ሪፖርት | ፈረሰኞቹ የጦና ንቦቹን በሦስት ጎል ብልጫ አሸንፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል በመውሰድ የደረጃ ሰንጠረዡን አናት ተረክቧል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ9ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን ሦስት ለምንም ያሸነፉበት አሰላለፍን ምንም ሳይለውጡ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ያለ ጎል አቻ የተለያየው ወላይታ ድች ግን የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርጓል። በዚህም ቃልኪዳን ዘላለም እና መሳይ ኒኮል አርፈው ስንታየሁ መንግሥቱ እና በኃይሉ ተሻገር በቀዳሚው አሰላለፍ ተካተዋል።

ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ጫና ፈጥረው መጫወት የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ5ኛው ደቂቃ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህም ከግራ እየተነሳ እንዲያጠቃ ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረው ቸርነት ጉግሳ አጥብቦ በተቃራኒ የሳጥኑ ክፍል ከቢኒያም በላይ የተቀበለውን ኳስ በቀጥታ በመምታት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የተከላካይ አማካዩ ጋቶች ፓኖም ከራሱ ክልል በረጅሙ የመታውን ኳስ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ከተከላካዮች ፈጥኖ በመውጣት በግራ እግሩ በድንቅ ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎት የፈረሰኞቹ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ብሏል።

ከጅምሩ ፈተና የጠናባቸው ወላይታ ድቻዎች ስንታየሁ መንግሥቱን ዒላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች በመላክ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢያስቡም እስከ 18ኛው ደቂቃ ድረስ አንድም ጥቃት ሳያስመለክቱ ቆይተዋል። ይባስ ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ሱሌይማን ሀሚድ ባሻማው እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ጨርፎ ለጥቂት በወጣበት አጋጣሚ ሦስተኛ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። ከላይ በጠቀስነው 18ኛው ደቂቃ ግን ያሬድ ዳዊት ወደ ሳጥን አሻምቶት ሳሙኤል ተስፋዬ ሊጠቀም ሲል ተጨርፎ እግሩ ስር የደረሰው ዘላለም አባቴ የቡድኑን የመጀመሪያ ሙከራ አድርጎት ወጥቶበታል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ኳሱን በተሻለ እያንሸራሸሩ መጫወትን የመረጡ ሲሆን በሚገኙ ክፍተቶች ግን ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ነበር። በተቃራኒው በመጠኑ ጫናው የቀነሰላቸው ድቻዎች ዘርዘር ብለው ወደ ፊት እየተጠጉ ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ጎል ፍለጋ መንቀሳቀስ ይዘዋል። 36ኛው ደቂቃ ላይም እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም መሰረት አድርገው እየተጫወቱበት በነበረው አጨዋወት አናጋው ባደግ ከግራ መስመር ያሻገረውም ኳስ ረጅሙ አጥቂ ስንታየሁ በተከላካዮች መካከል ዘሎ በግንባሩ ወደ ግብ ቢመታውም ለጥቂት አግዳሚውን ታኮ ወጥቶበታል። በድጋሚ በ44ኛው ደቂቃም ሳሙኤል ከመዓዘን ምት ያሻማው ኳስ በረከት ሲሞክረው በተመሳሳይ ወጥቶበታል። አጋማሹም 2-0 ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በ48ኛው ደቂቃ ወላይታ ድቻ እጅግ አስቆጪ ዕድል አምክኗል። በዚህም ስንታየሁ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተከላካዮችን በማለፍ ለመምታት ቢያመቻቸውም የመጨረሻው ውሳኔው ጥብቅ ሳይሆን ምቱን ግብ ጠባቂው ባህሩ መልሶታል። በ55ኛው ደቂቃም ሌላ ለግብ የቀረበ ዕድል ከቆመ ኳስ ፈጥረው በረከት ወጥቶበታል። የጨዋታውን ግለት ለመቆጣጠር አሁንም ከኳስ ጋር ጊዜ ማሳለፍን የመረጡት ጊዮርጊሶች አልፎ አልፎ የድችን ግብ በፈጣን ሽግግር ቢጎበኙም የጠራ ዕድል ግን መፍጠር አልቻሉም።

አሁንም የጊዮርጊስ ግብ ክልል መድረስ ያላቆሙት ወላይታ ድቻዎች በ76ኛው ደቂቃ በኃይሉ ተሻገር በቀኝ የሳጥኑ ክፍል ሆኖ በሞከረው ኳስ በጉዳት ተቀይሮ የወጣውን ባህሩ የተካው ሉክዋጎን ለመፈተን ሞክረዋል። ከደቂቃ በኋላ ግን ለሦስተኛ ግብ እጅ ሰጥተዋል። በ62ኛው ደቂቃ አማኑኤልን ቀይሮ የገባው ዳግማዊ አርአያ አጎሮ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ከግራ መስመር መሬት ለመሬት ያሻማውን ኳስ በአንድ ንክኪ መረብ ጋር አዋህዶታል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ ሳሙኤል ድቻን ከባዶ መሸነፍ የምታድን የመጨረሻ ጥቃት ሰንዝሮ የጎኑን መረብ ታኮ ወጥቶበታል። ጨዋታውም በፈረሰኞቹ 3ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል።