ከፍተኛ ሊግ | የ5ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

በቶማስ ቦጋለ እና ጫላ አቤ

ከፍተኛ ሊጉ በሦስቱ አዘጋጅ ከተሞች ዛሬ በተደረጉ 11 ጨዋታዎች ቀጥሎ አምስቱ ጨዋታዎች 1-0 ሲጠናቀቁ የነገ ጨዋታዎች ከመከናወናቸው አስቀድሞ ሁለት ምድቦች አዳዲስ መሪዎች አግኝተዋል።

የ03:00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ በምድብ ‘ሀ’ ወልዲያ እና አዲስ ከተማ ክፍለከተማን ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢታይም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ግን ወልዲያዎች የተሻሉ ነበሩ። በበድሩ ኑርሁሴን እና ኃይሌ ጌታሁን የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ ከነሱ በተሻለ የግብ አጋጣሚዎችን ያገኘው ብሩክ ጌታቸው ደግሞ ያገኛቸውን የግብ አጋጣሚዎች ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል። በአዲስ ከተማዎች በኩል 39ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ በቀለ ከቀኝ መስመር ወደግብ ያደረገውና የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ የወጣው ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ሙከራቸው ነበር።

ከዕረፍት መልስ አዲስ ከተማዎች በተሻለ መረጋጋት ጨዋታውን ሲያስቀጥሉ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ወልዲያዎች በአንጻሩ የሚያገኙትን ኳስ ወደፊት ቶሎ ቶሎ ለመውሰድ በመጓጓት መረጋጋት ተስኗቸው ተስተውሏል። በተለይም 64ኛው ደቂቃ ላይ ኃይሌ ጌታሁን ከግራ መስመር ያሻገረው እና በድሩ ኑርሁሴን ረዝሞበት ሳያገኘው የቀረው ኳስ አስቆጪ ሙከራቸው ነበር። አዲስ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ እየተሻሻሉ ቢሄዱም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ጨዋተውም ያለግብ ተጠናቋል።

ጅማ ላይ በምድብ ‘ለ’ ቀዳሚ በነበረው ጨዋታ ይርጋ ጨፌ ቡና እና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ተገናኝተዋል። በውጤቱም ሥዩም ደስታ ዕረፍት ሊወጡ ሲቃረቡ ባስቆጠራት ግብ ቀዳሚ የሆኑት ይርጋ ጨፌዎች ከዕረፍት መልስ ዮሐንስ ኪሮስ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ደግሞ ኦኒ ዑጅሉ ባስቆጠሯቸው ግቦች 3-0 ማሸነፍ ችለዋል።

በምድብ ‘ሐ’ ሆሳዕና ላይ የመጀመሪያ ጨዋታ የሆነው የቡራዩ ከተማ እና የሀምበሪቾ ዱራሜ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ የሆነና ጥሩ እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን ጨዋታው በተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ በረከት ወንድሙ ያሻገረውን ኳስ የፊት መስመር ተጫዋቻቸው ዳግም በቀለ በጥሩ ሁኔታ በማስቆጠር ሀምበሪቾ ዱራሜን መሪ ማድረግ ችሏል። በቡራዩ ከተማ በኩል የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋች የነበረው አብዲ ሁሴን ኳስ በማሰራጨት እና ለተከላካይ ሽፋን በመሰጠት በኩል አመርቂ የሆነ እንቅስቃሴ ሲያስመለክተን ነበር። ጨዋታው ፉክክር በሞላበት መልኩ እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ በ40ኛው ደቂቃ የሀምበሪቾ ዱራሜው ግብ ጠባቂ አስራት ሚሻሞ ጭንቅላቱ ላይ ባጋጠመው ከፍተኛ ግጭት በሁለተኛው ግብ ጠባቂያቸው በምንታምር መለሰ ሊቀየር ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ቡራዩ ከተማዎች አቻ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በእንዳለ ዮሐንስ የሚመራው የሀምበሪቾ ዱራሜ የተከላካይ መስመር ግቡን ሳያስደፍር መውጣት የቻለ ሲሆን በነቃልአብ በጋሻው እና ስንታየው አሸብር የሚመራው የአማካይ ክፍል በጥሩ ሁኔታ ሲንቀሳቀስ ተመልክተናል። የጨዋታው መገባደጃ አከባቢ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች የሰዓት መግደል ሙከራ ሲያደርጉ ጨዋታውም ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ሀምበሪቾ ዱራሜ የማሸነፍ ግስጋሴውን በማስቀጠል ከአራት ጨዋታዎች 12 ነጥቦች በማስካት ከነገ ጨዋታዎች በፊት ወደ አንደኝነት መጥቷል።

የ05:00 ጨዋታዎች

በባህር ዳሩ የዱራሜ እና ጋሞ ጨንቻ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ጋሞዎች የተሻሉ ነበሩ። በተለይም 27ኛው ደቂቃ ላይ ፍስሐ ቶማስ ከቀኝ መስመር ወደግብ ሞክሮት የላዩን አግዳሚ ታኮኮ የወጣው ኳስ እና 42ኛው ደቂቃ ላይ ፍስሐ ቶማስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ለገሠ ዳዊት ወደግብ ሞክሮት ግብጠባቂው ማፑቱ ይስሃቅ የመለሰው ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በሚያገኙት ኳስ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ሲከተሉ የነበሩት ዱራሜዎች ከተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ ለመገኘት እና የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ታይቷል።

ከዕረፍት መልስም ጋሞ ጨንቻዎች በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ሲቀጥሉ 72ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው በሰለሞን ጌታቸው ግብ መሪ መሆን ችለዋል። 

ዱራሜዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ይበልጥ ተነቃቅተው ሁለት ፈታኝ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። 75ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ከተሰጠ የማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ  ያገኘው ተስፋሁን ተሾመ በግንባሩ በመግጨት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው እና የግቡ የቀኝ ቋሚ ግብ ከመሆን አግደውታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ዳግም ደሳለኝ በግንባሩ በመግጨት ኳሱን ወጥቶ ከነበረው ግብ ጠባቂው ማሳለፍ ቢችልም አምበሉ በለጠ በቀለ በፍጥነት ደርሶ ኳሱን ማስወጣት ችሏል። ጨዋታውም በጋሞ ጨንቻ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህም ውጤት መሰረት ጋሜ ጨንቻ ከነገ ጨዋታዎች በፊት ምድቡን በ11 ነጥቦች መምራት ጀምሯል።

ረፋድ ላይ በተደረገው የምድብ ‘ለ’ ጨዋታ
ከንባታ ሺንሺቾ አዱኛ ገብረመድኅን 88ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ ቂርቆስ ክፍለ ከተማን 1-0 መርታት ችሏል።

