‘ከጨለማ በኋላ ብርሃን’ – ኢትዮጵያ መድን

በመጀመሪያው ሳምንት በክለቡ ታሪክ እጅግ አስከፊ ከሆኑ ውጤቶች አንዱን በማስመዝገብ የጀመሩት ኢትዮጵያ መድኖች በመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ግን ከአስከፊው ሽንፈት ቀና ያሉባቸውን ተከታታይ ድሎች አሳክተዋል። ገና ብዙ መንገድ ቢቀርም ብዙዎች የሰጉለት ቡድን ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ፤ እኛም ስለቡድኑ የአራት ጨዋታ ጉዞ ተከታዩን አሰናድተናል።

ከስምንት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሱት ኢትዮጵያ መድኖች ሊጉን የከፈቱበት መንገድ እጅግ አስደንጋጭ የሚባል ነበር። የአምናውን የሊጉን አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመግጠም የጀመሩት መድኖች ፍፁም ደካማ በነበሩበት ጨዋታ አሰቃቂ የሚባል የ7-1 ሽንፈት ማስተናገዳቸው አይዘነጋም።

ምናልባት ከግቦቹ መብዛት ባለፈ በጨዋታ ዕለቱ ኢትዮጵያ መድኖች በአጠቃላይ የጨዋታ ሂደት ፍፁም ደካማ የነበሩ ሲሆን በተለይ ደግሞ ቡድኑ ከኳስ ውጪ ያሳያው ፍፁም ደካማ የነበረ አደረጃጀት በትልቁ የሊግ እርከን ከሚጫወት ቡድን የማይጠበቅ አስደንጋጭ መከላከል ነበር። ተደራጅተው በተጠና የቦታ አያያዝ መከላከል የተሳናቸው መድኖች በመከላከል ቀጠናው በዝቶ ከመገኘት ባለፈ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለማቆም የሚያስችል ቁመና ላይ እንዳልነበሩ አስተውለናል። ከዚህ ባለፈም ኳስ በሚይዙባቸው ቅፅበቶችም የተሳኩ ጥቂት የኳስ የቅብብል ሂደቶች (Sequence of Pass) ለማድረግ ይቅርና በአብዛኞቹ የማቀበል ሂደቶች የቡድን አጋራቸውን እንኳን ፈልገው ለማግኘት ሲቸገሩ እና ይበልጥ ራሳቸውን ለተጨማሪ ጥቃት የማጋለጣቸው ነገር የጨዋታው መነጋገርያ ነጥቦች ነበሩ።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ብዙዎች ሜዳ ላይ ባዩት ነገር ‘ኢትዮጵያ መድን እና አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ የውድድር ዘመኑን እንዴት ይገፉት ይሆን ?’ የሚሉ የስጋት ድምፆች ሲስተጋቡ እንዲሁም ቡድኑ በክረምቱ ካደረገው የአሰልጣኝ ሹም ሽር ጋር በማያያዝ በርካቶች የክለቡን አመራሮችን ሲያብጠለጥሉ ተመልክተናል።

ከአሰቃቂው ሽንፈት በኋላ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ከሱፐር ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ “በአጠቃላይ ሲታይ ሰፊ ውጤት ነው። ነገር ግን ከነበረብን ችግር አንፃር መሻሻል የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ስላሉ ያን ያህል ሞራል የሚነካ አይደለም።” በሚል የሰጡት ሀሳብ ለብዙዎች በወቅቱ ትርጉም የሰጠ አልነበረም። ታድያ ቡድኑ ከአሰቃቂው ሽንፈት ማግስት በሰንጠረዡ በምንም ነጥብ እና በስድስት የግብ ዕዳ ቢቀመጥም በቀጣይ ባደረጋቸው ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ሦስቱንም በማሸነፍ በአሁኑ ወቅት በዘጠኝ ነጥቦች እና በአንድ የግብ እዳ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሦስት ነጥቦች አንሰው በሁለተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ በቅተዋል። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለው ነገር ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል።

አዕምሯዊ ጉዳዮችን በቁጥሮች መለካት እና መመዘን ባይቻልም ሰባት የተቆጠረበትን ቡድን ከሚፈጠርበት የሞራል ዝቅታ በፍጥነት ወጥቶ በቀጣይ ጨዋታዎች በዚህ ረገድ የተሻሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ከውጤት ጋር አጅቦ እንዲጓዝ በማስቻል ረገድ ተጫዋቾች አዕምሮ ላይ በሰሩት ሥራ የቡድኑ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የሰሩት ስራ ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረው ነው። የተጫዋቾች ጉዳት አሁን ድረስ ከመድን ጋር የቀጠለ አሉታዊ ጉዳይ ቢሆንም የቡድኑ አባላት እና አመራሮች ዳግም ወደ ራሳቸው በመመልከት ይህን አስከፊ ሽንፈት እንደ መነሳሻ በመጠቀም የተሻለ ነገር ሜዳ ላይ ማሳየት ጀምረዋል።

