ዋልያዎቹ የቻን ዝግጅታቸውን ሞሮኮ ላይ እንደሚያደርጉ ተገለፀ

ጥር ላይ የቻን ውድድር ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፊል የዝግጅት ጊዜውን ሞሮኮ ላይ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።

የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የፊታችን ጥር 6 በአልጄሪያ አራት ከተሞች እንደሚደረግ ይታወቃል። የማጣሪያ ጨዋታዎችን አልፎ በውድድሩ መሳተፉን ያረጋገጠው የሀገራችን ብሔራዊ ቡድንም በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ አልጄሪያ፣ ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር ተደልድሏል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቹ የሊጉን ጨዋታዎች በአካል ድሬዳዋ ስታዲየም ተገኝተው ተጫዋቾችን እየተመለከቱ ሲሆን ከትናንት በስትያም ለ42 እጩ ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል።

የተጫዋቾቹን ጥሪ በተመለከተ ሴካፋ አሠልጣኝ ውበቱ አባተን አናግሮ በሰራው ዘገባ ላይ አሠልጣኝ ውበቱ ከተወሰኑ የሀገር ቤት የልምምድ ቆይታ በኋላ ወደ ሞሮኮ አምርተው መደበኛ ዝግጅታቸውን ውድድሩ እስኪጀምር እንደሚከውኑ ገልፀዋል። እንደ ሴካፋ ድረ-ገፅ ከሆነ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችንም ለማግኘት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አሠልጣኙን ዋቢ አድርጎ አትቷል።