በመቻል እና በአሚን መሐመድ ክርክር ዙርያ ውሳኔ ተላለፈ

መቻል በአሚን መሐመድ ጉዳይ በዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ ተላለፈበት።

ባሳለፍነው የውድድር ዓመት አጋማሽ ላይ መቻልን የተቀላቀለው የመስመር አጥቂው አሚን መሐመድ ቀሪ የስምንት ወር ኮንትራት እየቀረው በጊዜው ወደ ዝግጅት አልገባም በሚል ክለቡ ማገዱ ይታወቃል። ተጫዋች አሚን መሐመድም በጊዜው ወደ ዝግጅት እንድገባ የተደረገልኝ ጥሪ የለም በማለት ቅሬታውን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ አምርቷል። ጉዳዮን ሲመረምር የቆየው የዲሲፕሊን ኮሚቴም የሁለቱን ወገኖች መከራከርያ ሀሳብ ካዳመጠ በኋላ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም መሠረት ተጫዋች አሚን ላይ የተወሰነው የእግድ ውሳኔ ተገቢ ባለመሆኑ እግዱ እንዲሻር፣ ተጫዋቹ ወደ ሥራ እንዲመለስ፣ ያልተከፈለው ደሞዝ እንዲከፈለው እና መቻል ተጫዋቹን በክለቡ እንዲመለስ ካልፈለገ ውሉ ማጠናቀቂያ ጊዜ ያለውን ደሞዝ በመክፈል ማሰናበት እንደሚችል ተወስኗል። ይህን ውሳኔ ክለቡ በሰባት ቀን ተፈፃሚ የማያደርግ ከሆነ በፌዴሬሽኑ በኩል የተጫዋች ምዝገባ እና ዝውውር እንዲታገድ እና ምንም አይነት አገልግሎት እንዳያገኝ ተወስኗል። መቻል ይህን ውሳኔ የማይቀበል ከሆነ ይግባኝ የመጠየቅ መብቱ እንደሆነ ተመላክቷል።