ገና ከውድድሩ ጅማሮ አስቀድሞ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በዝግጅታቸው ዙርያ ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ቡድኑ በተከላካይ መስመር ስላጋጠመው ተደጋጋሚ ጉዳት ስጋታቸውን አጋርተውን ነበር። በቅድመ ውድድር ዝግጅታቸው ወቅት ከወጣቱ ተከላካይ ተመስገን ተስፋዬ በስተቀር በተለይ በመሀል ተከላካይ እንዲሁም በመስመር ተከላካይ ስፍራ የሚጫወቱ ተጫዋቾቹን በተደጋጋሚ በተከሰቱ ጉዳቶች አጥቶ የነበረው መድን በዚህም መነሻነት በፈለጉት ልክ የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረጋቸውን እንዲሁ አሰልጣኙ በወቅቱ ገልፀው እንደነበር አይዘነጋም።

ያለ በቂ የወዳጅነት ጨዋታ ወደ ሊጉ የገባው ቡድኑ ከውድድሩ አስቀድሞ በነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከመጀመሪያ ተሰላፊዎቻቸው ይልቅ በርከት ያሉ ወጣት ተጫዋቾችን ለመሞከር የተጠቀሙበት እንደመሆኑ በመጀመሪያው ጨዋታ ወጣቶችን ከባለልምድ በማጣመር የተሰራው የመጀመሪያ አስራ አንድ ምርጫ በወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ የተሞከረ አለመሆኑ ቡድኑን ዋጋ እንዳስከፈለው ተመልክተናል።

በቅዱስ ጊዮርጊሱ የመጀመሪያ ጨዋታቸው በኢትዮጵያ መድኖች በኩል ጨዋታውን ለመጀመር በብቸኝነት ብቁ የነበረውን የመሀል ተከላካይ ተመስገን ተስፋዬ እና አማካዩን አስጨናቂ ፀጋዬን በመሀል ተከላካይነት በማጣመር የጀመሩ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ደግሞ ሙሉ ጤንነት ላይ ያልነበረውን ፀጋሰው ድማሞን በማስገባት ከተመስገን ጋር ለማጣመር ቢሞክሩም እንደ ቡድን የነበራቸውም ሆነ የመሀል ተከላካይ ጥምረቱ ፍፁም ያልተረጋጋ እንደነበር አስተውለናል። ከሁለተኛው ጨዋታ አንስቶ ግን በተለይ የሁለገቡ ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ ከጉዳት አገግሞ መመለስ በቡድኑ የመከላከል መስመር ላይ የፈጠረው አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዳለ እየተመለከትን እንገኛለን። በመጨረሻዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ቴዎድሮስ በቀለ በሁለት አጋጣሚዎች ከአማካዩ አስጨናቂ ፀጋዬ እና በአንዱ ጨዋታ ደግሞ ከተመስገን ተስፋዬ ጋር የፈጠራቸው ጥምረቶች ቡድኑን በመከላከሉ በሚገባ አሻሽለዋል።

ከመጀመሪያው ጨዋታ አንፃር ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድኖች በመከላከሉ ረገድ ቡድኑ የተረጋጋ (Stable) ወደ መሆን እየመጡ ያለ ይመስላል። በሦስቱ ጨዋታዎች በድምሩ አራት ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ በሂደት የሚያስተናግደው የግብ መጠን እየቀነሰ ይገኛል በዚህም በአርባምንጩ ጨዋታ 3 ፣ በለገጣፎው 1 እንዲሁም በመጨረሻው የወላይታ ድቻ ጨዋታ ደግሞ ግብ ሳያስተናግዱ መውጣት ችለዋል። በተጨማሪነትም ከሚያስተናግዱት ግቦች መቀነስ ባለፈ ከመጀመሪያው ጨዋታ አንፃር ቡድኑ ተጋጣሚዎች የሚሰነዝሩበት የግብ ሙከራ በመጠንም ሆነ በጥራት እየቀነሰ ይገኛል። በጊዮርጊሱ ጨዋታ በአጠቃላይ 9 ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን አስተናግዶ የነበረው መድን በቀጣይ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ይህ አሃዝ 8 ፣ 6 በመጨረሻው ደግሞ 4 መሆኑ የቡድኑ መከላከል በመሻሻል ላይ ስለመገኘቱ ይናገራል።

እንደ ቡድን በመንቀሳቀስ በሊጉ የመቆየትን ዓላማ ሰንቀው ወደ ውድድር ለገቡት መድኖች ከምንም በላይ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት መገንባት መሰረታዊው ግብዓት እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም ቡድናቸው እንደ ቡድን በመከላከል ሆነ በተከላካይ ስፍራ አሁን ጉዳት በመጀመሪያ አስራ አንድ ተመራጮቻቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳረፈ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ቡድናቸው በመከላከሉ ረገድ እያሳየ የሚገኘው እምርታ ትልቅ ዕረፍት የሚሰጣቸው ይሆናል።

ከመከላከሉ እምርታ ባለፈ ቡድኑ በማጥቃቱ ረገድም ቀስ በቀስ የመሻሻል ምልክቶችን እየሰጠ ይገኛል። በመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች በኳስ ቁጥጥር ረገድ ተጋጣሚዎቹ ላይ መጠነኛ የሆነ የበላይነትን መውሰድ የጀመረ ሲሆን ወደ ተጋጣሚ ግብ የሚያደርጋቸው የሙከራዎች መጠንም እንደ መከላከሉ አስገራሚ ባይሆንም መሻሻሎች እንዳሉ እያስተዋልን እንገኛለን። በአጠቃላይ በአራት ጨዋታዎች 10 ግቦችን ያስቆጠረው መድን ከፈረሰኞቹ ቀጥሎ በሊጉ በርከት ያሉ ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ቡድን ያደርገዋል።

በተለይ ደግሞ ከማጥቃት ጨዋታ ዕድገቱ በስተጀርባ ከመድኖች ጋር ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገው ወጣቱ ኪቲካ ጅማ ትልቅ ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። ለሊጉ ተመልካቾች በሚገባ ራሱን እያስዋወቀ የሚገኘው ተጫዋቹ እስከ አሁን በሜዳ በቆየባቸው 295 ደቂቃዎች በየ59 ደቂቃዎች በግቦች ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል። እስካሁን በአምስት ግቦች ላይ ተሳትፎ ያለው ይህ የመስመር አጥቂ አራት ለግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል በሊጉ ቀዳሚው ተጫዋቾች ሲሆን በስሙም አንድ ግብ ማስመዝገብ ችሏል።

ከዚህ ባለፈ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በጊዜ ባለመጠናቀቃቸው በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ቡድናቸውን ማገልገል ሳይችሉ ቀርተው ከጨዋታ ሳምንት ሦስት አንስቶ ወደ ጨዋታ ዕለት ስብስብ መግባት የጀመሩት የቡድኑ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ተፅዕኗቸው በፍጥነት መሰማት ጀምሯል። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ጋናዊው አማካይ ዑማር ባሺሩ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ለቡድኑ አንድ ግብ እና ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ተቀይሮ በመግባት የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ሳይመን ፒተርም እንዲሁ ብቸኛ የማሸነፍያ ግብ ማስቆጠር ሲችል ኳሷን ያመቻቸለት ዑመር ባሺሩ መሆኑ ሁለቱ ተጫዋቾች በመድን ስብስብ ላይ እየፈጠሩት ስላለ ፈጣን ተፅዕኖ እንድናስብ የሚያስገድድ ነው።

ሌላው ማጥቃቱ ላይ ሊነሳ የሚችለው ነጥብ በግቦች ላይ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙ ተጫዋቾች ጉዳይ ነው። ቡድኑ እስካሁን ባደረጋቸው አራት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠራቸው አስር ግቦች በተለያዩ ስምንት ተጫዋቾች የተመዘገቡ ናቸው። ይህም በሊጉ ቀዳሚ የሚያደርጋቸው ሲሆን የቡድኑ ማጥቃትም በግለሰቦች ላይ ከመንጠልጠል ይልቅ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚታገዝ የመሆኑ ነገር በጥሩነት የሚነሳ ጉዳይ ነው።

ስለቡድናቸው መሻሻል ከለገጣፎ ለገዳዲ ድል በኋላ የተየቁት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ “ግቦች ስለገቡ በሚፈለገው መልኩ ቡድኑ መጥቷል ማለት አይቻልም። አራት ያገባ ቡድን ደካማ ነው ባይባልም የሚቀሩን ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል። ለእኔ ከግቦቹ ባለፈ ቡድኑ እንደቡድን በየዲፓርትመንቱ ያሉ ተጫዋቾች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይበልጥ በትኩረት ነው የምመለከተው ከዚህ አንፃር አሁንም ብዙ የሚቀሩን መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች አሉ።” ሲሉ ነበር የገለፁት።

ከአስከፊው ሽንፈት ማግስት መሻሻሎች ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን በሊጉ የመቆየት ውጥኑን ለማሳካት ገና ቀሪ ብዙ ነጥቦች ይጠበቁበታል። ታድያ ውጥናቸውን ለማሳካት ይህን ሰሞነኛ መነቃቃት የማስቀጠል ግዴታ ቢኖርባቸውም በውድድር ዘመኑ በቀጣይ ለሚገጥሟቸው ፈተናዎች ሁሉ “ከጨለማው በኋላ ብርሃን” ስለመኖሩ በሚገባ ትምህርት የወሰዱ ይመስላል።