የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 ወላይታ ድቻ

👉”ጨዋታው በምንፈልገው መልኩ ሄዷል ፤ ማድረግ ያለብንን ነገር አድርገናል”ዘሪሁን ሸንገታ

👉”አቅማችን የፈቀደውን ነው ያደረግነው። አቅማችን ይሄ ነው ፤ በአቅማችን ልክ አስበናል” ፀጋዬ ኪዳነማርያም

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው…

ጨዋታው በምንፈልገው መልኩ ሄዷል ፤ ማድረግ ያለብንን ነገር አድርገናል። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ነገር አድርገናል። እርግጥ ሁለት ጎሎችን ካገባን በኋላ ትንሽ የመቀዛቀዝ ነገር ታይቶብን ነበር። የሆነው ሆኖ በአጠቃላይ ሦስት ግቦች አስቆጥተን ጨዋታውን አሸንፈን ወጥተናል።

ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ እየተቀዛቀዘ ስለሚመጣበት ምክንያት…

ይሄ ጥሩ ነገር ካደረግን እና ግቦችን ካስቆጠርን በኋላ ጨዋታውን ለመጨረስ ከማሰብ የሚመጣ ነው። 90 ደቂቃ የተሻለ ሆነን ግቦችን አስቆጥረን መሄድ እንችላለን። ግን እዚህ ላይ ትንሽ ክፍተት አለ። በቀጣይ ይሄንን አስተካክለን እንመጣለን።

ስለዋንጫ ፉክክር…

ዛሬ ላይ ሆኖ ስለዋንጫ መናገር አይቻልም። እኛ ፊታችን ላይ ያለውን ጨዋታ አሸንፈን ለመውጣት ነው የምናስበው።

ተጎድቶ ስለወጣው ግብ ጠባቂው ባህሩ…

ባህሩ ጥሩ ግብ ጠባቂ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ጥሩ ግብ ጠባቂዎች አንዱ ነው። ዛሬ ትንሽ ጉዳት አጋጥሞታል። ይህ ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ አላወቅንም። ግን ቻርለስም አለ።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው…

በጨዋታው በእንቅስቃሴ የጠበቅነውን ነገር ነው ያገኘነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈውም ከሀዋሳ ጋር ሲጫወት ቶሎ ነበር ግብ ያስቆጠሩት። ይህንን ተከትሎ በመጀመሪያው 15 ደቂቃ ጥንቃቄ አድርገን ግብ እንዳይቆጠርብን ነበር ተነጋግረን የገባነው። ነገር ግን መጠንቀቅ በሚገባን ነገር ላይ ሁለት ግቦች አስቆጥረውብናል። በዛሬው ጨዋታ እነቃልኪዳን ፣ እድሪስ እና ንጋቱን አጥተን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። ከአማካይ በላይ ቡድኑ ብዙ አስፈሪ አልነበረም። በአጠቃላይ በዛሬው ጨዋታ በሁለታችን መካከል የነበረው ልዩነት የልምድ አጨዋወት እና የቡድን ስብስብ ነው። በሁለቱ ነገሮች ነው የበለጡን። ይህንን ነገር መቀበል ያስፈልጋል። ይህንን ተቀብሎ ወደ ቀጣይ ጨዋታ መሄድ ነው የሚያዋጣው።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ ስላደረጉት ጥረት…

የጎል ዕድሎችን አግኝተናል። በሁለተኛውም አጋማሽ ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን አግኝተን ነበር። ግን ጊዮርጊሶች ከአንድ አንድ ነው የሚያስቆጥሩት። እኛ ግን ዕድሎችን እያገኘን እያመከንን ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመምራታቸው በፊት እና ከመሩ በኋላ የሚጫወቱበት መንገድ ይለያያል። ቅድም እንዳልኩት ዛሬ በልምምድ አጨዋወት ነው የበለጡን። እነርሱ በመጀመሪያው 15 ደቂቃ የራስ መተማመናቸውን አግኝተው ነው መጫወት የጀመሩት። ከኋላ ደግሞ ጠጣር ተከላካይ ነው ያላቸው። በብሔራዊ ቡድንም ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚያውቁ ተጫዋቾች ነው ያሉት። እኛ ስብስባችን ይሄ ነው። አቅማችን የፈቀደውን ነው ያደረግነው። አቅማችን ይሄ ነው ፤ በአቅማችን ልክ አስበናል። በቀጣይ ከጉዳት የሚመለሱ ተጫዋቾች ካሉ እነሱን ይዘን በአቅማችን ልክ ለመዘጋጀት እንሞክራለን።