የአሠልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-0 ፋሲል ከነማ

👉”ዛሬ ተጫዋቾቻችን ሜዳ ላይ ላሳዩት ተነሳሽነት እና ተጋድሎ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው” ፀጋዬ ኪዳነማርያም

👉”አንዳንዴ አሸንፌ ወጣለው ብለህ ባሰብክበት ልክ ላታገኘው ትችላለህ” ኃይሉ ነጋሽ

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው…

የዛሬው ጨዋታ ተስተካካይ ጨዋታ ነው። ሌሎች ቡድኖች ከእኛ የተሻለ ጨዋታ ተጫውተዋል። የሆነው ሆኖ ይህን ተስተካካይ ጨዋታ በነጥብ ማጀብ ነበረብን። በመጀመሪያ ደረጃ እግዚአብሔርን ነው ማመስገን የምፈልገው። ምክንያቱም እዚህ ድሬዳዋ ከመጣን 5 ጨዋታዎች አድርገን 3 አሸንፈን አንድ አቻ ወጥተን በቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ነው የተሸነፍነው። ይሄ ቀላል ውጤት አይደለም። ከምንም በላይ ግን ዛሬ ተጫዋቾቻችን ሜዳ ላይ ላሳዩት ተነሳሽነት እና ተጋድሎ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለው። የዛሬው ውጤታችን ነጥባችንን ወደ ሁለት አሀዝ አሳድጎታል። ወደ ዕረፍት እየተቃረብን ስለሆነ ይሄ ትልቅ ነገር ነው። ዛሬ ከፍተኛ የሜዳ ላይ ቁርጠኝነት ነበረን። በሁሉም ነገር ዲሲፕሊን ነበርን። በመጀመሪያ ደረጃ ፋሲል ትልቅ ክለብ ነው። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ይበዙበታል። ይህንን ተከትሎ ከባለፈው የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ስህተታችን ተምረን በመጀመሪያው 15 ደቂቃ ተጠንቅቀን ነው የተጫወትነው። እነሱ ቶሎ ቶሎ ለማጥቃት ቢያስቡም እኛ በትዕግሥት እየተከላከልን በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሞክረናል። በአጠቃላይ ዛሬ በተለየ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ተጫውተን ድል አሳክተናል።

ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ሽንፈት በኋላ ዛሬ ስለተስተካከለው ነገር…

ዛሬ እንደቡድን ነው የተጫወትነው። እንደ ቡድን ያጣከው ነገር አንዳንድ ጊዜ በልምድ እና ፍላጎት ይሸፈናል። ባለፈው ሳምንት ፈዘን ነው የነበረው ፤ ምክንያቱም በጎል ስለተቀደምን። ዛሬ የመጀመሪያው የተከላካይ አማካያችን ንጋቱ ከጉዳት ተመልሶልናል። ፋሲሎች አማካይ ላይ ጠንካራ ስለሆኑ ይህ ቦታ ወሳኝ ነበር። ሁለተኛ ደጉም ወደ ቀዳሚ አሰላለፍ ተመልሷል። በተጨማሪም ግብ ጠባቂያችን ቢኒያምም ተመልሶልናል። ስለዚህ በየዲፓርትመንቱ የተሻለ ነገር ነበር ዛሬ። ዞሮ ዞሮ ዛሬም በአቅማችን ልክ በተራበ መንገድ ተጫውተን አሸንፈናል ፤ በዚህም ደስ ብሎኛል።


አሰልጣኝ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ

ስለጨዋታው…

መጀመሪያ ወላይታ ድቻዎች ጥቅጥቅ ብለው ነበር የሚጫወቱት። ያንን አስከፍቶ ለመጫወት ያደረግነው ጥረት አልሰራም ፤ እሱ ላይ ትንሽ ጥሩ አልነበረም። በሁለተኛው አጋማሽም ተጫዋቾቻችን ላይ መነቃቃት እንዲኖር ተናጋግረን ነበር የገባነው። ባገኙት አጋጣሚ ጎል አስቆጥረው ልንሸነፍ ችለናል።

ስለሽንፈታቸው ምክንያት …

ለመከላከል የሚገባ ቡድን ክፍተት ያሳጣሀል። ያንን ክፍተት መፍጠር ከእኛ ይጠበቃል። ያን ለማድረግ ተጫዋቾቻችን የሚችሉትን አድርገዋል ፤ ግን አልተሳካም። አንዳንዴ አሸንፌ ወጣለው ብለህ ባሰብክበት ልክ ላታገኘው ትችላለህ ፤ ብቻ ዛሬ ተሸንፈናል።

በሁለተኛው አጋማሽ ስለተደረጉ ቅያሬዎች…

ሱራፌል መጠነኛ ጉዳት ስለነበረበት እሱን ቀይረናል ፤ ሀብታሙንም እንደዚሁ። ግን የገቡትም ተጫዋቾች ጥረት አድርገዋል ግን ባሰብነው ልክ አልሄደልንም።