የአሠልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 2-2 ወልቂጤ ከተማ

👉”ከዕረፍት በኋላ ባደረግነው ነገር የአቻው ውጤት ይገባናል” ዮርዳኖስ ዓባይ

👉”እንደ ጨዋታው የአቻ ውጤት አይገባንም ነበር።… ጌታነህ ማለት የወይን ጠጅ ማለት ነው ” ገብረክርስቶስ ቢራራ

አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው…

በጨዋታው ከዕረፍት በፊት ጥሩ አልነበርንም። ከእረፍት በኋላ ደግሞ በጣም የተሻለ ነበርን። እያሸነፍን የመጣንበት ነገር ዛሬም እንድናሸንፍ ትንሽ ጭንቀት ውስጥ የከተተን ይመስለኛል። ከዕረፍት በኋላ ደግሞ እንደታየው የተሻለ ሆነን በመጨረሻው ደቂቃ ግብ አስቆጥረናል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግቦችን እያስቆጠሩ ስለመሆኑ…

ምንም እንኳን ስኬታማ ብንሆንም መጀመሪያ ላይ የምንሳሳታቸው ኳሶች ዋጋ እያስከፈሉን ነው። ግን ለማሸነፍ ውስጣችን ያለው ነገር የመጨረሻውን ውጤት እያስተካከለው ነው። እስከ መጨረሻው የምንታገለው ነገር ውጤቶችን እንድናገኝ አድርጎናል ግን መጀመሪያ የምንሳሳታቸው ኳሶች ግቦች እንዲቆጠሩብን እያደረጉ ነው። ጨዋታውን ለማግኘት ደግሞ ብዙ ጉልበት እንድናወጣ እያስገደደን ነው። ከመጀመሪያው ግብ እያገባን ስህተቶችን እየቀነስን ብንመጣ ኖሮ ይሄ ሁሉ ነገር አይመጣም ነበር።

ስለተገኘው አንድ ነጥብ…

አንዱ ነጥብ ይገባናል። ከእረፍት በኋላ ባደረግነው ነገር የአቻው ውጤት ይገባናል። ስለዚህ የተገኘው አንድ ነጥብ ለሁለታችንም ቡድኖች ፍትሀዊ ነው።

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው…

ከሞላ ጎደል ጨዋታው ጥሩ ነው። እንደታየው ጥሩ ተጫውተናል። ከእረፍት በፊት ባስቆጠርናቸው ጎሎች እስከ 88ኛው ደቂቃ ድረስ እየመራን ነበር። ነገርግን እግርኳስ እንደዚህ ነው ፤ ባለቀ ሰዓት ምንም ነገር ሊከሰት ይችላል። እንደ ጨዋታው የአቻ ውጤት አይገባንም ነበር። ይህ ቢሆንም የመጣውን ውጤት እንቀበላለን።

በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ስላስተናሀዱበት ምክንያት…

እግርኳስ 90 ደቂቃ ትኩረት ይፈልጋል። ተጫዋቾችን ግን ሙሉ 90 ደቂቃ ትኩረት አድርጉ ማለት አትችልም። አንዳንድ ጊዜ በመሐል እንደዚህ አይነት ነገር ይከሰታል። ባለቀ ሰዓት የገባብን ከመዓዘን ምት የተመታ ኳስ ነው። ከዛ በፊት የተመቱ የመዓዘን ምቶችን ተከላክለን ጨርሰን ነበር። ግን ይህ ተቆጠረብን። እንዳልኩት እንቀበላለን።

ስለጌታነህ ከበደ ብቃት…

ጌታነህ ማለት የወይን ጠጅ ማለት ነው። የወይን ጠጅ እየቆየ ሲሄድ እንደሚጣፍጠው ማለት ነው። ጌታነህ ለእኔ ሁሌ ምርጡ ተጫዋቼ ነው።