የ08:00 ጨዋታዎች

ብርቱ ፉክክር በታየበት የምድብ ‘ሀ’ የቡታጅራ ከተማ እና ሰንዳፋ በኬ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል በኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ለመውሰድ ረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ተደርጓል። 35ኛው ደቂቃ ላይ ሰንዳፋዎች መሪ መሆን ችለዋል። በማራኪ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የወሰዱትን ኳስ በስተመጨረሻም ማሙሽ ደባሮ በጥሩ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። 38ኛው ደቂቃ ላይ ቡታጅራዎች ፈታኝ ሙከራ ሲያደርጉ ከማዕዘን የተሻማው ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ ያገኘው ካሳሁን ገብረሚካኤል ከረጅም ርቀት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም ኳሱ የግቡን የቀኝ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በቀኝ መስመር የተሰጠውን የቅጣት ምት የቡታጅራው ክንዴ አብቹ በአስደናቂ ሁኔታ በማስቆጠር ቡድኑ አቻ ሆኖ ወደ ዕረፍት እንዲያመራ አስችሏል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በተመሳሳይ ሂደት ቀጥሏል። በአጋማሹ የተሻለው የመጀመሪያ ሙከራም 60ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ የሰንዳፋ በኬው ማሙሽ ደባሮ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ያገኘው መሳይ ሰለሞን በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡ የግራ ቋሚ ገጭቶ መልሶበታል። ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ሁለቱም ቡድኖች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። በጨዋታው መገባደጃ ላይም ቡታጅራዎች ከቆመ ኳስ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው የግቡ ቋሚ መልሶባቸዋል። ጨዋታውም 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከምሳ በኋላ ጅማ ላይ የተደረገው ተጠባቂ ጨዋታ በሰፊ የግብ ልዩነት ተጠናቋል። የወቅቱን የምድብ ‘ለ’ መሪ ሻሸመኔ ከተማን ከአዲስ አበባ ከተማ ባገናኘው ጨዋታ የመዲናዋ ክለብ በመጀመሪያዎቹ 13 ደቂቃዎች በሙሉቀን ታሪኩ እና ኤርሚያስ ኃይሉ ግቦች 2-0 መምራት ችሏል። ሻሸመኔዎች ከአምስት ደቂቃ በኋላ ‘ አምረላ ደልታታ ባስቆጠራ ግብ ልዩነቱን ማጥበብ ቢችሉም አዲስ አበቤዎቹ ከዕረፍት መልስ
በሙሉሰው መኮንን እና ከማል ሀጂ ሁለት ግቦችን በማከል ጨዋታውን በ4-1 ውጤት ጨርሰዋል። አዲስ አበባዎች ባሳኩት ድል ነጥባቸውን 10 በማድረስ ከሻሸመኔ ጋር ያላቸውን ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ አድርገዋል።     

በምድብ ‘ሐ’ ሁለተኛ ጨዋታ ኦሜድላ እና የየካ ክፍለ ከተማ ተገናኝተው በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረው እንቅስቃሴ በየካ የበላይነት የተስተዋለበት እና በኦሜድላ በኩል የተቀዛቀዘ እና ጉልበት ላይ ያተኮረ አጨዋወት ያየንበት ነበር። ይህም አጨዋወታቸው በየካዎች የበላይነት እንዲወሰድባቸው አድረጓቸዋል። ብዙም የግብ ሙከራ ባልታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የኃይል ሚዛኑ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የየካ ክ/ከተማ ሲሆን በግብ ሙከራ በኩል ከመጀመሪያው አጋማሽ በአንፃሩ የተሻለ የግብ ሙከራ የተመለከትንበት ነበር። የካዎች ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ያከናወኑ ቢሆንም እስከ 81ኛው ደቂቃ ድረስ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ቆይተዋል። በ81ኛው ደቂቃ የፊት መስመር ተጫዋቻቸው የሆነው ብስራት በቀለ በድኑን አሸናፊ ያደረገችውን ግብ አስቆጥሮ ሙሉ ሦስት ነጥብ የካ ክ/ከተማ እንዲያገኝ ረድቶታል። በጨዋታውም የኦሜድላ ተጫዋቾች ኃይል የቀላቀለ እንቅስቃሴ በማድረግ ከእለቱ የመሀል ዳኛ ጋር ሲጋጩ ተስተውሏል። ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላም የኦሜድላ ተቀያሪ ተጨዋቾች እና ሜዳ ውስጥ የነበሩት ተጫዋቾች በጨዋታው ዉጤት እና በዳኞቹ ውሳኔዎች ደስተኛ አለመሆናቸውን በሚያሳይ መልኩ ተቃውሟቸውን ሲገልፁ ተስተውሏል።

