የአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እና ሀዲያ ሆሳዕና ጉዳይ ውሳኔ ተሰጥቶበታል

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ ተይዞ የነበረው የሀዲያ ሆሳዕና እና አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ጉዳይ ውሳኔ ተላልፎበታል።

ሀዲያ ሆሳዕና በተጠናቀቀው የ2014 የውድድር ዓመት በአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እየተመራ እንደነበር አይዘነጋም። የውድድር ዓመቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ግን አሠልጣኙ እና ክለቡ ከውል ስምምነት ማቋረጥ ጋር በተያያዘ አለመስማማት ውስጥ የነበሩ ሲሆን ጉዳያቸውም ወደ ሀገሪቱ የእግርኳስ የበላይ አካል አምርቶ ሲመረመር ቆይቷል። ጉዳዩ በስምምነት እንዲቋጭ ተደርጎ ሳይሳካ ከቀረ በኋላም ረዘም ላሉ ጊዜያት አቤቱታ አቅራቢ አሠልጣኝ ሙሉጌታ እና ተከሳሽ ሀዲያ ሆሳዕና እግርኳስ ክለብ ለዲሲፕሊን ኮሚቴው የመከራከሪያ ሀሳባቸውን ሲያቀርቡ የነበረ ሲሆን ኮሚቴውም የሁለቱን ወገኖች የጽሑፍ ክርክር ተመልክቶ ተከታዩን ውሳኔ መስጠቱን የአሠልጣኙን ጉዳይ ከያዙት ጠበቃ አቶ ብርሃኑ በጋሻው አረጋግጠናል።

በዚህም የሀዲያ ሆሳዕና እግርኳስ ክለብ ለአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ያልከፈለውን የሰኔ እና ሐምሌ 2014 ደሞዝ በ7 ቀናት ውስጥ እንዲከፍል አለበለዚህ ከተጫዋቾች ምዝገባ እና ዝውውር እንዲታገድ እንዲሁም ክለቡ በሰጠው መልስ ለፊርማ የወሰደው ቅድመ ክፍያ ተመላሽ እንዲደረግ የተደረገውን የፊርማ የገንዘብ ውል ስምምነት ፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት በመቅረብ ያልተዋዋሉት እና በፌዴሬሽኑ ፀድቆ ማህተም ያረፈበት ሆኖ ባለመገኘቱ ለፊርማ ከተከፈለው ላይ የቀሪ ጊዜ ተመላች ያድርግልን በማለት የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

በተጨማሪም አሠልጣኝ ሙሉጌታ ከክለቡ ለመሰናበት ከጠየቀ በኋላ መልሶ ወደ ክለቡ ልመለስ በማለት ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ መደረጉ በውሳኔው የ5 ገፅ እባሪ ተያይዟል።