫዋቾችን ማስፈረም ጀምሯል፡፡

የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከጀመረ ሰንበትበት ያለው ክለቡ የሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር የፈፀመ ሲሆን በቀጣዩ ቀናትም ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

ክለቡን ከተቀላቀሉ ሰባት ተጫዋቾች መካከል ፍቃዱ ደነቀ አንደኛው ነው፡፡ የቀድሞው የድሬዳዋ ከተማ ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የመሀል ተከላካይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር በከፍተኛ ሊጉ ቆይታን አድርጎ ቀጣዩ መዳረሻው ንግድ ባንክ ሆኗል፡፡ አማካዩ ልዑልሰገድ አስፋው ሁለተኛው ፈራሚ ነው፡፡ በደሴ ከተማ እና ባለፈው ዓመት ደግሞ በሀምበሪቾ ቆይታ ነበረው፡፡

የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ ፣ ስልጤ ወራቤ እና ነቀምት ከተማ ተከላካይ ጌቱ ባፋን ጨምሮ ፣ አላዛር አድማሱ አማካይ ከሀምበሪቾ ፣ ሳምሶን ደጀኔ አማካይ ከኢትዮጵያ መድን ፣ ፕላንክ ቾል ግብ ጠባቂ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ እና አላዛር የግራ መስመር ተከላካይ ከሶዶ የክለቡ አዳዲስ ፈራሚዎች ናቸው፡፡