የ10:00 ጨዋታዎች

ቀዝቃዛ በነበረው የዕለቱ የባህር ዳር የመጨረሻ ጨዋታ ጅማ አባ ቡና እና ሀላባ ከተማ ሲገናኙ የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል የሚቆራረጡ ቅብብሎች በዝተው የታዩበት ሲሆን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ግን ሀላባዎች የተሻሉ ነበሩ። 23ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን ተሾመ የትኩረት ማነስ እና አለመረጋጋት ሲስተዋልበት የነበረው ግብ ጠባቂ ሌሊሳ ታዬ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ሠርቶ መቆጣጠር ያልቻለውን ኳስ ቢያገኘውም እጅግ ደካማ በሆነ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። በተደጋጋሚ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ሀላባዎች ወደ ዕረፍት ከማምራታቸው በፊት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በክሬ መሐመድ በቀኝ መስመር የተሰጠውን የቅጣት ምት ጥሩ አድርጎ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስም ሀላባዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ 51ኛው ደቂቃ ላይ ምስጋናው ግርማ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሙሉቀን ተሾመ ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መልሶበታል። በጨዋታው የግብ ዕድል ለመፍጠር መቸገራቸውን የቀጠሉት ጅማ አባ ቡናዎች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራቸውን 57ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ጃፋር ከበደ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የላዩን አግዳሚ ተጠግቶ ወጥቶበታል። በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ የተጋጣሚ የግብ ክልል በቶሎ የሚደርሱት በርበሬዎቹ በመጨረሻም ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። ሰዒድ ግርማ አመቻችቶ ያቀበለው ኳስ የደረሰው ምስጋናው ግርማ ወደግብ ሲመታ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ሰዒድ ግርማ አስቆጥሮት ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ በኋላም ሀላባዎች ጨዋታውን አረጋግተው 1-0 በማሸነፍ ማጠናቀቅ ችለዋል።

በምድብ ‘ለ’ የመጨረሻ ጨዋታ አምቦ ከተማ እና ካፋ ቡናን አገናኝቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ባህሩ ከድር ለካፋ ቡና እንዲሁም ኢብሳ ጥላሁን ለአምቦ ከተማ ባስቆጠሯቸው ግቦች 1-1 ተጠናቋል። ከዕረፍት መልስ ጨዋታ ሊጠናቀቅ 13 ደቂቃዎች እስኪቀሩት ድረስ በተመሳሳይ ውጤት ቢቀጥልም ዮናታን ከበደ በ77ኛው እና 85ኛው ደቂቃዎች ከመረብ ያሳረፋቸው ግቦች ካፋ ቡናን የ3-1 ድል ባለቤት አድርገዋል።

ሆሳዕና ላይ የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ የሆነው የሶዶ ከተማ እና የነገሌ አርሲ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር እና በግብ ሙከራ በኩል የነገሌ አርሲ የበላይነት የታየበት እና ፈጣን እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ነበር። በ20ኛው ደቂቃ በሶዶ ከተማዎች የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የነገሌ አርሲ ተጫዋች ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ ቦጋለ በማስቆጠር ነገሌ አርሲን መሪ ማድረግ ሲችል ብዙም ሳይቆይ በ22ኛው ደቂቃ የነገሌ አርሲው ተጫዋች ዱሬሳ ገመቹ  ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በድንቅ አጨራረስ በማስቆጠር ነገሌን የ2-0  መሪ ማድረግ ችሏል። በዚህም ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሶዶ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ይልቅ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ያደረጉ ቢሆንም ጨዋታውን በመቆጣጠሩ ረገድ ነገሌ አርሲዎች የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። በነገሌ አርሲ በኩል መሀል ሜዳውን በበላይነት በልጠው እንዲጫወቱ ሲረዳ የነበረው ሰለሞን ገመቹ ሲሆን በመከላከሉ ረገድ ግብ ጠባቂያቸው አባቱ ጃርሶ ጥሩ ጥሩ የሆኑ የግብ ሙከራዎችን ሲያመክን እና በቀኝ መስመር በኩል ቱፋ ተሽቴ ጥሩ የሆነ ኦንቅስቃሴ ሲያደርግ ተመልክተናል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 12 ደቂቃ ሲቀረው በ78ኛው ደቂቃ ሶዶ ከተማን ከሽንፈት ያላዳነች ግብ አሸናፊ ሽብሩ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በነገሌ አርሲዎች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።