የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዲ ኤስ ቲቪ የቀጥታ ስርጭት ሊመለስ ነው

ከዓለም ዋንጫ መጠናቀቅ በኋላ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዲ ኤስ ቲቪ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የምስል መብት የገዛው ዲ ኤስ ቲቪ ወቅታዊው የብዙዎች ትኩረት የሆነውን የዓለም ዋንጫ ለተከታዮቹ ለማድረስ ከ8ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ሁለት ጨዋታዎች ጀምሮ ያለፉትን አራት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ሳምንታትን እያስተላለፈ እንደማይገኝ ይታወቃል። አሁን ግን ለሊጉ ድምቀት የሰጠው ይህ ስርጭትም ከ13ኛ ሳምንት ጀምሮ እንደሚመለስ ድረ-ገፃችን አረጋግጣለች።

የዲ ኤስ ቲቪ የቀረፃ እና ፕሮዳክሽን ባለሙያዎች ነገ ዓርብ ድሬዳዋ እንደሚገቡ የሰማን ሲሆን የዓለም ዋንጫው እሁድ ከተጠናቀቀ በኋላ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ13ኛ ሳምንት ሰኞ ሲቀጥል የጨዋታ ሳምንቱን ሙሉ ለተመልካች እንደሚያደርሱ ተመላክቷል። በድሬዳዋ ስታዲየም ከሚደረገው የመጨረሻ ሳምንት ውጪ ግን ምናልባት በሜዳ አለመመቸት ምክንያት የተራዘሙት አራት ተስተካካይ ጨዋታዎች አዲስ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ ሽፋን ላያገኙ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።