ሪፖርት | ፋሲል ከነማ ሲዳማ ቡናን ረቷል

ዐፄዎቹ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ ድል ያገኙበትን ውጤት ሲዳማ ቡና ላይ አስመዝግበዋል።

ምሽት 01፡00 ላይ የሲዳማ ቡና እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ ሲደረግ ሲዳማዎች በዘጠነኛው ሳምንት መቻልን 2-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ሙሉዓለም መስፍንን በጉዳት ከስብስብ ውጪ በሆነው ሙሉቀን አዲሱ ተክተዋል። ዐፄዎቹ በበኩላቸው በዘጠነኛው ሳምንት ለገጣፎ ለገዳዲን 3-0 ከተረቱበት አሰላለፍ ሱራፌል ዳኛቸውን በበዛብህ መለዩ ቦታ ተክተው ቀርበዋል።

ጨዋታው ገና እንደተጀመረ ፋሲል ከነማዎች ለማጥቃት ወደ ሲዳማ የግብ ክልል ይዘውት የሄዱት ኳስ ሳጥን ውስጥ የግራ መስመር ተከላካዩ ሰለሞን በእጅ በመንካቱ የፍፁም ቅጣት ተሰጥቷቸዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ፍቃዱ ዓለሙ ግብ አድርጎት ፋሲል ከነማ መምራት ጀምሯል። በጊዜ ግብ ያስተናገዱት ሲዳማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ቢጥሩም ውጤታማ መሆን አልቻሉም። በ14ኛው ደቂቃም ቡልቻ ሹራ ሳጥኑ መግቢያ ላይ ቡድኑን አቻ የማድረጊያ የመጀመሪያ ጥቃት ሰንዝሮ ወጥቶበታል።

ፋሲሎች የኳስ ቁጥጥሩን ወደ ራሳቸው ለማድረግ እየጣሩ የሚያገኟቸውን ኳሶች በዓላማ ወደ ላይኛው ሜዳ እየወሰዱ ለተጨማሪ የግብ ምንጭነት ለመጠቀም ሲሞክሩ ታይቷል። በ19ኛው ደቂቃም ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ሽመክት የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ነክቶ ሲመለስ የመጀመሪያው ግብ ባለቤት ፍቃዱ አግኝቶይ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጎታል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሽመክት ከፍቃዱ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ተከላካዮችን በፍጥነት በማለፍ በቀኝ እግሩ የመታው ኳስ ሦስተኛ ጎል ሆኗል።

ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆነባቸው የመጣው ሲዳማዎች ሁለተኛ ግብ እንደተቆጠረባቸው ለፍፁም ቅጣት ምቱ መነሻ የሆነው ሰለሞን እና አማካዩ ቴዎድሮስን በማስወጣት ከባዱን ፈተና መጋፈጥ ይዘዋል። ይህ ቢሆንም ግን በ32ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት በተሻማና ሽመክት በቅርቡ ቋሚ ሆኖ በሞከረው አጋጣሚ ለሌላ ግብ ተዳርገው ነበር። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ በተመሳሳይ ከቆመ ኳስ በተፈጠረ አጋጣሚ ጊት ቡድኑን ሊያነሳሳ የሚችል የግንባር አጋጣሚ ፈጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል።

ዐፄዎቹ ሁለተኛውን አጋማሽም በፈጣን ሁኔታ ጀምረዋል። ገና በ48ኛው ደቂቃም ሀብታሙ ገዛኸኝ ከተከላካይ ጋር ታግሎ በግራ መስመር ላይ ያገኘውን ኳስ አክርሮ በመምታት አራተኛ ግብ ተቆጥሯል። አሠልጣኝ ሥዩም የአጥቂ መስራቸውን በማደስ ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ቢወጥኑም ጠንካራውን የፋሲል የኋላ መስመር በቀላሉ ማስከፈት አልቻሉም። በእንቅስቃሴ ረገድ ግን የተሻለ እድገት አሳይተው ነበር። በ63ኛው ደቂቃም ከመዓዘን ምት የተሻማ ኳስ ሙሉዓለም ተጨራርፎ ደርሶት ግብ ለማድረግ ቢሞክርም ሳማኬ ይዞበታል።

በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቀዝቀዝ ያለው የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ቀጣዩን ሙከራ ለማስተናገድ መገባደጃው አካባቢ መጠበቅ ግድ ብሏል። በዚህም 85ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለውን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው መናፍ ዐወል የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ፍሬው ሰለሞን በቀጥታ መረብ ላይ አሳርፎታል። ሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩት 6 ደቂቃዎች ማብቂያ ላይ አምሳሉ ጥላሁን ሳጥን ውስጥ ጥፋት ሰርቶ ሲዳማ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ይገዙ ቦጋለ የማሳረጊያ ጎል አድርጎት ጨዋታው 4ለ2 ተጠናቋል።